ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “ኢየሱስ ክርስቶስ ወጣቶች ደስተኛ ሕይወት የሚያገኙበት መንገድ ነው!”
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ቅዱስ ወንጌልን ማንበብ፣ በትጋት መጸለይ እና የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስን በከፍተኛ ጉጉት ማጥናት የኢየሱስ ክርስቶስ ዓይኖች፣ ስሜቶች እና አመለካከቶች ወደ ልባችን እና ወደ አእምሯችን እንዲተላለፉ ለማድረግ ይረዱናል” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለወጣቶች የተዘጋጀውን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ዕትም አስመልክተው የጻፉት አዎንታዊ መልዕክት፥ “ላ ስታምፓ” በተሰኘ የጣሊያን ዕለታው ጋዜጣ ላይ ሰኞ ጥር 13/2016 ዓ. ም. ታትሟል። ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው ክርስቲያኖች ለመሆናችን እውነተኛው ምክንያት ፍቅር መሆኑን አስታውሰው፥ ወጣቶች የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስን ከልብ እንዲያጠኑ አደራ ብለዋል።
"ለቤተ ክርስቲያን ሕልውና ዋነኛው ምክንያት ፍቅር ነው" ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ከሁሉ አስቀድሞ እግዚአብሔር አብ ለሰው ልጆች ስላለው የርኅራኄ እና የምሕረት ፍቅር እንዲሁም ኢየሱስ ወልድ በሕይወቱ፣ በሞቱ እና በትንሣኤው የገለጠልንን ፍቅር እናገራለሁ" ብለዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም “እያንዳንዳችን እግዚአብሔር ለእኛ ላለን ፍቅር ምላሽ የምንሰጠው እርሱን፣ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን በማፍቀር ነው” ብለው፥ ሁላችን እርስ በእርስ እንድንፋቀር አደራ ብለዋል።
ኢየሱስን በማወቃችን እና ሌሎችም እንዲያውቁት በማድረግ የሚገኝ ደስታ
“እግዚአብሔር ፍቅር ነው” የሚለውን የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ የጻፉትን ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የክርስትና ሕይወታችን የሚፈልቀው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ስንገናኝ እንደሆነ አስታውሰው፥ ይህም ለሕይወታችን አዲስ አድማስ እና አዲስ አቅጣጫን ይሰጠናል ብለዋል። እንደዚሁም የምንወደውን ሰው በሚገባ ከማወቅ እና ከመውደድ በተጨማሪ ስለ እርሱ ሌሎችም እንዲያውቁ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “አንድ ሰው ለኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን ፍቅር ወደ ዓለም ሁሉ ማምጣት በእውነቱ ጣፋጭ የወንጌል ደስታ ነው" ብለዋል። "ይህ በእጃችሁ ያለው ይህ ውብ መጽሐፍ ከእንደዚህ ዓይነት ፍቅር የተወለደ እና እኛ አማኞች ለኢየሱስ ያለው ፍቅር ነው" ብለዋል።
በድጋሚ በአዲስ መልክ የታተውመው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1992 ዓ. ም. ታትሞ የነበረውን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስን “YOUCAT” መሠረት ያደረገ ቢሆንም፥ ለወጣቶች በሚመች ዘይቤ እና አካሄድ የተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመዋል። “በእጃችሁ የሚገኘው ይህ ድንቅ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ መጽሐፍ፥ እኛ የኢየሱስ ክርስቶስ አማኞች፥ ለእርሱ ካለን ፍቅር በመሆኑ የፍቅር ፍሬ ነው” ብለዋል።
“የፍቅር ፍሬ በመሆኑ ይህን አዲሱን የትምህርተ ክርስቶስ መጽሐፍ ውደዱት!” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ አዲሱ መጽሐፍ እናንተ ለኢየሱስ ክርስቶስ ያላችሁትን ታላቅ ፍቅር ከመቀስቀስ ወይም ከማንቃት ውጭ ሌላ ዓላማ እንደሌለው ትገነዘባላችሁ ሲሉም አክለዋል።
ኢየሱስ ክርስቶስ በእኔ ቦታ ምን ያደርጋል?
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ወጣት ካቶሊካውያን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የበለጠ ለማወቅ እና የእርሱ የፍቅር መልዕክት የሕይወታቸውን ዕቅድ በተሻለ ሁኔታ ለመረዳት እንዲያስችላቸው ወጣቶች አዲሱን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስን በሚገባ እንዲያጠኑ አሳስበዋል። ከኢየሱስ ጋር ያለን ግንኙነት የመቀጠል ሚስጥሩ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ ቦታ ሆኖ የሚያደርገውን ነገር በማንኛውም ጊዜ ማጤን እንደሆነ ተናግረዋል።
“ኢየሱስ በእውነት ሕያው እና አስደሳች ሕይወት የሚገኝበትን መንገድ ነው!” በማለት የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በእኛ ላይ የሚደርሰውን ለማወቅ፣ ለመፍረድ እና ውሳኔ ለማድረግ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የሚመሳሰል ዕይታ፣ ስሜት እና አቋም እንዲኖረን ተጠርተናል ብለዋል። ለወጣቶች የተዘጋጀውን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ “YOUCAT” ጥናትን ከማያቋርጥ ጸሎት ጋር በማጣመር ወጣቶች ዓለምን እና የዕለት ተዕለት ክስተቶችን በኢየሱስ ክርስቶስ ዓይን መመልከትን መማር ይችላሉ ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጨረሻም፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ደስተኛ ሕይወትን ለማግኘት የሚያግዝ መንገድ እንደሆነ ገልጸው፥ “ይህን የወጣትነት፣ አዲስ እና ሙሉ ሕይወት ለውድ ወጣቶች እመኝላቸዋለሁ” በማለት መልዕክታቸውን ደምድመዋል።