ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የሃይማኖት መሪዎች በሰላምና በአየር ንብረት ጉዳይ ላይ እንዲተባበሩ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፥ በዱባይ ከተማ ከኅዳር 20 እስከ ታህሳስ 2/2016 ዓ. ም. ድረስ በመካሄድ ላይ ባለው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP28) ላይ ለተገኙት የሃይማኖት መሪዎች መልዕክት ልከዋል። እሑድ ኅዳር 23/2016 ዓ. ም. በላኩት የቪዲዮ መልዕክታቸው፥ የዓለም የሃይማኖት መሪዎች ለፍጥረታት በሚደረግ እንክብካቤ እና የሰላም ጥረቶችን የሚያበረታታ ኅብረት እንዲኖራቸው አደራ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በዱባይ ከተማ በመካሄድ ላይ በሚገኘው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP28) ለሃይማኖት መሪዎች በተዘጋጀው መድረክ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት የላኩት መልዕክት ዋና ጭብጥ፥ የሃይማኖት መሪዎቹ ለጋራ ጥቅም በሚያደረጓቸው ጥረቶች ላይ ኅብረትን እንዲፈጥሩ የሚያሳስብ እንደ ሆነ ተመልክቷል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በዱባይ ከተማ በመካሄድ ላይ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP28) ላይ መገኘት ያልቻሉት ባጋጠማቸው የጉንፋን ሕመም ምክንያት እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፥ መልዕክታቸውን ለጉባኤው ያደረሱት እርሳቸውን ወክለው ጉባኤውን በመካፈል ላይ የሚገኙት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን እንደሆኑ ታውቋል።

ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀ መድረክ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጉባኤው ላይ ባለመገኘታቸው የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸው፥ በማከልም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በዚህ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በሃይማኖት ተቋማት ስም ለመጀመሪያ ጊዜ ድንኳን ማዘጋጀቱንም አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። “መድረኩ በጋራ ለመሥራት ፈቃደኛ መሆናችንን ይመሰክራል” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ዛሬ ዓለም ከማንም ጋር የማይቃረን ነገር ግን ሁሉንም የሚደግፍ ጥምረት ያስፈልጋታል” ሲሉ ተናግረዋል። “አብሮ መሥራት ለራስ ብቻ ወይም ለአንድ ወገን ጥቅም ሳይሆን ለዓለማችን ጥቅም ነው” ብለዋል።

ምስክርነትን መስጠት

በመሆኑም ሁሉም የሃይማኖት ተቁማት ተወካዮች ኅብረታቸውን በማጠናከር፣ ዘላቂ እና የተከበረ ሕይወት ዘይቤዎችን በመመሥከር እና መልካም አርአያ በመሆን ለውጥ ማምጣት የሚቻል መሆኑን በተጨባጭ እንዲያሳዩ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋብዘዋል።

"የአገራት መሪዎች የጋራ መኖሪያ ምድራችንን ከጉዳት እንዲጠብቁ አጥብቀን እናሳስባለን" ብለው፥ “በመካከላችን የሚገኙ ድሆች እና አቅመ ደካሞች ጸሎታቸውን ወደ ልዑል እግዚአብሔር ዙፋን በማቅረብ ላይ እንደሚገኙ እና ጩኸታቸውንም በማሰማት ላይ ይገኛሉ” ብለዋል። በመልዕክታቸው ማጠቃለያም፥ ሁሉም ሰው ፍጥረትን ከጉዳት እንዲጠብቅ እና የጋራ መኖሪያ ምድራችንን እንዲንከባከብ እና ዘወትር በሰላም ለመኖር ጥረት እንዲያደርግ አደራ ብለዋል።

የተዋሃደ እምነት መግለጫ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ፥ በዱባይ ከተማ ከኅዳር 20 እስከ ታህሳስ 2/2016 ዓ. ም. ድረስ በመካሄድ ላይ ባለው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP28) ላይ፥ በሃይማኖት ተቋማት ስም ለመጀመሪያ ጊዜ በተዘጋጀው የድንኳን የምረቃ ሥነ ሥር ዓት ላይ የተገኙትን የሃይማኖት መሪዎች እና የብዙ እምነት ተወካዮችን በመቀላቀል የጋራ መግለጫ ሠነድን ፈርመዋል። መግለጫው በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ዓለም አቀፍ ፍትህን ለማስፈን የእምነት ማህኅረሰቦችን እና የሃይማኖት ተቋማት የሚፈጥሩትን የጋራ ተጽእኖ ለመጠቀም የሚፈልግ መሆኑ ታውቋል።

 

05 December 2023, 16:25