ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሰላም ጸሎት በማድረግ ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሰላም ጸሎት በማድረግ ላይ  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “ከሁሉ በፊት ለእግዚአብሔር መሆን” ለሚለው መጽሐፍ የመቅድም ጽሑፍ አበረከቱ

ደራሲ ኦውስተን አይቨሪ፥ “ከሁሉ በፊት ለእግዚአብሔር መሆን እና ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ሱባኤ መግባት” በሚል አርዕስት በቅርቡ ለጻፈው መጽሐፍ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የመቅድም ጽሑፋቸውን አበርክተዋል። ማክሰኞ የካቲት 5/2016 ዓ. ም. ለንባብ የበቃውን ይህን መጽሐፍ በጋራ ያሳተሙት “ሜሴንጀር” እና ሎዮላ የተባሉ ማተሚያ ድርጅቶች መሆናቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው ለመጽሐፉ መቅድም ያቀረቡት ሙሉ ጽሑፍ የሚከተለው ነው፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በትክክል በሕይወት ልምዱ መሠረት የሎዮላው ቅዱስ ኢግናጢዎስ እያንዳንዱ ክርስቲያን ሕይወቱን በሚገልጽ ትግል ውስጥ እንደሚሳተፍ በግልጽ ተመልክቷል። ይህ ትግል የአብ ፍቅር በውስጣችን እንዳይኖር የሚያደርገውን ድብቅነታችንን ለማሸነፍ የሚደረግ ትግል ነው። ትግሉን የምናሸንፍ ከሆነ እግዚአብሔር እኛን የራሱ መኖሪያ ሊያደርገው ይችላል።  

በራሳችን ብቻ ከመመካት አደጋ ለሚታደገን እግዚአብሔር በውስጣችን መኖሪያ የምናዘጋጅለት ከሆነ  ለፍጥረታት በሙሉ እና ለእያንዳንዱ ፍጡር ክፍት እናደርጋለን። በዚህም የእግዚአሔር ሕይወት እና ፍቅሩ ለሌሎች የሚገለጥበት መንገድ እንሆናለን። ያኔ ብቻ ነው ሕይወት በእውነት ምን እንደሆነ የምንገነዘበው፤ ለእርሱ እና ለሌሎች እንድንሆን የሚፈልገው የጥልቅ አፍቃሪ እግዚአብሔር ስጦታ መሆን የምንችለው።

ትግሉን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሞቱ እና በትንሳኤው አስቀድሞ አሸንፎልናል። በዚህ መንገድ እግዚአብሔር አብ ፍቅሩ ከዚህ ዓለም ሃያላን ሁሉ እንደሚበረታ በእርግጠኝነት ለዘላለም ገልጧል። ነገር ግን እንደዚያም ሆኖ ያንን ድል ለመቀበል እና እውን ለማድረግ ገና ትግል ይቀራል።

በራሳችን ብቻ ከመመካት አደጋ እና አሁን እራሳችንን ችለናል በሚል ቅዠት እና የጸጋው ተካፋዮች እንዳንሆን ከሚያግደን ድብቅነት የተነሳ በዓለማዊነት በመኖር በፈተና ውስጥ መሆንን እንቀጥላለን። ከሥነ-ምህዳር ቀውስ እስከ ጦርነቶች፣ በድሆች እና ተጋላጭ በሆኑ ሰዎች ላይ ከሚደርሱ ኢ-ፍትሃዊ ድርጊቶች እስከ በዓለም ዙሪያ ያሉ ለሕይወት አስጊ የሆኑ ቀውሶች ድረስ፥ መነሻቸው ለእግዚአብሔር እና ለሌሎች ሰዎች መሆናችንን አለመቀበል ነው።

ያንን ፈተና ለመቋቋም ቤተ ክርስቲያን በብዙ መንገዶች ታግዘናለች። ትውፊቶቿ እና ትምህርቶቿ፣ የጸሎት እና የኑዛዜ ልምምዶች እና የቅዱስ ቁርባን መደበኛ አከባበር እግዚአብሔር በላያችን ሊያፈስ የሚፈልገውን የጸጋ ስጦታ የምንቀበልባቸው መንገዶች ናቸው። ከእነዚህ ልምምዶች መካከል ሱባኤ እና የሎዮላ ቅዱስ ኢግናጤዎስ መንፈሳዊ ልምምዶች ይገኙበታል።

ከመጠን በላይ የሆነ ፉክክር እና የማያቋርጥ ውጥረት በሚታይበት ማኅበረሰባችን ውስጥ መንፈሳዊ ሕይታችንን ለማበረታታት ሱባኤ መግባት እጅግ ተወዳጅ እየሆኑ መጥቷል። ነገር ግን የክርስቲያን ሱባኤ አንዳንድ ጊዜ ለዕረፍት ብለን ከምንወጣው ነጻ ጊዜ በጣም የተለየ ነው። የትኩረት ማዕከል እኛ ሳንሆን መልካሙ እረኛ፣ እንደ ተወዳጅ ልጆቹ ፍላጎታችንን የሚመልስልን እግዚአብሔር ነው።

ሱባኤ ፈጣሪ ለፍጥረታቱ በቀጥታ የሚናገርበት ጊዜ ነው። ቅዱስ ኢግናጤዎስ በመንፈሳዊ ልምምዶች ቁ. 15 ላይ እንደገለጸው፥ ሱባኤ እግዚአብሔርን በተሻለ መንገድ እናገለግለው ዘንድ፥ ነፍሳችንን በፍቅሩ እና በምስጋናው የሚያቃጥል ነው። ፍቅር እና አገልግሎት እነዚህ ሁለት የመንፈሳዊ ልምምዶች መሪ ሃሳቦች ናቸው። ኢየሱስ እንደ ደቀ መዛሙርቱ እና ጓደኞቹ ከእርሱ ጋር እንድንጓዝ ሰንሰለታችንን በመበጣጠስ እኛን ሊያገኘን መጣ።

የመንፈሳዊ ልምምዶችን ፍሬዎች ሳስብ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተ ስይዳ የመጠመቂያ ገንዳ አጠገብ ያለውን ሽባ ሰው፥ ‘ተነሥና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ!’ ያለውን አስባለሁ (ዮሐ. 5:1-16)። ሽባው ሰው መታዘዝ ያለበት ትዕዛዝ እና በተመሳሳይ መንገድም የኢየሱስ ክርስቶስ የገርነት እና የአፍቃሪነት ግብዣ ነው።

ሰውየው ውስጣዊ ሽባነት ያለበት ሰው ነበር። ተፎካካሪዎች እና ተወዳዳሪዎች በሚገኙበት ዓለም ውስጥ ውድቀት ተሰምቶታል። የሚፈልገውን ነገር እንደተከለከለ ስለተሰማው ተበሳጭቶ እና በራስ ብቻ በመመካት አመክንዮ ውስጥ የተያዘ ስለነበር ሁሉም ነገር በእርሱ ጥንካሬ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ እርግጠኛ ነበር። ሌሎች ከእርሱ የበለጠ ጠንካራ እና ፈጣን ስለነበሩ በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ወደቀ። ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስ በምሕረቱ ሊያገኘው መጥቶ ከራሱ እንዲወጣ ጠራው። ለኢየሱስ ክርስቶስ የመፈወስ ኃይል ራሱን ክፍት በማድረግ ከውስጣዊም ሆነ ውጫዊ ሽባነት ዳነ። እግዚአብሔርን እያመሰገነ እና ለመንግሥቱ በመሥራት በራስ ብቻ ከመመካት ኩራት ተላቅቆ በየዕለቱ በጸጋው ላይ የበለጠ መደገፍን በመማር ወደፊት ለመራመድ መነሳት ቻለ። በዚህ መንገድ ሰውየው የዚህን ዓለም ተግዳሮቶች በተሻለ መንገድ ለመጋፈጥ ብቻ ሳይሆን ዓለምን በስጦታ እና በፍቅር አመክንዮ እንዲሠራ መሞገት የሚችል ደቀ መዝሙር ሆነ።

እንደ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትነቴ፥ ከሁሉ አስቀድመን እኛነታችንን የእግዚአብሔር ንብረት ማድረግ፣ ከዚያም ለፍጥረት እና ለሌሎች ሰዎች በተለይም ዕርዳታችንን የሚጠይቁ አቅመ ደካሞችን ማበረታታት እፈልጋለሁ። በዘመናችን ያሉትን ሁለቱን ታላላቅ ቀውሶች፥ የጋራ መኖሪያ ቤታችን የሆነች የምድራችን ውድመት እና የሰዎችን የጅምላ ስደትና መፈናቀልን ለማየት የፈለኩት ለዚህ ነው። ሁለቱም በእነዚህ ገፆች ውስጥ የተገለጹት፥ ማንነታችንን የእግዚአብሔር ንብረት ያለማድረግ ቀውስ ምልክቶች ናቸው። በተመሳሳይም ቤተ ክርስቲያን የራሷን የሲኖዶሳዊ ትውፊት ስጦታ እንደገና እንድታገኝ ለማበረታታት ፈልጌአለሁ። ምክንያቱም በእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል ለሚናገረው መንፈስ ቅዱስ ክፍት ስትሆን መላዋ ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔርን እያመሰገነች መንግሥቱን ለማምጣ እገዛዋን እያበረከተች ወደ ፊት ትጓዛለች።

“ከሁሉ በፊት ለእግዚአብሔር መሆን” የሚለው ርዕሥ እና ላለፉት በርካታ ዓመታት ያስተማረኝ የቅዱስ ኢግናጤዎስ አስተንትኖ አንድ ላይ በመቆራኘታው ደስተኛ ነኝ። የመጽሐፉ ደራሲ ኦውስተን አይቨሪ፥ ከብዙ አሥርተ ዓመታት በፊት ያቀረብኳቸውን የሱባኤ ስብከቶች ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ከሆንኩ በኋላ ካቀረብኳቸው አስተምህሮቼ ጋር አንድ ላይ በማሰባሰብ፥ “ከሁሉ በፊት ለእግዚአብሔር መሆን” በሚለው ጭብጥ ውስጥ በማካተት ታላቅ አገልግሎት ሰጥቷል። በዚህ መንገድ ሁለቱም እንዲያበሩ እና በቅዱስ ኢግናጤዋስ መንፈሳዊ ልምምዶች እንዲበሩ አድርጓቸዋል።

ይህ የምንገኝበት ጊዜ እራችንን የምንደበቅበት እና የምንቆልፍበት ጊዜ አይደለም። እግዚአብሔር እኛ ከራሳችን ወጥተን ተነስተን እንድንራመድ እየጠየቀን እንደሚገኝ በግልፅ ተመልክቻለሁ። ከዘመናችን ስቃይ እና ጩኸት ዕይታችንን ወደ ሌላ መመለስ ሳይሆን ወደ ጸጋው መንገድ በሚወስደን መስመር እንድንገባ ይጠይቀናል። እያንዳንዳችን በጥምቀታችን በኩል የዚያ መንገድ አመልካቾች ነን። የሚያስፈልገው እራሳችንን ክፍት ማድረግ ነው።

እነዚህ ስምንት ቀናት በፍቅሩ አማካይነት የእግዚአብሔርን ጥሪ አዳምጠን የሕይወት፣ የተስፋ እና ለሌሎች የጸጋ ምንጭ በመሆን እና የሕይወታችሁን እውነተኛ ደስታን የምታውቁባቸው ጊዜያት እንዲሆኑ እመኝላችኋለሁ። ቅዱስ ኢግናጤዎስ ራሳችንን ለሌሎች የበለጠ በሰጠን መጠን የእግዚአብሔርን ጥልቅ ፍቅር እንድናውቅ ይጋብዘናል። ከሁሉ በፊት የእግዚአብሔር ለመሆን እራሳችንን መርዳት እንድችል በጸሎታችሁ እስታውሱኝ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ከቫቲካን ጥቅምት 1/2016 ዓ. ም.

14 February 2024, 16:44