ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የማልታ ሉዓላዊ ሠራዊት ማኅበር በሰብዓዊነት ዲፕሎማሲው እንዲቀጥል አበረታቱ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
"ሥራችሁ ሰብዓዊ ዕርዳን ማድረግ ብቻ አይደለም” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ማኅበሩ በሌሎች በርካታ ተቋማትም መልካም አገልግሎት በማበርከት ላይ እንደሚገኝ አስታውሰው፥ ደካሞችን በማገልገል የእግዚአብሔር ስም የሚከብርበት እና እግዚአብሔር ለእነርሱ ያላቸውን ፍቅር የሚመሰክሩበት መሆኑን ቅዳሜ ጥር 18/2016 ዓ. ም. በቫቲካን በተቀበሏቸው ወቅት በሰጡት ማሳሰቢያ ገልጸዋል።
እምነትን ከአደጋ መከላከል እና ድሆችን ማገልገል አይነጣጠሉም
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ለማልታ ሉዓላዊ ሠራዊት ማኅበር አምባሳደሮች ባሰሙት ንግግር፥ እምነትን የመጠበቅ እና ድሆችን የማገልገል ተልዕኮ የማይነጣጠሉ መሆናቸው በሕጋዊ ቻርታቸው ላይ መጠቀሱን አስረድተዋል። በማቴ. 26 ላይ እንደተጠቀሰው በቢታንያ ማርያም የምትባል ሴት የኢየሱስ ክርስቶስን እግር ሽቶ እንደቀባች የሚገልጸውን የወንጌል ክፍል በማስታወስ፥ ማኅበሩ ድሆችን በሚያገለግሉበት ወቅት ኢየሱስን የሚያገለግሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
“በዓለም ዙሪያ ማኅበሩ የሚያከናውኗቸው ዲፕሎማሲያዊ ተግባራት በዚህ መንገድ መታየት አለባቸው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ይህም ማኅበራቸውን በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኝ የምዕመናን ማኅበር እንዲሆን ከማድረጉ በተጨማሪ በዓለም አቀፍ ሕግ የሚገዛ ሉዓላዊ መንግሥትም ነው ብለዋል። በዚህ መካከል ሁለት የተለያዩ እውነታዎች ሊኖሩ እንደማይችሉ የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ የማልታ ሉዓላዊ ሠራዊት ማኅበር ለዓለም አቀፍ ሕግ በመገዛት ለበጎ አድራጎት ሥራዎች የቆመ ሃይማኖት ተቋም መሆኑን አስረድተዋል።
ለቅድስት መንበር የሚገዛ ሉዓላዊ መንግሥት እና ሃይማኖታዊ ማኅበር
የማልታ ሉዓላዊ ሠራዊት ማኅበር እንደ ሃይማኖታዊ ማኅበር በታላቁ ሊቃውንት በኩል ለቅድስት መንበር እና ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የሚታዘዝ መሆኑን አስታውሰው፥ ማኅበሩ በተወካዮቻቸው አማካይነት የሚያሳዩት ፍሬያማ ትብብር ለቤተ ክርስቲያን እና ለኅብረተሰቡ የሚቀርብ ጠቃሚ የጋራ ተግባር እንደሆነ አስረድተዋል።
የማልታ ሉዓላዊ ሠራዊት ማኅበር ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ያለው ግንኙነት ነፃነቱን እንደማይገድብ የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ነገር ግን በቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ በሆኑት በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በኩል የሚደረግለት ጥበቃ ጥቅሙን የበለጠ የሚያረጋግጥ እና ከዚህ በፊት እንደተከሰተው ሁሉ በአስቸጋሪ ወቅት በቀጥታ ቶሎ ጣልቃ መግባትን የሚያሳይ ነው” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ፥ ማኅበሩ ድሆችን በማገልገል ላሳየዉ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት አመስግነው፥ በቅድስት መንበር ሥር በመሆን የሚያካሂደውን አገልግሎት መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል። “ይህ ጥገኝነት የዲፕሎማሲ ውክልና አስፈላጊነትን እንደማይቀንስ፥ ይልቁን ማንነታቸውን የበለጠ ለመረዳት እንደሚያስችል፥ በተለይ ከፍተኛ የእርዳታ ፍላጎት በሚታይባቸው ዘርፎች የማኅበሩ ሐዋርያዊ እና የበጎ አድራጎት ተግባር ለሁሉም ክፍት እና ለጋስ እንዲሆን ያግዛል” ብለዋል።
"ይህ ልዩ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴአችሁ ጠቀሜታውን ሳይቀንስ፥ ለተጋላጭ ሕዝቦች ተጨባጭ እገዛን በማድረግ፥ ውድ ምስክርነት እና አስደናቂ ምልክት የሚሰጥ ነው” በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቅዳሜ ጥር 18/2016 ዓ. ም. ለማልታ ሉዓላዊ ሠራዊት ማኅበር አምባሳደሮች ያስተላለፉትን መልዕክት ደምድመዋል።