ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለዛይድ ሽልማት አሸናፊዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፉ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በአቡ ዳቢ ከተማ ለተካሄደው የሰብዓዊ ወንድማማችነት የዛይድ ሽልማት ሥነ-ሥርዓት ባስተላለፉት መልዕክት፥ የሽልማቱ አሸናፊዎች በሰብዓዊ ወንድማማችነት ዙሪያ ያበረከቱትን ከፍተኛ አስተዋጽዖ አወድሰው፥ ሁሉም ሰው የሰላም እና የውይይት ባሕሉን እንዲያሳድግ አበረታትተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው ሰኞ ጥር 27/2016 ዓ. ም. ያስተላለፉትን የቪዲዮ መልዕክት፥ በአቡ ዳቢ ከተማ በተካሄደው የሽልማት ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት አባላት ተመልክተውታል። የዘንድሮው ሽልማት የተዘጋጀው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና የአል-አዝሃር ታላቁ ኢማም ሼክ አህመድ አል ጣይብ በኅብረት ሆነው “የሰው ልጅ ወንድማማችነት ለዓለም ሰላም እና አብሮነት” የሚለውን ሠነድ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2019 የተፈራረሙበትን አምስተኛ ዓመት ለማክበር እንደሆነ ተነግሯል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቪዲዮው መልዕክታቸው ላይ ለታላቁ ኢማም ሼክ አህመድ አል ጣይብ ሰላምታቸውን አቅርበው፥ አራቱ የሽልማቱ አሸናፊዎች የሰው ልጅ ዕድገት ለማጎልበት በሚደረገው ጥረት ላሳዩት አጋርነት ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

የዛይድ ዓለም አቀፍ ሽልማት የተቀበሉት፥ በላቲን አሜሪካ ቺሊ ውስጥ በሚገኝ ማረሚያ ቤት ከታራሚዎች ጋር የሚሠሩ እና የአገሪቱ ዜጋ የሆኑት ካቶሊካዊት መነኩሴ እህት ኔሊ ሊዮን ኮርሪያ፣ በግብጽ የካርዲዮሎጂ የቀዶ ጥገና ሐኪም ግብፃዊው ዶ/ር ማግዲ ያዕቆብ፣ ናህድላቱል ኡላማ እና መሐመድያህ የተባሉ ሁለት የኢንዶኔዥያ እስላማዊ ድርጅቶች መሪዎች መሆናቸው ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለአሸናፊዎቹ ምስጋናቸውን ባቀረቡበት መልዕክታቸው፥ የተሸላሚዎቹ ምሳሌነት በሌሎች ሃይማኖቶች ውስጥ የሚገኙ ምዕመናንም እንደዚሁ መላውን ሰብዓዊ ቤተሰቦችን የሚያገለግሉበትን፣ የእያንዳንዱን የሰው ልጅ ክብር የሚያስጠብቁበት እና በሰብዓዊ ወንድማማችነት ሠነድ ውስጥ የቀረቡትን እሴቶች ለማሳደግ የሚያስተባብራቸው እና የሚያበረታታቸው እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ሰብዓዊ ወንድማማችነት ጥላቻን እና ኢ-ፍትሐዊነትን ለማሸነፍ የሚያግዝ መንገድ እንደሆነ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስረድተው፥ የተለያዩ ባሕሎችን እና ወጎችን እያከበርን የእርስ በርስ ጥላቻን፣ ጥቃትን እና ኢ-ፍትሃዊነትን ለማሸነፍ ወንድማማችነትን መገንባት እንዳለብን በመረዳት፥ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ እንደ ወንድም እና እንደ እህት በኅብረት ተጉዘናል” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአቡ ዳቢ ከተማ በተካሄደው የሽልማት ሥነ-ሥርዓት ላይ ለተገኙት አባላት፥ የተስፋ ዘሮችን ወደ ዓለም ሁሉ ማዳረስን እንዲቀጥሉ በመጋበዝ አጭር የቪዲዮ መልዕክታቸውን አጠናቅቀዋል።

 

 

 

06 February 2024, 16:10