ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “የሃይማኖት ሚና የሰዎችን ልብ በማስተማር ኅብረተሰቡን እንዲለውጡ ማገዝ ነው”
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በሰሜን አሜሪካ ኢንዲያና ግዛት ውስጥ ከሚገኝ የኖትርዳም ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት እና የአስተዳደር አባላትን ሐሙስ ጥር 23/2016 ዓ. ም. በቫቲካን ተቀብለው በመምህራን ተልዕኮ ላይ ያላቸውን ራዕይ ማጠቃለያ አቅርበዋል። በዩኒቨርሲቲው በሃላፊነት ቦታ ለሚገኙት ወንድ እና ሴት አባላት በጥልቀት ያስተነተኑባቸውን ሦስቱን የትምህርት ቋንቋዎች በማስታወስ እነርሱም ራስ፣ ልብ እና እጅ መሆናቸውን ገልጸዋል። እነዚህ ሦስቱ የሰውነት ክፍሎች የካቶሊክ ትምህርት አስኳል እንደሆኑ ገልጸው፥ ግባቸውም ወጣቶች ወደ ብስለት እና ወደ ሙሉነት እንዲደርሱ መርዳት ነው ብለዋል።
ልዩ ልዩ አእምሯዊ ፋኩልቲዎች
ኖትርዳምን የመሳሰሉ ካቶሊክ ዩኒቨርስቲዎች እውቀትን ለማሳደግ የሚረዱ የጥናት እና የምርምር ሥራዎችን እንደሚያካሂዱ የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ ብዙ ጊዜም ልዩ ልዩ ዘርፎች የሚገኙባቸውን የትምህርት ዘዴዎችን እንደሚጠቀሙ አስረድተዋል። “እነዚህ ካቶሊካዊ የትምህርት ተቋማት የሚያካሂዷቸው የማስተማር ጥረቶች ከክርስትና መልዕክት የሚፈልቁ እና ለሁሉም የግል እና ማኅበራዊ ሕይወት የሚኖረውን የእምነት እና የምክንያታዊ አንድነት ጽኑ እምነት ላይ የተመሠረቱ ናቸው” ብለዋል። በመሆኑም የኖትርዳም ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ መምህራን፥ ተማሪዎቻቸው በጠቅላላ ትምህርት እና የካቶሊክ ምሁራዊ ትውፊትን በማድነቅ ጭንቅላታቸውን ወይም የአዕምሮ ብቃታቸውን እንዲያዳብሩ ማገዝ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የልብ ህልሞች
በአይሁድ እና በክርስትና ባሕል ውስጥ የጥበብ እና የእምነት መቀመጫ ተብሎ የሚታወቀውን ልብ ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የካቶሊክ ትምህርት ሦስት የረቀቁትን እነርሱም እውነትን፣ መልካምነትን እና ውበትን ለማዳበር የሚያግዝ ሊሆን ይገባል ብለዋል። ይህም ጥልቅ የሕይወት ጥያቄዎችን በጋራ ለመመልከት መምህራን እና ተማሪዎች እውነተኛ ግንኙነት እንዲፈጥሩ ይጠይቃል ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የኖትርዳም ካቶሊክ መምህራን፥ ወጣቶች በራሳቸው ሕሊና ምላሽ እንዲሰጡ በማድረግ ሕልማቸውን እንዲያልሙ መርዳት እንደሚገባ አደራ ብለዋል። ይህ ማለት የውይይት እና የእርስ በእርስ ግንኙነት ባህል በማሳደግ ሁሉን ሰው እንደ ወንድም እና እንደ እህት በመመልከት፥ ከሁሉም በላይ እንደ ተወዳጅ የእግዚአብሔር ልጅ እውቅናን መስጠትን፣ ማድነቅን እና መውደድን እንዲማሩ ማድረግ እንደሆነ አስረድተዋል። ስለሆነም የሃይማኖት ሚና የሰዎችን ልብ በማስተማር ተማሪዎች ኅብረተሰቡን እንዲያድሱ እና የሕይወት ፈተናዎችን እንዲጋፈጡ በሚረዳ መልኩ ማነጽ እንደሆነ አክለው አስረድተዋል።
ለአገልግሎት የዋሉ እጆች
ለሰው ልጅ የበጎ አድራጎት ሥራ የቆሙ ንቁ እጆች የካቶሊክ ትምህርት ግብን እንደሚወክሉ የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በተግባራችን አማካይነት በጋራ አብሮ መኖርን፣ ወንድማማችነትን እና ሰላምን በማስተማር የተሻለች ዓለም እንድንገነባ ተጠርተናል” በማለት አክለዋል። “በተቋሞቻችን ግድግዳዎች ወይም በድንበሮች ታጥረን መቆየት አንችልም” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ነገር ግን ወደ ተረሱት ዳርቻዎች በመድረስ በጎረቤታችን አማካይነት ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ለመገናኘት እና እርሱን ለማገልገል መጣር አለብን ብለዋል። ቅዱስነታቸው ከዚህም ጋር በተያያዘ የተቸገሩ ማኅበረሰቦችን ለመርዳት ዩኒቨርሲቲው በተማሪዎች መካከል ቅንዓትን ለማጎልበት ለሚያደርገው ጥረት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
ለኅብረተሰቡ በጎነት የሚሆኑ ኃይለኛ ዘዴዎች
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የትምህርት ቤቱን ልዩ ባህሪ እና ማንነት ለማስጠበቅ ላደረጉት የላቀ አገልግሎት በማመስገን፥ ከኖትርዳም ዩኒቨርሲቲ ባለስልጣናት ጋር የነበራቸው ቆይታ አጠናቅቀዋል። "ለዚህ ተቋም ሕይወት የምታበረክቱት አስተዋጾ ጠንካራ የካቶሊክ ትምህርት ትሩፋትን በማጎልበት እና የዩኒቨርሲቲው መሥራች የነበሩ የአባ ኤድዋርድ ሶሪን ፈለግ በመከተል በኅብረተሰቡ ውስጥ በጎነት ጠንካራ እንዲሆን ያስችላል ብለዋል።
ቅዱስነታቸው በመጨረሻም በዕለቱ ያደረጉትን ንግግር ጽሑፍ በማንበባቸው እንግዶችን አመስግነው፥ በየዕለቱ ለሚታተመው ጋዜጣም ደንበኛ በመሆን ወቅታዊ እና ጠቃሚ መረጃዎችን ማግኘት እንደሚችሉ ተናግረዋል።