ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ለእምነት አስተምህሮ ማስተባባሪያ ጽሕፈት ቤት አባላት መልዕክት ሲያስተላልፉ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ለእምነት አስተምህሮ ማስተባባሪያ ጽሕፈት ቤት አባላት መልዕክት ሲያስተላልፉ   (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ "የሚባርኩት የተመሳሳይ ጾታ ጥንዶችን እንጂ ጋብቻቸውን አይደለም!”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ዓመታዊ ጉባኤያቸውን ያካሄዱ የእምነት አስተምህሮ ማስተባባሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አባላትን በሐዋርያዊ የመሰብሰቢያ ሕንጻ ውስጥ ተቀብለው ንግግር አድርገውላቸዋል። ቅዱስነታቸው ከጽሕፈት ቤቱ አባላት ጋር ቅዱሳት ምስጢራትን፣ ሰብዓዊ ክብርን፣ የወንጌል ስርጭት አገልግሎትን እና የእምነት ተማጽኖ ሠነድን በሚመለከቱ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ዓርብ ጥር 17/2016 ዓ. ም. በጽሕፈት ቤቱ ጉባኤው ማጠቃለያ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፥ አባላቱ ላበርከቱት መልካም ተግባር አመስግነው፥ በቅድስት መንበር ሥር በሚገኙ ከፍተኛ ጳጳስዊ ጽሕፈት ቤቶች ‘ሮማን ኩሪያ’ ውስጥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2022 ዓ. ም. ያደረጉትን ማሻሻያ በማስታወስ፥ የእምነት አስተምህሮ ማስተባባሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤትን በሁለት ዘርፍ ማለትም የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮን የሚከታተል እና የትምህርት መስክ እንዲከታተል ማዋቀራቸውን አስታውሰዋል።

እነዚህ የአገልግሎት ዘርፎች አስቀድመው የነበሩ ቢሆንም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው ውስጥ ለማካተት የፈለጓቸው ርዕሦች እንደሆኑ ገልጸው፥ ቅዱሳት ምስጢራት፣ ሰብዓዊ ክብር እና እምነት በሚሉት ርዕሦች ዙሪያ በርካታ ሃሳቦችን አቅርበዋል።

አዲሱ የእምነት አስተምህሮ ጽሕፈት ቤት ሠነድ

ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው የዳሰሱት የመጀመሪያው ርዕሥ፥ ቅዱሳት ምስጢራት የሚል ሲሆን፥ ቅዱሳት ምስጢራት የቤተ ክርስቲያን ሕይወት እንዲያድግ የሚያደርጉ በመሆናቸው እነርሱን በሚያስተዳድሩ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች በኩል ልዩ እንክብካቤ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ተናግረዋል።

አባላቱ የቅዱሳት ምስጢራትን ውበት እና የማዳን ኃይላቸውን መውደድ እና መንከባከብ እንደሚገባ አሳስበዋል። ቀጥለውም ሰብዓዊ ክብርን በማስመልከት ባደረጉት ውይይት፥ የእምነት አስተምህሮ ማስተባባሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ይህን ርዕሥ የሚመለከት አዲስ ሠነድ በማዘጋጀት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ሠነዱ፥ እንደ ቤተ ክርስቲያን ደጋፊ ወደሌላቸው፣ በተጨባጭ በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ውስጥ ከሚታገሉ እና ለተናቁ ሰዎች መብት መከበር በግላቸው ዋጋ ወደሚከፍሉ ሰዎች ዘንድ ለመቀራረብ እንደሚያግዝ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

ዛሬ ወንጌልን ስለ መስበክ

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሦስተኛው የመወያያ ርዕሥ የሆነው እምነት ለረጅም ጊዜ ሲናገሩ የቆዩት ሲሆን፥ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛ እንደተናገሩት፥ በዓለማችን በርካታ አካባቢዎች እምነት ከአሁን በኋላ ለጋራ ሕይወት ግልጽ ቅድመ ሁኔታ ሊሆን ያለመቻሉን እውነታ መደበቅ አንችልም ብለዋል።

“በእርግጥም እምነት ብዙውን ጊዜ ይከዳል፣ ይሳለቅበታል እንዲሁም ይገለላል” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በዛሬው ዓለማችን የእምነት አስተምህሮ እና ምስክርነት በርካታ ምክንያቶችን ከግምት ውስጥ ማስገባት አለበት ብለዋል። በተለይም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ አዳዲስ ባሕሎች ከብዙ ተግዳሮቶቻቸው ጋር የሚያነሷቸው እንግዳ የትርጉም ጥያቄዎች፥ ከተልዕኮአዊ የቤተ ክርስቲያን መዋቅራዊ ለወጥ አስፈላጊነት እና በመጨረሻም፥ በቤተ ክርስቲያን ሕይወት እና ተልዕኮ ውስጥ የወንጌል ስርጭት አገልግሎት ማዕከላዊነትን በማስታወስ፥ በቅድስት መንበር ሥር የሚገኝ የእምነት አስተምህሮ ማስተባባሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት እነዚህን ዘርፎች በሚገባ ለመከታተል የሚያስችል ዕርዳታ የሚያስፈልገው መሆኑን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስረድተዋል።

ሐዋርያዊ ቡራኬዎች

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቀጥለውም፥ የወንጌል አገልግሎት ዐውድን መሠረት በማድረግ፥ በቅርቡ ይፋ የሆነውን የሐዋርያዊ ቡራኬ ሠነድ በመጥቀስ መልዕክት ለማስተላለፍ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል። በሠነዱ ውስጥ በግልጽ እንደተብራራው፥ የሐዋርያዊ እና ድንገተኛ ቡራኬዎች ዋና ዓላማ፥ በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ የሚገኙ ሰዎች በእምነት ጉዞአቸው ለመቀጠል ወይም አንዳንድ ጊዜ እንደገና ለመጀመር ባላቸው ፍላጎት ዕርዳታን ለሚጠይቁት በሙሉ እግዚአብሔር እና ቤተ ክርስቲያን ያላትን ቅርበት በትክክል ለማሳየት ነው ብለዋል።

በዚህ ረገድም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሁለት ነጥቦች ላይ አጽንዖት ሰጥተው፥ በመጀመሪያ እነዚህን ቡራኬዎች ለመቀበል ከሥርዓተ አምልኮ እና ቅርፅ ውጭ ማንኛውም ዓይነት የሥነ-ምግባር ፍፁምነት እንደማያስፈልጋቸው ገልጸዋል።

በሁለተኛ ደረጃ፥ ተመሳሳይ ጥንዶች በድንገት ወደ አንድ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ቀርበው ቡራኬን ሲጠይቁ፥ አገልጋዩ የሚባርከው “ጋብቻቸውን ወይም ኅብረታቸውን” ሳይሆን ነገር ግን የጠየቁትን ሰዎች ብቻ እንደሆነ ገልጸው፥ ጥንቃቄ የሚያሻው ጉዳይ በመሆኑ ግለሰቡ የሚኖርበትን አካባቢ እና ይህን ለማድረግ ተስማሚ የሆኑ መንገዶችን ግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚገባ አሳስበዋል።

27 January 2024, 16:24