ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ኮንራድን በቤተልሔም በሚገኝ የሕጻናት ማሳደጊያ ውስጥ ብጹዕ ካርዲናል ኮንራድን በቤተልሔም በሚገኝ የሕጻናት ማሳደጊያ ውስጥ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ብጹዕ ካርዲናል ኮንራድን ወደ ቅድስት ሀገር መላካቸው ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በቅድስት መንበር የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የበጎ አድራጎት ሥራ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ኮንራድ ክራየቪስኪን ወደ ቅድስት ሀገር ልከዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው ብጹዕ ካርዲናል ኮንራድን ወደ ቅድስት አገር የላኩት በዚህ ወቅት በአካባቢው እየተካሄደ ያለው ጦርነት ባስከተለው መከራ ውስጥ ከሚገኘው ሕዝብ ጋር ያላቸውን አጋርነት ለመግለጽ እንደሆነ ታውቋል። ቅዱስነታቸው ከዚህም ጋር ሁሉም ሰው ስለ ሰላም እንዲጸልይ አደራ ብለዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ኮንራድ ክራየቭስኪ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ተልዕኮ ተቀብለው በብርሃነ ልደቱ ወቅት በቅድስት አገር ከሚገኙ ሕዝቦች ጋር ለመሆን ወደ ሥፍራው መጓዛቸውን፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የበጎ አድራጎት ሥራ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ዓርብ ታኅሳስ 12/2016 ዓ. ም. በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።

የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የአጋርነት መግለጫ ምልክት 

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የበጎ አድራጎት ሥራ አስተባባሪ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ኮንራድ  የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን አጋርነት ለመግለጽ ግጭቶች እና ጦርነቶች ያሉባቸውን አካባቢዎች በተደጋጋሚ ጎብኝተው እንደ ነበር ይታወሳል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የካቲት ወር 2022 ዓ. ም. ሩስያ ዩክሬንን በወረረችበት ወቅት በዩክሬን በመከራ ውስጥ ለሚገኙት ሕዝቦች ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የላኩት ሰብዓዊ ዕርዳታዎችን ለማድረስ በተከታታይ ወደ ዩክሬን መጓዛቸው ይታወሳል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በዓለማችን ውስጥ ሕዝቦችን እያስጨነቀ የሚገኝ “ሦስተኛው የዓለም ጦርነት” ያሉት እንዲቆም በማለት በየዕለቱ ለሰላም በመጸለይ፥ ምድሪቱን የሚጎዱ ግጭቶች እንዲቆሙ፥ በተለይም በዩክሬን፣ በሶርያ፣ በብዙ የአፍሪካ አገሮች እና አሁን በእስራኤል እና በፍልስጤም መካከል በመካሄድ ላይ ያለው ጦርነት እንዲቆም ጥሪ ማድረጋቸውን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የበጎ አድራጎት ሥራ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት መግለጫ አስታውቋል።

በዚህ መሠረት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ጦርነት የሚያስከትለውን መዘዝ እየተጋፈጡ የሚገኙ ሰዎች መከራን በተጨባች የሚካፈሉ መሆናቸውን ለመግለጽ፥ በቫቲካን የበጎ አድራጎት ሥራ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ የሆኑትን ብጹዕ ካርዲናል ኮንራድ ክራየቪስኪን ወደ ቅድስት ሀገር ለመላክ መወሰናቸው ታውቋል።

የር. ሊ. ጳ. የበጎ አድራጎት ሥራ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ብጹዕ ካርዲናል ኮንራድ ክራየቪስኪ
የር. ሊ. ጳ. የበጎ አድራጎት ሥራ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ብጹዕ ካርዲናል ኮንራድ ክራየቪስኪ

የብርሃነ ልደቱን በዓል በጦርነት ውስጥ የምታሳልፍ ሀገር

ብጹዕ ካርዲናል ኮንራድ ክራየቪስኪ የብርሃነ ልደቱን በዓል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደባ ቅድስት አገር ውስጥ ከአካባቢው ክርስቲያን ማኅበርሰብ ጋር እንደሚያሳልፉ ታውቋል። ብፁዕ ካርዲናል ኮንራድ ይህን ታላቅ የሰላም ጥሪ ለመቀላቀል፥ የሰላም አለቃ እና የዓለማችን ብቸኛ ተስፋ የሆነውን የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት በኅብረት ለማክበር በኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ከሆኑት ከብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ እና ከመላው የአካባቢው ክርስቲያን ማኅበረሰብ ጋር ይህን ታላቅ የሰላም ጥሪ የሚቀላቀሉት መሆናቸውን መግለጫው አስታውቋል። መግለጫው አክሎም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “የጦር መሣሪያ ከባድ ጥቃቶችን ማድረስ በቀጠለባቸው አካባቢዎች የሰላም ስጦታን ለማግኘት ሁሉም ሰው የካርዲናሉን ጉዞ በጸሎት እንዲተባበር ጋብዘዋል።

“ዳግም ጦርነት አይካሄድ!” የማለት ድፍረት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከእስራኤሉ ፕሬዝዳንት ሺሞን ፔሬዝ እና ከፍልስጤሙ ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ ጋር እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ሰኔ 8 ቀን 2014 ዓ. ም. በቫቲካን የአትክልት ሥፍራ ተገናኝተው በኅብረት መጸለያቸውን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የበጎ አድራጎት ሥራ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት በመግለጫው አስታውሷል። የበጎ አድራጎት ሥራ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቱ፥  በእስራኤል እና በሃማስ መካከል ጦርነት እየታካሄደ ባለበት ዛሬም ጸሎቱ ጠቃሚ እንደሆነ በማስታወስ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በወቅቱ ያቀረቡት የሚከተለውን ጸሎት በመድገም መግለጫው አጥናቅቋል፥

“አሁን ጌታ ሆይ ድረስልን! ሰላምን ስጠን፤ ሰላምን አስተምረን፤ ወደ በሰላም ጎዳና ምራን። ዓይኖቻችንን እና ልባችንን ክፈትህ ዳግም ወደ ጦርነት እንዳንመለስ ለመወሰን ድፍረትን ይስጡን። 'ዳግመኛ ጦርነት አታድርግ!'; "በጦርነት ሁሉ ይጠፋል። ሰላምን ለማምጣት የሚያግዙ ተጨባጭ እርምጃዎችን እንድንወስድ ድፍረትን ስጠን። መከፋፈል፣ ጥላቻ እና ጦርነት የሚሉት ቃላት ከእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ ይወገዱ። ጌታ ሆይ የምላሳችንንና የእጃችንን ግፍ አርቅልን። ልባችንን እና አእምሮአችንን በማደስ ወደ አንድነት የሚያደርሰንን ወንድማማችነት እና የሕይወታችን አካሄድ ዘወትር የሰላም እንዲሆን አድርግልን።”

23 December 2023, 14:19