ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የብርሃነ ልደቱ ትዕይንት ትህትናን እና ደስታን ያስተምረናል አሉ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ እንደምን አረፈዳችሁ! ቅዱስ ፍራንችስኮስ ከስምንት መቶ ዓመታት በፊት ማለትም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1223 ዓ. ም. ጣሊያን ውስጥ ግሬቾ በተባለ አካባቢ የብርሃነ ልደቱን ትዕይንት አዘግጅቶ ነበር። ትዕይንቶች ዛሬ በመኖሪያ ቤቶች እና በሌሎች ቦታዎች እየተዘጋጁ ባሉበት በዚህ ወቅት አመጣጡን በድጋሚ ማየቱ መልካም ነው።
የቅዱስ ፍራንችስኮስ ዓላማ ምን ነበር? እስቲ እርሱ እራሱ የተናገራቸውን እንስማ፥ “ትዕይንቱን በቤተልሔም የተወለደውን ሕፃኑን ኢየሱስ ክርስቶስን ማስመሰል እፈልጋለሁ። ለጨቅላ ሕፃን የሚያስፈልጉ ነገሮችን ከማጣቱ የተነሳ የደረሰበትን መከራ በዓይነ ሕሊና ማስታወስ እፈልጋለሁ። በከብቶች በረት ውስጥ እንደተቀመጠ፣ እንዴትስ በበሬ እና በአህያ መካከል እንደተኛ መመልከት እፈልጋለሁ" በማለት ተናግሮ ነበር። ቅዱስ ፍራንችስኮስ የሚያምር የጥበብ ሥራ ማሳየት አልፈለገም። ነገር ግን በብርሃነ ልደቱ ትዕይንት አማካይነት የኢየሱስ ክርስቶስን ትሕትና፣ የደረሰበትን መከራ፣ ለእኛ ፍቅር ሲል በቤተልሔም ውስጥ በደሳሳ የከብቶች በረት ውስጥ መወለዱን ለማየት ፈልጓል። በእርግጥ የቅዱስ ፍራንችስኮስ የሕይወት ታሪክ ጸሐፊ እንደሚናገረው፥ በዚያ አስደናቂ ትእይንት አማካይነት ወንጌላዊ ትህትናው ጎልቶ ይታያል። ድህነት ተወድሷል፣ ትህትናም ታይቷል። የግሬቾ አካባቢ እንደ አዲስ ቤተልሔም ሆናለች” ሲል ይገልጻል።
ይህ የብርሃነ ልደቱ ትዕይንት እንደ የትህትና ትምህርት ቤት የታየበት የመጀመሪያው ባህሪ ነው። ታሪኩ ለእኛ የሚነግረን ትልቅ መልዕክት አለው። ዛሬ በሕይወት መካከል ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የማጣት አደጋ በብርሃነ ልደቱ በዓል ወቅት በግልጽ እየጨመረ መጥቷል። የብርሃነ ልደቱን ትርጉም በሚያበላሽ ከፍተኛ የፍጆታ ባሕል ውስጥ ገብተናል። ትኩረትን በሚከፋፍሉ የማስታወቂያ ማዕበል ተውጠናል፥ የማይጠቅሙንን ነገሮች ችላ ያለ ማለት አደጋ ውስጥ እንገባለን። ኢየሱስ ክርስቶስ በድህነት ውስጥ ራሱን እንደ ስጦታ ሊሰጠን ሲመጣ፥ በዓሉ ለብዙዎች ስጦታን የሚለዋወጡበት አጋጣሚ ይሆናል። ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን በተመለከተ፥ ለእምነት ከፍተኛ እንቅፋት የሚሆን ፈተና ይህ ነው፥ “ነገር ግን ልባችሁ በመጠጥ ብዛት እና በስካር፥ ስለ ኑሮም በማሰብ እንዳይዝል፥ ያ ቀንም በድንገት እንዳይመጣባችሁ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ” (ሉቃ. 21፡34)። የልብ መበታተን ወደ ዓለማዊ ሁካታ ውስጥ በማስገባት ነፍስን ያደነዝዛል።
ስለዚህ የብርሃነ ልደቱ ትዕይንት የተዘጋጀው እኛን ወደ አስፈላጊው ነገር ለመመለስ ነው። በመካከላችን ሊኖር ወደሚመጣው እግዚአብሔር እንድንመለስ፥ እንዲሁም ከሌሎችም ጋር መልካም ግንኙነት እንዲኖረን፣ በኢየሱስ ክርስቶስ፣ በቅዱስ ዮሴፍ እና በእመቤታችን ቅድስት ማርያም የተገለጸውን የተቀደሰ ቤተሰብ ምሳሌን በመከተል፥ ከምንወዳቸው እና በእረኞች ከሚመሰሉ ሰዎች ጋር መልካም ግንኙነት እንዲኖረን ያሳስበናል። ከሁሉ በፊት ሰዎችን እንደማንነታቸው መቀበል እንደሚገባ፥ በብርሃነ ልደቱ ትዕይንት ውስጥ የሚታዩ ገጸ-ባህሪያት ትሁትና፣ ድሆች መሆናቸውን እና ከፍጥረት ጋር ተስማምተው መኖራቸውን እናስተውላለን። የብርሃነ ልደቱ ትዕይንት ገጠራማ አካባቢን በስፋት ያሳያል። በትዕይንቱ ውስጥ በሬ እና አህያ አሉበት። ወደ አስፈላጊ ነገር በመመለስ ሕይወታችንን ለማስተካከል ትዕይንቱን በጽሞና መመልከቱ መልካም ነው። ከዕለታዊ እንቅስቃሴ ተለይተን በጸሎት እና በጸጥታ መንፈስ ርህራሄን እና ሰላምን ለማግኘት ጸጥ ወዳለበት ሥፍራ የመሄድ ያህል ነው። ከምናባዊ እና ከአመጽ ምስሎች የተናሳ የምግብ አለመፈጨት ችግር የሚጋለጡ ሕፃናት እና ወጣቶችን እንዳሉ አስባለሁ። ሕጻናት እና ወጣቶች በኢየሱስ ክርስቶስ የልደት ትዕይንት ውስጥ እውነተኛነትን እና ብልሃትን ማግኘት ይችላሉ። ከአያቶቻቸው ጋር በመሆን አንዳቸው ለሌላው መልካምን ሲያደርጉ መመልከት ምንኛ ያስደስታል!
ጣሊያን ውስጥ ግሬቾ በተባለ አካባቢ ተዘጋጅቶ የነበረው የብርሃነ ልደቱ ትዕይንት የሚናገረው ስለ ትህትና ብቻ ሳይሆን ስለ ደስታም ጭምር ነው። በዘመኑ የተነገረውን ዜና እንመልከት፡- “የደስታም ቀን ይመጣል፣ የሐሴት ጊዜም ይሆናል! ቅዱስ ፍራንችስኮስ ደምቋል። ሕዝቡም ደስ ብሎት እየጎረፈ ከዚህ በፊት ቀምሶ በማያውቀው ደስታ ውስጥ ይገኛል። ሁሉም ሰው ሊገለጽ በማይችል ደስታ ተሞልቶ ወደ ቤቱ ተመለሰ” ይላል።
ያ ያልተለመደ የብርሃነ ልደቱ ደስታ ከየት የመጣ ነው? በእርግጠኝነት ስጦታዎችን ከመለዋወጥ ወይም አስደሳች የዓላት ጊዜን በማሳለፍ አይደለም። አንድ ሰው የኢየሱስ ክርስቶስን መምጣት፣ የእግዚአብሔርን ርኅራኄ በተጨባጭ ሲረዳ፣ ብቻችንን የማይተወን የሚያጽናናን ከልብ የመነጨ ደስታ ነበር። የብርሃነ ልደቱ ትዕይንት ልምድ ነው። በዚህ ትዕይንት አማካይነት የእግዚአብሔርን ቅርበት በተጨባጭ መንገድ መገንዘብ እንችላለን። እንደ እውነቱ ከሆነ ዕለታዊ የኑሮ ሁኔታም ተገልጿል። እረኞች እና ሌሎች የሥራ ዓይነቶችም ታይተዋል። በሄሮድስ ቤተ መንግሥት የተመሰለው ክፋትም አለበት፤ የዓለም ውበት እና መከራም በውስቱ አለበት። ሁሉም ነገር በአዲስነት የሚታይበት፣ እግዚአብሔር በመካከላችን በመሆን ህልውናችንን የሚቀበልበት ሁኔታም ይታያል።
ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ! የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ትዕይንት የተስፋ እና የደስታ ምንጭ የሆነውን የእግዚአብሔር ወደ እኛ መቅረብ ማወቅ የምንችልበት ትዕይንት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተነገርው የውኃ ጉድጓድ፣ የቤተልሔም እረኞች እና የግሬቾ አካባቢ ሰዎች እንዳደረጉት ሁሉ፥ የሕይወት ተስፋ እና ጭንቀት ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ የምናመጣበት ቦታ ነው። ከኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ትዕይንት አስቀድመን የምንወደውን ነገር ሁሉ ለኢየሱስ ክርስቶስ በአደራ ከሰጠነው እኛም ታላቅ ደስታን እናገኛለን (ማቴ 2፡10)።”