ፈልግ

ቅዱስነታቸው በጉባኤው ላይ ከተገኙት የአካዳሚው አባላት ጋር ሰላምታ ተለዋውጠዋል  ቅዱስነታቸው በጉባኤው ላይ ከተገኙት የአካዳሚው አባላት ጋር ሰላምታ ተለዋውጠዋል   (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “ሰው ትርጉም የሚያገኘው በእርስ በርስ ግንኙነት እንጂ በቴክኖሎጂ በኩል አይደለም!"

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጳጳሳዊ የሥነ-ሕይወት ጥናት አካዳሚ አስተባባሪነት ከየካቲት 4-5/2016 ዓ. ም. ድረስ በተካሄደው ጉባኤ ላይ የተገኙትን የአካዳሚው አባላት በቫቲካን ተቀብለው ንግግር አድርገውላቸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጉባኤውን ተሳታፊዎች ሰኞ የካቲት 4/2016 ዓ. ም. በቫቲካን ተቀብለው ባሰሙት ንግግር፥ በሰው ልጅ የትርጉም ፍለጋ ላይ ከሌሎች ሰዎች ጋር ያለን ግንኙነት የህልውናችን እምብርት ነው ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በቫቲካን የተቀበሏቸው አባላት፥ “የሰው ልጅ ማንነት፣ ትርጉሞች እና ተግዳሮቶች" በሚል ርዕሥ በተዘጋጀው ጠቅላላ ጉባኤን የተሳተፉ እንደ ነበር ታውቋል።  

ቅዱስነታቸው ለአባላቱ ባደረጉት ንግግር፥ አካዳሚው በሰው ልጅ ልዩነት ላይ የሚያደርገው ምርምር እና ጥረት አስፈላጊነት ገልፀው፥ በሁሉም የሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ ባለው የቴክኖሎጂ መስፋፋት ላይ በማሰላሰል፥ ቴክኖሎጂን ከሰው ልጅ ዕድገት በተቃራኒ መመልከት እንደማይቻል ጠቁመዋል። ሳይንሳዊ እና ቴክኖሎጂያዊ እውቀትን ሰፋ ባለ አድማስ ውስጥ በማስቀመጥ ከቴክኖክራሲያዊ የበላይነት አስተሳሰብ መከላከል እንደሚያስፈልግ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስቱ አሳስበዋል።

የአስተሳሰብ ወጥነት እና የአመለካከት ልዩነት

የሰው ልጅን በተለያዩ ገፅታዎች የሚያስቀምጠውን ቴክኖሎጂ በምሳሌነት የጠቀሱት ቅዱስነታቸው፥ እያንዳንዱን ዓይነት መረጃ ለመተንተን የሚችል ሁለትዮሽ ኮድን እንደ ዲጂታል ቋንቋ መጠቀምን ገልጸዋል።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኦሪት ዘፍጥረት ምዕ. 11:1-9 ላይ ስለ ባቢሎን ግንብ ከሚናገረው ታሪክ ጋር ያለውን ትይዩነት ግልጽ በሆነ መንገድ በመጥቀስ፣ የሰው ልጅ እርስ በርስ የሚግባባበትን አንድ ቋንቋ ብቻ ለመፍጠር የሚያደርገውን ጥረት እግዚአብሔር መቅጣት ብቻ ሳይሆን ሰዎች በሙሉ እንደ ሌሎች ሰዎች ተመሳሳይ አስተሳሰብ እንዲኖራቸው የማስገደድ ዝንባሌን ለመከላከል የሰዎችን ቋንቋ በማለያየት እንደ ባረከው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ተናግረዋል። “በዚህም መንገድ ከአቅም ውስንነት እና ተጋላጭነት ጋር ፊት ለፊት እንዲጋፈጡ እና ልዩነቶቻቸውን በማክበር አንዱ ለሌላው መተሳሰብን እንዲያሳይ የሰው ልጆች ይሞገታሉ” ብለዋል።

የግንኙነት ጥልቀት ከቋንቋ በላይ ነው

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሳይንስ ጠበብት እና ተመራማሪዎች ሥራቸውን ዘወትር በኃላፊነት እንዲለማመዱ እና የፈጠራ ተግባራቸው ዘወትር ከእግዚአብሔር ችሎታ የበታች መሆኑን እንዲያውቁ አሳስበዋል። ሰው ሠራሽ አስተውሎት ወይም “ተናጋሪ መሣሪያዎች” ተብለው የሚጠሩ በመሆናቸውም፥ የቴክኖሎጂ ዕድገቶች ምንም ዓይነት የሰውን ልጅ ሕልውና ማሳነስ በማይችሉ መንገዶች መከናወን አለባቸው ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመቀጠል “የሥነ-ሰብ ሊቃውንት ዋና ተግባር የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሃብቶችን በማዋሃድ ለሰው ልጅ የማይጠፋ ልዩ ባህሪ እውቅና ለመስጠት እና ለማስተዋወቅ የሚያስችል ባሕል ማዳበር ነው” ብለዋል።

በሐዘን፣ በስሜት፣ በፍላጎት እና ሆን ተብሎ በሚታወቀው መስክ ውስጥ ከሚገኝ ቋንቋ ይልቅ በሰው ልጆች መካከል ያለውን ግንኙነት ከፍ የማድረግ ዕቅድ መኖሩን ቅዱስነታቸው ገልጸው፥ አክለውም “እነዚህን ስሜታዊ ልውውጦች የሚገነዘቡት እና በእግዚአብሔር ጸጋ በመታገዝ ከሌሎች ጋር ወደ አዎንታዊ እና ጠቃሚ ግንኙነቶች መቀየር የሚችሉት ሰዎች ብቻ ናቸው” ብለዋል።

ፍሬአቸውን ሌሎችም ጭምር መሰብሰብ የሚችሉባቸውን ዛፎች መትከል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ጳጳሳዊ የሥነ-ሕይወት ጥናት አካዳሚ ተመራማሪዎች በቴክኖሎጂ ዕድገት ላይ ያላቸውን አስተያየት የሚለዋወጡበትን የዕውቀት ዘርፍን ለመፍጠር ያደረጉትን ውይይት በማወደስ፥

በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እየተካሄደ ካለው የሲኖዶስ ሂደት ጋር ያለውን ተነሳሽነትንም አጉልተው አሳይተዋል። "ይህ ሂደት ጥንቃቄ የተሞላበት ትኩረት፣ የመንፈስ ነፃነት እና ያልተመረመሩ እና ያልታወቁ መንገዶችን ለመከተል ዝግጁ መሆንን የሚያካትት በመሆኑ ወደ ኋላ ከመመልከት እና ከንቱ ሙከራዎችን ከማድረግ የጸዳ ነው" ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማጠቃለያቸው፥ ክርስትና በቴክኖሎጂ እና በባሕል መካከል ለሚደርግ ውይይት አስተዋይነታ ያለውን ገጽታን ሲሰጥ መቆየቱን ተናግረው፥ “ክርስትና ሥር በሰደዱ ባሕሎች ውስጥ ዘልቆ በመግባት በኢየሱስ ክርስቶስ እና በወንጌል ብርሃን በመተርጎም፥ በተለያዩ ባሕላዊ ሁኔታዎች ውስጥ የሚገኙትን የቋንቋ እና የጽንሰ ሐሳብ ሃብቶች በማሟላት ዘወትር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል” ብለዋል።

13 February 2024, 16:39