የሕይወት ፈተና ለማሸነፍ “የእምነታችን ጀማሪና ፍጹም አድራጊ የሆነውን ኢየሱስን መመልከት” ይኖርብናል
የእስጢፋኖስ መያዝ
በዚህ ጊዜ እስጢፋኖስ ጸጋንና ኀይልን ተሞልቶ በሕዝቡ መካከል ድንቅ ነገሮችንና ታምራዊ ምልክቶችን ያደርግ ነበር። “የነጻ ወጪዎች ምኵራብ” ተብሎ የሚጠራው ምኵራብ አባላት የሆኑ ከቀሬናና ከእስክንድርያ፣ እንዲሁም ከኪልቅያና ከእስያ አውራጃዎች የመጡ ሰዎችም ተቃውሞ አስነሥተው እስጢፋኖስን ይከራከሩት ጀመር፤ ይሁን እንጂ ይናገርበት የነበረውን ጥበብና መንፈስ መቋቋም አልቻሉም።
በዚህ ሁኔታ ሕዝቡን፣ የአገር ሽማግሌዎቹንና የሕግ መምህራኑን በማነሣሣት፣ እስጢፋኖስን አስይዘው በአይሁድ ሸንጎ ፊት አቀረቡት።
የእስጢፋኖስ መወገር
በሸንጎው ስብሰባ ላይ የነበሩትም ይህን በሰሙ ጊዜ እጅግ ተቈጡ፤ ጥርሳቸውንም አፏጩበት። እስጢፋኖስ ግን በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ወደ ሰማይ ትኵር ብሎ ሲመለከት፣ የእግዚአብሔርን ክብር እንዲሁም ኢየሱስ በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየና፣ “እነሆ፤ ሰማያት ተከፍተው፣ የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ” አለ።
በዚህ ጊዜ በታላቅ ድምፅ እየጮኹ ጆሯቸውን ደፍነው እርሱ ወደ አለበት በአንድነት ሮጡ፤ ይዘውም ከከተማው ውጭ ጣሉት፤ በድንጋይም ይወግሩት ጀመር። ይህ በሚሆንበት ጊዜ በዚያ የነበሩ ምስክሮችም ልብሳቸውን ሳውል በተባለ ጕልማሳ እግር አጠገብ አስቀመጡ።
እስጢፋኖስም እየወገሩት ሳለ፣ “ጌታ ኢየሱስ ሆይ፤ ነፍሴን ተቀበላት፤” ብሎ ጸለየ፤ ከዚያም ተንበርክኮ በታላቅ ድምፅ፣ “ጌታ ሆይ፤ ይህን ኀጢአት አትቍጠርባቸው!” ብሎ ጮኸ፤ ይህን ካለ በኋላም አንቀላፋ (የሐዋርያት ሥራ 6፡ 8-15፣ 7፡54-60)
ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!
የመጀመሪያው ሰማዕት የቅዱስ እስጢፋኖስ በዓል ዛሬ ይከበራል። የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ከምዕራፍ (6-7) ውስጥ ስለሱ የሚያወሳ ሲሆን እናም በዛሬው የስረዓተ አምልኮ በእርሱ ማለትም በቅዱስ እስጢፋኖስ በሕይወቱ የመጨረሻ ቀናት ውስጥ የገጠመውን ስቃይ እና መወገር ለእኛ ገልጦልናል (የሐዋ. 6,12; 7,54- 60 ይመልከቱ)። በገና በዓል አስደሳች ወቅት ለእምነቱ የተገደለው የመጀመሪያው ክርስቲያን መታሰቢያ በዓል ብቅ ማለቱ ያለቦታው የተከሰተ በዓል ሊመስል ይችል ይሆናል። ሆኖም በትክክል በእምነት እይታ፣ የዛሬው በዓል ከገና ትክክለኛ ትርጉም ጋር የሚስማማ ነው። በቅዱስ እስጢፋኖስ ሰማዕትነት፣ በእውነቱ አመጽ በፍቅር ፣ በሞት በህይወት መሸነፉን ያሳያል፣ እርሱ በታላቅ ስቃይ ውስጥ እምነቱን በመሰከረበት ወቅት የተከፈተ ሰማይ ይመለከታል፣ ለአሳዳጆቹም ይቅርታ ያደርግላቸዋል።
በመንፈስ ቅዱስ የተሞላው ይህ ወጣት የወንጌል አገልጋይ ኢየሱስን በቃላት እና ከሁሉም በላይ በሕይወቱ ውስጥ ለመተረክ ችሏል። የእርሱን ሕይወት ስንመለከት “በምትያዙበትም ጊዜ ምን እንናገራለን፣ ምንስ እንመልሳለን ብላችሁ አትጨነቁ፤ በዚያን ጊዜ የምትናገሩት ይሰጣችኋል፤ በእናንተ የሚናገረው የሰማዩ አባታችሁ መንፈስ እንጂ እናንተ አይደላችሁምና” (ማቴ 10፡19-20) በማለት ኢየሱስ ለደቀመዛሙርቱ የሰጠው ተስፋ ሲፈጸም እናያለን። በሕይወትም ሆነ በሞቱ ውስጥ ከጌታው ጋር በተመሳሰለ የቅዱስ እስጢፋኖስ አስተምህሮ ውስጥ፣ እኛም በአብ የታመነ እውነተኛ የኢየሱስ ምስክርነት ላይ ማተኮር እንደ ሚገባን እንማራለን። ለዘለአለም ህይወት እና ለሰማይ ክብር የሚያበቃን ሀብት እና ስልጣን ሳይሆን ነገር ግን ፍቅር እና ራስን በመስጠት እንደ ሆነ እንማራለን።
በእለታዊ ሕይወታችን ውስጥ የሚያግጥሙን ፈተናዎች እና ተግዳሮቶች በተገቢው ሁኔታ ለመጋፈጥ እና በተስፋ የተሞላ ምላሽ ለመስጠት ያስችለን ዘንድ ትኩረታችንን “የእምነታችን ጀማሪና ፍጹም አድራጊ የሆነውን ኢየሱስን መመልከት” (ዕብ 12፡2) ይገባናል። ለእኛ ክርስቲያኖች ፣ ሰማይ ከእንግዲህ ወዲህ ከምድር እጅግ የተለየ ሩቅ አይደለም፣ በኢየሱስ አማካይነት ሰማይ ወደ ምድር ወረደ። ለእርሱ ምስጋና ይግባውና በመንፈስ ቅዱስ ኃይል መላውን የሰው ልጅ መገናኘት እና ወደ መንግስተ ሰማይ መምራት እንችላለን። የመጀመሪያው ምስክርነት ትክክለኛ ሰው የመሆን ባሕሪይ ሲሆን በኢየሱስ መሠረቱን ያደረገ የአኗኗር ዘይቤ የሆኑትን ገርነት እና ብርታት፣ ትሑት እና ክቡር ፣ ዓመፀኛ ያልሆነ ነገር ግን ጠንካራ ባሕሪይ መላበስ ይኖርብናል።
እስጢፋኖስ ከቤተክርስቲያኗ የመጀመሪያዎቹ ሰባት ዲያቆናት መካከል አንዱ ነበር (ሐዋ. 6: 1-6)። እርሱ በወንድማማችነት መንፈስ እና በቅዱስ ወንጌል የተቀባ ፍቅር አማካይነት ክርስቶስን እንድናውጅ አስተምሮናል። የእርሱ ምስክርነት በሰማዕትነት የሚጠናቅቅ ሲሆን፣ ለእኛ የክርስቲያን ማህበረሰባች እድሳት የመነሻ ምንጭ ነው። እነሱ የበለጠ የወንጌል ተልዕኮ እንዲያፋፍሙ የተጠሩ ሲሆን ሁሉም ቅዱስ ወንጌልን ለማብሰር የሚጥሩ በየተኛውም የመልካምድር አቀማመጥ ውስጥ ለሚገኙትን ሰዎች ቅዱስ ወንጌልን ለማዳረስ እና የመዳን ጥማት ያላቸውን ሰዎች ጥም ለማርካት ተጠርተዋል። ዓለማዊ አመክንዮን የማይከተሉ ማህበረሰቦች ራሳቸውን ማዕከል ያላደረጉ፣ የራሳቸውን ምስል የማይከተሉ ሲሆን ነገር ግን ለየት ባለ መልኩ የእግዚአብሔር ክብር እና የሰዎችን መልካምነት፣ በተለይም አቅመ ደካማ እና ድሃ ለሆኑ ሰዎች ትኩረት ይሰጣሉ።
የመጀመሪያው ሰማዕት የቅዱስ እስጢፋኖስ በዓል ትናንት እና ዛሬ ያሉትን ሰማዕታት ሁሉ እንድናስታውስ ፣ ከእነሱ ጋር ህብረት እንዳለን እንዲሰማን፣ በልባችን እና በከንፈሮቻችን የኢየሱስን ስም በማኖር እንድንኖር ኣና እንድንሞት ጸጋ እንዲያሰጡን ልንማጸናቸው የገባል። የአዳኙ እናት የሆነቺው ማርያም እይታችንን በኢየሱስ ላይ በማደረግ በየቀኑ ከእርሱ ጋር የተመሳሰለ ሕይወት በዚህ የገና ወቅት እንድንኖር እንድትረዳን ልንማጸናት የገባል።
ምንጭ፡ የቅዱስ እስጢፋኖስ ዓመታዊ በዓል በታኅሳስ 16/2012 ዓ.ም. በተከበረበት ወቅት በወቅቱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ካደረጉት አስተንትኖ የተወሰደ።
አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን