ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የብርሃነ ልደቱን ትዕይንት በጎበኑበት ወቅት ቅድስት ሀገርን እንድናስብ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በጣሊያን ከግሬቾ አካባቢ የተበረከተውን እና በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የተተከለውን የገና ዛፍ እና የብርሃነ ልደቱን ትዕይንት በመጥቀስ ለልዑካኑ ባደረጉት ንግግር፣ የልደቱ ትዕይንት “ከ800 ዓመታት በኋላ የገናን ድባብ ለማስታወስ ያለመ መሆኑን አስታውሰዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በንግግራቸው፥ “ከአሲሲ ከተማ የመጣው ምስኪኑ ሰው በሃሳብ ወደ ቅድስት ሀገር ያደረገው ጉዞ፥ አሁንም በሕይወታችን የግሬቾ ዋሻዎችን በመመልከት የቤተልሔም መልክዓ ምድርን እንድናስታውስ ያደርጉናል" ብለዋል ።
በዚያች ትንሽ መንደር የገና ትዕይንቶችን ለመመልከት ብዙ ወንድሞች፣ ወንድ እና ሴት ምዕመናን ከተለያዩ ቦታዎች ይመጡ እንደ ነበር አስታውሰው፥ ከዚህ የተነሳ ዛሬ የምንመለከተው ሕያው የብርሃነ ልደቱ ትዕይንት መፈጠሩን አስረድተዋል። ዘንድሮ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በተዘጋጀው የብርሃነ ልደቱ ትዕይንት ተነስተን በዓይነ ሕሊናችን ግሬቾን ስናስብ ይህም ወደ ቤተልሔም ይወስደናል ብለዋል። ሥጋን ለብሶ ሰው የሆነው እግዚአብሔርን፣ ትንሹን እና ድሃውን ኢየሱስ ክርስቶስን ስናስብ፣ ድሃ እና መከላከያ የሌላቸውን የቅድስት አገር ነዋሪዎችን በተለይም ሕፃናት እና ወላጆቻቸው እያሳለፉ ያለውን ስቃይ በማሰብ ቅርበታችን እና መንፈሳዊ ድጋፋችንን እንገልጽላቸዋለን ብለው፥ የጦርነቱ ዋጋ ከፋዮች እነዚህ ናቸው” ብለዋል።
ጸጥታ እና ጸሎት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ንግግራቸውን በመቀጠል፥ “በእያንዳንዱ የብርሃን ልደቱ ትዕይን ፊት፣ በቤታችን የተሠሩትንም ቢሆን፥ ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት በቤተልሔም የሆነውን ነገር እናስታውሳለን” ሲሉ አስምረውበታል። ይህም በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ውስጥ የጸጥታ እና የጸሎት ፍላጎትን ሊያነቃቃ ይገባል ብለው፥ ጸጥታ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚነግረንን ለማዳመጥ የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።ጸሎትም የአመስጋኝነትን እና የርኅራኄን፥ ምናልባትም የብርሃነ ልደቱ ትዕይንት በውስጣችን የሚቀሰቅሰውን እንባ ለመግለጽ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል። በዚህ ሁሉ ማርያም የእኛ አርአያ በመሆን ምንም ሳትናገር ነገር ግን በልቧ ታስብ እና ታወድስ እንደነበር አስታውሰዋል።
የገና ዛፍ አካባቢን የመንከባከብ አስፈላጊነት ያስታውሰናል
በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በብርሃነ ልደቱ ትዕይንት አጠገብ የተተከለው 28 ሜትር ከፍታ ባለው ዛፍ ላይ የተሰቀሉ የኮከብ ምስሎች እና ሌሎች የተለያዩ የሕጻናት መጫወቻ አሻንጉሊቶች፥ ካሪታስ ለተሰኘ ካቶሊካዊ የዕርዳታ አከፋፋይ ድርጅት የሚሰጡ መሆናቸው ቅዱስነታቸው ገልጸው፥
ይህም በየአካባቢያችን የሚበቅሉ ዛፎችን እና የጋራ መኖሪያ ምድራችንን የመንከባከብ አስፈላጊነትን በማጉላት እንድናሰላስል የሚያደርገን አጋጣሚ እነሆነ ተናግረው፥ “እነዚህ ትንንሽ ምልክቶች በሥነ-ምህዳር ለውጥ መካከል ለእግዚአብሔር ስጦታዎች የምንሰጠው የአክብሮት እና የምስጋና ምልክቶች ናቸው” ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ረፋዱ ላይ ከልዑካን ቡድኑ ጋር ከተገናኙ በኋላ ከሰዓት በኋላ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው እና በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የሚከበረው የብርሃነ ልደቱ ትዕይንት የምርቃት ሥነ-ሥርዓት ተፈጽሟል። ሥነ-ሥርዓቱን የመሩት የቫቲካን ከተማ ርዕሠ መስተዳድር ብፁዕ ካርዲናል ፈርናንዶ ቬርጌዝ አልዛጋ መሆናቸው ተመልክቷል።