ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “በፈተና ጊዜ ዘወትር የኢየሱስ ክርስቶስን ዕርዳታ መለመን ይገባል!” አሉ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ! የዛሬው ቅዱስ ወንጌል ኢየሱስ ክርስቶስ ርኩስ መንፈስ ያደረበትን ሰው ነፃ እንዳወጣው ይነግረናል (ማር. 1: 21-28)። ርኩሱም መንፈስ ሰውየውን በኃይል ካንፈራገጠው በኋላ እየጮኸ ከእርሱ ወጣ (ማር. 1: 23 እና 26)። የክፉ መንፈስ ወይም የዲያብሎስ ሥራ ይህ ነው። ነፍሳችንን በቁጥጥሩ በማድረግ ሊያስራት ይፈልጋል። ዲያብሎስ የሚፈልገው ይህንን ነው። ነፃነታችንን ከሚነጥ ወይም ከሚያፍን የዲያቢሎስ ሰንሰለቶች መጠንቀቅ አለብን። ልባችንን ሊያስሩ የሚችሉ አንዳንድ ሰንሰለቶችን ለመጥቀስ እንሞክር።
የእርሱ ተገዥዎች የሚያደርገን እና እርካታ የሌለው፣ ጉልበታችንን፣ ንብረታችንን እና ከሰዎች ጋር ያለንን ግንኝነት የሚነጥቅ፣ ሱስ የተባለ የሕይወታችን ጠንቅ መኖሩን እገነዘባለሁ። ሌላው እና ሁለተኛው የነፍሳችን ሰንሰለት ባሁኑ ጊዜ የገነነው፥ የማይቻል ፍጽምነትን የሚያበረታታ፣ ወደ ከፍተኛ የፍጆታ ስሜት የሚገፋፋ፣ የሕይወታችን ግብ ደስታ ብቻ እንደሆነ የሚነግረን ሰንሰለት ነው። ሌሎች ተጨማሪ ሰንሰለቶችም፥ በራስ መተማመንን የሚሸረሽሩ፣ ሰላማዊነትን የሚያበላሹ፣ ሕይወትን የመምረጥ እና የመውደድ ችሎታን የሚያሳንሱ ፈተናዎች እና ሁኔታዎችም አሉ።
ሌላው ሰንሰለት ፍርሃት ነው። ፍርሃት ተስፋን በማስቆረጥ እርካታ ቢሶች እና ሁል ጊዜ ሌሎችን ወቃሾች እንድንሆን የሚያደርግ ነው። ሌላው አስቀያሚ ሰንሰለት አለ። እሱም ስልጣንን ማምለክ ነው። ይህ ሰንሰለት በሰዎች መካከል ግጭቶችን የሚፈጥር፥ ኢኮኖሚያዊ ኢ-ፍትሃዊነትን እና የሚያታልሉ አስተሳሰቦችን በማቅረብ እና እንዲሁም በጦርነት የሰው ሕይወት እንዲጠፋ እና ንብረትም እንዲወድም የሚያደርግ ነው። ሰንሰለቶቻችን ብዙዎች ናቸው። በሕይወታችን ውስጥ በእውነት ብዙ ሰንሰለቶች አሉ።
እንግዲህ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዓለም የመጣው ከእነዚህ ሰንሰለቶች ነፃ ሊያወጣን ነው። ዛሬ ኢየሱስ ክርስቶስን "የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ! አንተ ከእኛ ጋር ምን አለህ ልታጠፋን መጣህ?" እያለ በመጮኽ ከሚገዳደር ሰይጣን ጋር ግጥሚያ ይዘናል (ማር. 1:24)። ኢየሱስም መልሶ፥ ‘ዝም በል ከእርሱ ውጣ!’ አለው (ማር. 1:25)። ኢየሱስ ክርስቶስ ክፉ መንፈስን የማስወጣት ኃይል አለው። ኢየሱስ ክርስቶስ ከክፉው መንፈስ ነፃ ያወጣናል። ኢየሱስ ክርስቶስ ክፉው መንፈስን ሲያስወጣ ከእሱ ጋር ፈጽሞ የማይደራደር መሆኑን ልብ ልንል ይገባል። በምድረ በዳ በተፈተነ ጊዜም ኢየሱስ ክርስቶስ ከዲያብሎስ ጋር ፈጽሞ አልተደራደረም። ምላሾቹ ከሰይጣን ጋር ምንም ዓይነት ድርድር እንደማይፈልግ የሚገልጹ እና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥም የተጠቀሱ ናቸው። ወንድሞቼ እና እህቶቼ ሆይ! ከዲያብሎስ ጋር ምንም ዓይነት ውይይት ሊኖር አይገባም! ከእርሱ ጋር ማውራት ከጀመራችሁ ሁልጊዜ ስለምትሸነፉ መጠንቀቅ ያስፈልጋል።
እንግዲያው ፈተና ሲያጋጠመን እና ግፍ ሲሰማን ምን ማድረግ አለብን? ከዲያብሎስ ጋር መደራደር አለብን? የለም! ከእርሱ ጋር መደራደር የለብንም። ኢየሱስ ክርስቶስን ልንጣራው ይገባል። የክፋት እና የፍርሃት ሰንሰለቶች ኃይለኛ በሚሆኑብን ቦታዎች የኢየሱስ ክርስቶስን ዕርዳታ እንለምን።
ዛሬም ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈሱ ኃይል ለክፉው መንፈስ ሊናገር ይፈልጋል፡- ‘ከዚህ ሂድ! ያንን ልብ በሰላም ተወው! ዓለምን፥ ቤተሰቦቻችንን እና ማህበረሰባችንንም አትከፋፍል! የመንፈሴ ፍሬ እንዲያብብ እንጂ ያንተ ማበብ የለበትም።’ ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረው ይህን ነው። በመካከላቸው ፍቅር፣ ደስታ እና የዋህነት ይንገሥ፤ ከዓመፅ እና ከጥላቻ ይልቅ ነፃነት እና ሰላም ይስፈን።
‘ልቤን ከሚያስሩ ሰንሰለቶች መላቀቅ እፈልጋለሁ? የሰይጣን ፈተናዎች ወደ ነፍሴ ከመግባታቸው በፊት አይ! ብዬ መቃወም እችላለሁን? በመጨረሻም ኢየሱስ ክርስቶስ በእኔ ውስጥ እንዲሠራ በመፍቀድ የእርሱን ፈውስ እለምናለሁ?’ በማለት ራሳችንን እንጠይቅ። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘወትር ከክፉ ነገር ትጠብቀን።”