ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “የእግዚአብሔር ኃይል የሚታወቀው በድካማችን ጊዜ ነው”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ረቡዕ የካቲት 20/2016 ዓ. ም. በጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ ለተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው በዕለቱ አስተምህሮአቸው፥ “የእግዚአብሔር ኃይል የሚገለጠው በድካማችን ወቅት ነው” ብለዋል።

ክቡራት ክቡራን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዛሬው ዕለት ያቀረቡትን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ትርጉም ከማቅረባችን አስቀድመን፥ ለአስተንትኖ ይሆናቸው ዘንድ የመረጡት የአዲስ ኪዳን ጥቅስ የሚከተለው ነው፥

“የክርስቶስ ኢየሱስ የሆኑት ስጋን ከመሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቅለውታል። በመንፈስ የምንኖር ከሆንን በመንፈስ ደግሞ እንመላለስ” (ገላ. 5: 24 - 26)

ክቡራት እና ክቡራን፥ ከዚህ ቀጥሎ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዕለቱ ያሰሙትን ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ክፍል ሙሉ ትርጉሙን እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ እንደምን አረፈዳችሁ! በዛሬው የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በመንፈሳዊ ትውፊት ውስጥ በተጠቀሱ ታላላቅ ርዕሦች ውስጥ የምናገኛቸውን ሁለት ክፉ ምግባሮችን እንመለከታቸዋለን። እነርሱስም ምቀኝነት እና ከንቱ ውዳሴ ናቸው።

በመጀመሪያ ቅናት የሚለውን እንመልከት። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በኦሪት ዘፍ. 4 ላይ ቅናት ከጥንታዊ ክፉ ድርጊቶች መካከል አንዱ እንደሆነ እንገነዘባለን። ቃየል ለአቤል ያለው ጥላቻ እያየለ የመጣው የወንድሙ የአቤል መስዋዕት እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘው መሆኑን ካወቀ በኋላ ነው። ቃየን የአዳምና የሔዋን በኩር ልጅ ነበር። ከአባቱ ርስት ትልቁን ድርሻ ወሰደ። ሆኖም ታናሽ ወንድሙ አቤል ባገኘው ትንሽ ነገር ቢሳካለት ቃየን ተቆጣ። የምቀኛ ሰው ፊት ሁል ጊዜ ያዝናል። ዘወትርም ወደ መሬት ይመለከታል። ሳያቋርጥ መሬቱን የሚመረምር ይመስላል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን የሚመለከተው ምንም የተለየ ነገር የለም። ምክንያቱም አእምሮው በክፋት በተሞሉ ሐሳቦች ውስጥ ስለታሸገ ነው። ምቀኝነት ካልታረመ ሌላውን ሰው ወደ መጥላት ያደርሳል። አቤል የወንድሙን ደስታ መሸከም በማይችለው በቃየል እጅ ተገደለ።

ምቀኝነት በክርስቲያናዊው አመለካከት በሚገባ ያልተመረመረ ብቻ ሳይሆን የፈላስፋዎች እና የጠቢባንን ቀልብ የሳበ ክፉ ምግባር ነው። በምቀኝነት ውስጥ የጥላቻ እና የፍቅር ግንኙነት አለ። አንድ ሰው ለሌላው ክፋን ይመኛል፤ ነገር ግን በድብቅ ያንን ሰው ለመምሰል ይፈልጋል። ሌላው የምቀኝነት ምልክት እኛ መሆን የምንፈልገው ነገር ግን ያልሆንነውን የመሆን መገለጫ ነው። ለአንድ ሰው ስኬት ኢ-ፍትሐዊ መሆን ነው።በዚህ ጊዜ ለራሳችን ብቻ እናስባለን። የዚያ ሰው ስኬት ወይም መልካም ዕድል ይበልጥ ለእኛ ይገባን ነበር! እንላለን።

የዚህ ክፉ ተግባር መነሻ ስለ እግዚአብሔር ያለን የተሳሳተ አስተሳሰብ ነው። እግዚአብሔር ከእኛ የተለየ የራሱ ‘ስሌት’ እንዳለው አንቀበልም። ለምሳሌ ኢየሱስ ክርስቶስ፥ ጌታው በቀን በተለያዩ ጊዜያት ወደ ወይን ቦታ እንዲሄዱ ስላዘዛቸው ሠራተኞች በተናገረው ምሳሌ ላይ፣ በመጀመሪያው ሰዓት ላይ የመጡት ሠራተኛች በመጨረሻው ሰዓት ላይ ከመጡት የበለጠ ደመወዝ እንደሚያገኙ ያምናሉ። ነገር ግን ጌታው  ለሁሉ ተመሳሳይ ክፍያ ይከፍላቸውና እንዲህ አላቸው፡- ‘እኔ የመረጥኩትን እንዳደርግ አይፈቀድልኝምን? እኔ መልካም ስለሆንኩ ትመቀኛለህን?’ (ማቴ 20:15) የራስ ወዳድነት እሳቤያችንን በእግዚአብሔር ላይ መጫን እንፈልጋለን። የእግዚአብሔር እሳቤ ግን ፍቅር ነው። እርሱ መልካም ነገሮችን የሚሰጠን ከሌሎች ጋር እንድንካፈል ነው። ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ክርስቲያኖችን ‘በወንድማማች መዋደድ አጥብቃችሁ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ። እርስ በርሳችሁ ይበልጥ ተከባበሩ’ (ሮሜ. 12፡10)። ለምቀኝነት መድኃኒቱ ይህ ነው!

አሁን ወደ ሁለተኛው ክፉ ምግባር ደርሰናል። እርሱም ከንቱ ውዳሴ ነው። ከምቀኝነት ክፉ ምግባር ጋር አብሮ የሚሄድ ሲሆን፥ እነዚህ ሁለቱ ክፉ ምግባራት አንድ ላይ በመሆን ዋና የዓለም ማዕከል መሆን የፈልጋሉ። ሁሉንም ነገር እና ሰው በነጻነት ለመበዝበዝ ይፈልጋሉ። ሁሉን ምስጋና እና ፍቅር ለራሱ ሊያደርግ ይፈልጋል። ከንቱ ውዳሴ የተጋነነ እና መሠረት የሌለው፣ ለራስ ከፍ ያለ ግምትን መስጠት ነው። በከንቱ ውዳሴ የተሞላ ሰው “እኔ ብቻ” የሚል የማይጨበጥ እኔነት በውስጡ አለው። ርኅራኄ የለሌው እና ከእርሱ በቀር ሌላ ሰው በዓለም እንዳለ ምንም አያስተውልም። ግንኙነቶቹ ሁል ጊዜ ቁሳዊ እና የበላይነትን የሚያንጸባርቁ ናቸው። የእርሱ ማንነት፣ የእርሱ ስኬቶች ለሁሉም ሰው መታየት አለባቸው። በከንቱ ውዳሴ የተሞላ ሰው የሌሎችን ትኩረት ለማግኘት ሳያቋርጥ ይጥራል። አንዳንድ ጊዜ የእርሱ ባህሪያት የማይታወቁ ከሆነ ይቆጣል።  ሌሎች ሰዎች ለእርሱኢ-ፍትሃዊ ናቸው። ሌሎችን ለመረዳት ብቃት የሌላቸው ናቸው። ኢቫግሪየስ ፖንቲከስ የተባለ መኔኩሴ በጽሑፎቹ ውስጥ የአንድን መነኩሴ በከንቱ ውዳሴ መሞላቱን እንዲህ በማለት ገልጿል። ከመጀመሪያዎቹ የመንፈሳዊ ሕይወት በኋላ ወደ ስኬት እንደ ደረሰ ስለተሰማው ምስጋናውን ለመቀበል ወደ ዓለም ወጣ። ነገር ግን በመንፈሳዊው ጉዞ ገና መጀመሪያ ላይ ብቻ እንደሆነ እና ብዙም ሳይቆይ ከደረሰበት ደርጃ ወደ ታች የሚያወርደው ፈተና አድብቶ እንደሚጠብቀው አልተገነዘበም ነበር።

መንፈሳዊ አስተማሪዎች ከከንቱ ውዳሴ የምንፈወስባቸውን ብዙ መድኃኒቶች አይነግሩም። ነገር ግን   የከንቱ ውዳሴ ክፋ ምግባር በራሱ ውስጥ መድኃኒት አለው። በከንቱ ውዳሴ የተሞላ ሰው ከዓለም ሊያጭድ ተስፋ ያደረገው ምስጋና በእርሱ ላይ ይነሳበታል። በሐሰት ማንነት የታለሉ እና ብዙም ሳይቆዩ በሚያፍሩበት ኃጢአት ውስጥ የወደቁት ስንቶች ናቸው!

ከንቱ ውዳሴን የምናሸንፍበት ከሁሉ የተሻለ መመሪያ በሐዋርያው ጳውሎስ ምስክርነት ውስጥ እናገኛለን። ሐዋርያው ጳውሎስ ሊያሸንፈው በማይችለው ሽንፈት ውስጥ ሁል ጊዜ ይወድቅ ነበር። ከዚያ ስቃይ እንዲያድነው ኢየሱስ ክርስቶስን ሦስት ጊዜ ለመነው። በመጨረሻ ግን ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰለት፥ ‘ብርታት በድካም ውስጥ በፍጹም ስለሚገልጥ ጸጋዬ ይበቃሃል’ አለው። ከዚያን ቀን ጀምሮ ጳውሎስ ነፃ ወጣ። የእርሱ ፍጻሜ የእኛም መሆን አለበት። ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው ሁለተኛ መልዕክት ምዕ. 12፡9 ላይ፥ ‘እርሱ ግን ‘ጸጋዬ ይበቃሃል፤ ኃይሌ በድካም ፍጹም ይሆናል’ አለኝ። እንግዲህ የክርስቶስ ኃይል እንዲያድርብኝ በበለጠ ደስታ በድካሜ መመካትን እወዳለሁ”።

 

 

28 February 2024, 16:20