ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ልማት ሰፊ የሥነ-ምግባር አመለካከት ሊኖረው ያስፈልጋል አሉ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ማክሰኞ ጥር 7/2016 ዓ. ም. በብፁዕ ካርዲናል ፒተር ታርክሰን ተነቦ በነጋታው ረቡዕ በተላከው መልዕክታቸው፥ የ2024 በዓለም ኢኮኖሚ መድረክ ላይ የዓለም መሪዎች ያላቸውን ግዴታ በማስታወስ የሰውን ልጅ የሚያጋጥም ትልቁ ተግዳሮት በሰላም አብሮ መኖር እና ለሁሉም እኩል ልማትን ማረጋገጥ እንደሆነ አስገንዝበዋል። አክለውም የመድረክ ተሳታፊዎች እና እያንዳንዳችን በድህነት ትግል ውስጥ ያለብንን የሞራል ኃላፊነት፣ ለመላው ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ሁሉን አቀፍ ልማት እና ስኬት ትኩረት እንደምንሰጥ ተስፋዬ ነው” ብለዋል።
ተለዋዋጭ የዓለም አቀፍ ሁኔታ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የዘንድሮው የዳቮስ የውይይት መድረክ አስጨናቂ የሆነ ዓለም አቀፍ አለመረጋጋት በሚታይበት ወቅት መካሄዱን ተናግረዋል። ፎረሙ አክለውም የዓለም መሪዎች የተሻለች ዓለምን ለመገንባት አዳዲስ መንገዶችን እንዲመረምሩ ዕድል የሚሰጥ ሲሆን፥ በሁሉም ሰዎች መካከል ማኅበራዊ ትስስርን፣ ወንድማማችነትን እና እርቅን የሚያጎለብቱበትን መንገድ እንዲፈልጉ ቅዱስነታቸው አሳስበዋል።
በዓለም ክፍሎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ሞትን እና በንብረት ላይም ውድመትን እያደረሱ ያሉ ጦርነቶች እና የረዥም ጊዜ ግጭቶች እንዳሳዘናቸው ገልጸው፥ “የዓለማችን ሕዝቦች የሚናፍቁት ሰላም ከፍትህ የሚገኝ ፍሬ እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም" ብለዋል። በመሆኑም የጦር መሣሪያዎችን ወደ ጎን ማድረግ ብቻ ሳይሆን የግጭት መንስኤ የሆኑ ኢፍትሃዊ ድርጊቶችን መፍታትን ይጠይቃል ብለዋል።
እየጨመረ ያለ የእኩልነት ማጣት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የግጭት መንስኤዎችን በመጥቀስ አንዳንድ የዓለም ክፍሎች ምግብን እንደሚያባክኑ እና ጥቂቶች በአምራች ኢንዱስትሪዎች ሲበለጽጉ በሌሎች ዘንድ የረሃብ እና የተፈጥሮ ሃብት ብዝበዛ መበራከቱን ጠቁመዋል። በተጨማሪም በወንዶች፣ በሴቶች እና በሕፃናት ላይ የሚደርሰውን መጠነ ሰፊ ብዝበዛ፣ ለዝቅተኛ ደሞዝ እንዲሠሩ የሚገደዱበትን፣ የግል ሙያ ዕድገት እና እውነተኛ ተስፋን የተነፈጉበትን ሁኔታ አውግዘዋል። “በዛሬው ዓለም ሰዎች በረሃብ እየሞቱ መሆናቸው፣ መበዝበዛቸው፣ ለመሃይምነት መዳረጋቸው፣ መሠረታዊ የሕክምና አገልግሎት እና መጠለያ ማጣታቸው እንዴት ሊገለጽ ይችላል?” ሲሉ በመገረም ጠይቀዋል።
ግሎባላይዜሽን የሚመራ ሰፊ የሥነ ምግባር አመለካከት
“ግሎባላይዜሽን ጥልቅ የሞራል ልኬት አለው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ልማት የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ የወደፊት ዕጣ ፈንታን የሚቀርጹ ውይይቶችን ለመምራት የሚያስችል ሰፊ የሥነ ምግባር አመለካከት ያስፈልገዋል ብለዋል። "አርቆ አሳቢ እና ሥነ-ምግባራዊ የግሎባላይዜሽን ሞዴሎችን" ለማስተዋወቅ የንግድ ድርጅቶች እና መንግሥታት እንዲተባበሩ ጋብዘዋል። ልማት፥ ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ሥልጣን ለግል ጥቅም ከመዋል ይልቅ፣ ለሰው ልጅ የጋራ ጥቅም መገዛት፣ ለድሆች፣ ለችግረኞች እና ተጋላጭ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ላሉ ቅድሚያን የሚሰጥ መሆን አለበት” ብለዋል።
ልማት ለሁሉም ሊዳረስ ይገባል
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጨረሻም የንግድ ተቋማት መሪዎች እና ፖለቲከኞች በኢኮኖሚ የተቸገሩ ሰዎች ከዓለም አቀፋዊ ዕድገት ጥቅማጥቅሞችን እንዲያገኙ፥ ለፍትሃዊ የዕድገት ስርጭት ቅድሚያን እንዲሰጡ አሳስበዋል። “ትክክለኛው ልማት ዓለም አቀፋዊ፣ በሁሉም አገሮች እና ከሁሉም የዓለም ክፍሎች ጋር የሚጋራ መሆን እንዳለበት፥ አለዚያ እስካሁን ድረስ ቀጣይነት ያለው መሻሻል የታየባቸው አካባቢዎች ወደ ኋላ ይመለሳሉ” በማለት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2024 ዓ. ም. በስዊዘርላንድ ዳቮስ ለሚካሄደው የዓለም ኢኮኖሚክ መድረክ ያስተላለፉትን መልዕክት ደምድመዋል።