ፈልግ

የፍልስጤም እና የእስራኤል ጦርነት የፍልስጤም እና የእስራኤል ጦርነት  (AFP or licensors)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “ጦርነት በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸም ወንጀል ነው” አሉ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ ጥር 5/2016 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለጸሎት ለተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች ካሰሙት ቃለ ምዕዳን በመቀጠል ንግግር አድርገዋል። ቅዱስነታቸው በንግግራቸው፥ ሁሉንም ዓይነት ጦርነቶች በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች እንደሆኑ ገልጸው፥ የሰው ልጅም ዓመፅን በማይቀበል ትምህርት በመታነጽ ሰላምን መፈለግ እንዳለበት አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ጦርነት በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸም ወንጀል ነው፤ ሕዝብ እና መላው ዓለም ሰላም ያስፈልገዋል፤ ጦርነት መቆም አለበት በማለት እሑድ ጥር 5/2016 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር ሆነው የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ካቀረቡ በኋላ ባሰሙት ንግግር፥ ጦርነት እንዲቆም በማለት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።  

“በጎርጎሮሳውያኑ አዲስ ዓመት መግቢያ ላይ የሰላም ምኞቶችን ብንለዋወጥም ነገር ግን የጦር መሣሪያዎች የሰው ሕይወት ማጥፋት እና ንብረት ማውደምን ቀጥለዋል" ሲሉ ቅዱስነታቸው በምሬት ተናግረዋል።ቅዱስነታቸው በዕለቱ ለምዕመናኑ ባሰሙት ንግግር፥ ሁሉም ሰው በእነዚህ ግጭቶች መካከል ሃላፊነት እና ስልጣን ላላቸው ሰዎች እንዲጸልይ አሳስበው፥ ጦርነት በሰላማዊ ሰዎች ላይ ሞትን የሚያስከትል፥ ከተሞችን እና መሠረተ ልማቶችን የሚያውድም፣ መፍትሄ የሚገኝበት መንገድ አለመሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል ብለው፥ ጦርነት በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸም ወንጀል ነው በማለት አስረድተዋል።

በኢየሩሳሌም የሚገኙት የቅድስት አገር ተንከባካቢ የሆኑት አባ ኢብራሂም ፋልታስ በጣሊያን ቴሌቪዥን ቀርበው ሲናገሩ መከታተላቸውን ቅዱስነታቸው ተናግረው፥ አባ ኢብራሂም ፋልታስ በማብራሪያቸው ስለ ሰላም ማስተማር አስፈላጊነት መናገራቸውን በማስታወስ፥ ሰላም እንዲሰፍን ማስተማር አለብን ብለዋል። “እያንዳንዱን ጦርነት ለማስቆም የሚያስችል በቂ ትምህርት ያለን አይመስልም” ብለው፥ ስለ ሰላም የማስተማር ጸጋን ለማግኘት ዘወትር መጸለይ ይገባል ብለዋል።

በኮሎምቢያ ውስጥ በመሬት መንሸራተት ለተጎዱት የቀረበ ጸሎት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለምዕመናኑ ባሰሙት ንግግር፥ የላቲን አሜሪካ አገር በሆነችው ኮሎምቢያ ውስጥ በደረሰ የመሬት መደርመስ አደጋ ለሞቱት ቢያንስ 34 ለሚሆኑ ሰዎች ጸሎት እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።በሰሜን ምዕራብ የአገሪቱ ክፍል ዓርብ ዕለት ከሰዓት በኋላ የጣለው ከባድ ዝናብ ኩይድቦ እና ሜዴሊን ከተሞችን በሚያገናኝ አውራ ጎዳና ላይ የመሬት መደርመስን አስከትሏል። በአደጋው በደርዘን የሚቆጠሩ አሽከርካሪዎች ቆስለዋል።

የጋዛ ጦርነት 100ኛ ቀን

በእስራኤል እና የሐማስ ታጣቂዎች መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት 100 ቀናትን ማስቆጠሩን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዕለቱ ባቀረቡት የጸሎት ጥሪ አስታውሰዋል። በፍልስጢየም የሚገኙ የሐማስ ታጣቂዎች እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ጥቅምት 7/2023 ዓ. ም. እስራኤል ውስጥ በበርካታ ማህበረሰቦች ላይ ባደረሱት ጥቃት 240 ሰዎችን ማገቱ እና ወደ 1,200 የሚጠጉ ሰዎችን መግደሉ ይታወሳል። እስራኤልም በአጸፋው በሃማስ ታጣቂዎች ላይ ጦርነትን በማወጅ በጋዛ ሰርጥ ሙሉ ወታደራዊ ጥቃቶችን መፈጸሟ አይዘነጋም።

በሐማስ ተዋጊዎች የሚመራ የጤና ተቋም እንደገለጸው፥ በጦርነቱ ወደ 23,000 የሚጠጉ ሰዎች ጋዛ ውስጥ እንደተገደሉ ቢያስታውቅም ነገር ግን እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ወደ 8,000 የሚጠጉ የሃማስ ተዋጊዎችን መግደሏን አስታውቃለች።

 

15 January 2024, 15:30