ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፥ በአቡ ዳቢ ሐዋርያዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት (ጥር ወር 2011 ዓ. ም.) ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፥ በአቡ ዳቢ ሐዋርያዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት (ጥር ወር 2011 ዓ. ም.)   (ANSA)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ሰላም መተዋወቅን፣ መደማመጥን እና በሃሳብ መግባባትን የሚጠይቅ መሆኑን ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አቡ ዳቢ በእስልምና ጉዳዮች ላይ በተካሄደው 4ኛው ዓለም አቀፍ መድረክ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ሰላም መተዋወቅን፣ መደማመጥን እና መቻቻልን የሚጠይቅ መሆኑን ገለጹ። መድረኩ በአቡዳቢ ከተማ በሰብዓዊ ወንድማማችነት ለዓለም ሰላም እና አብሮ የመኖር የጋራ መግለጫ ጥር 27/2011 ዓ. ም. የተፈረመበትን አምስተኛ ዓመቱን ማክበሩ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ለመድረኩ ተሳታፊዎች በላኩት መልዕክት፥ “ሌሎችን አለማወቅ፣ አለማዳመጥ እንዲሁም አለመቻቻል፥ እነዚህ ሦስቱ ጦርነትን በማስከተል እና ፍትህን በማጉደል የሰው ልጆች ወንድማማችነትን እንደሚያበላሽ ገልጸው፥ የሰው ልጅ ጥበብን እና ሰላምን ለማግኘት ከፈለገ በግልፅ ሊታወቁ ይገባል” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህን መልዕክት የላኩት፥ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አቡ ዳቢ ከተማ ከጥር 26-29/2016 ዓ. ም. ድረስ በአውሮፓ እና ሊባኖስ የእስልምና ጉዳዮች ላይ በመካሄድ ላይ ባለው  አራተኛው የምርምር መድረክ ላይ ለተገኙት አባላት ሲሆን፥ “እስልምና እና የሰው ልጅ ወንድማማችነት የአቡ ዳቢ አብሮ የመኖር ሠነድ ተፅእኖ እና ተስፋዎች ናቸው” ሲሉ አቋማቸውን አረጋግጠዋል።

የኮንግሬሱ ምሥረታ

አካዳሚያዊ መድረኩ የተፈጠረው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2014 ዓ. ም. በአውሮፓ የካቶሊክ ዩኒቨርስቲዎች ፌዴሬሽን (FECU)፣ በእስልምና እና በክርስቲያን ውይይቶች ላይ ለሚሠሩ ምሁራን ምርምር እና ሃሳባቸውን እንዲያካፍሉ እና በአካዳሚያዊ እና በማህበራዊ ተዋናዮች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማበረታታት እንደሆነ ታውቋል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2016 ፣ በ2018 እና በ2022 ዓ. ምህረቶች በተካሄዱት ቀደምት ኮንግረንሶች ላይ የተመሠረተው ይህ መድረክ፥ ከተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የመቻቻል እና አብሮ የመኖር ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የሰብዓዊ ወንድማማችነት፣ የዓለም ሰላም እና አብሮ የመኖር መግለጫ የወጣበትን አምስተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀ እንደሆነ ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስ ፍራንችስኮስ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አቡ ዳቢ ከተማ ሐዋርያዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ከአል-አዝሃር ታላቅ ኢማም ከሆኑት አህመድ አል ታይብ ጋር ተገናኝተው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የካቲት 4/2011 ዓ. ም. የሰብዓዊ ወንድማማችነት ሠነድ መፈረማቸው ይታወሳል።

በአራት አህጉራት ከሚገኙ 40 ዩኒቨርሲቲዎች እና የምርምር ተቋማት የተውጣጡ ከ57 በላይ ተናጋሪዎች እና ሊቃነ መናብርት ይህን ታሪካዊ ሠነድ ገምግመው በማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ሥነ መለኮት አውድ ውስጥ ለማስተዋወቅ የሚያግዙ ነጥቦችን ለመዳሰስ ማለማቸው ታውቋል።

ለኢ-ፍትሃዊነት እና ለጦርነት ፈተናዎች የተጋለጠው ሰው ልጅ ወንድማማችነት

ለመድርኩ አዘጋጆች ምስጋናቸውን የላኩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ዓለም አቀፋዊ ወንድማማችነት እና አብሮ መኖር ለፍትሕ መጓደል እና ለጦርነት ፈተናዎች መጋለጣቸው ዘወትር ለሰው ልጆች ሽንፈት ናቸው” ብለዋል። በተጨማሪም የአቡ ዳቢ ሠነድ በትምህርት እና በምርምር ተቋማት ውስጥ የአስተንትኖ ርዕሠ ጉዳይ በመሆን ለሰላም፣ ለፍትህ እና ለኅብረተሰብ ግንባታ፥ የዝቅተኞችን መብቶች ለማስከበር የሚተጉ አዳዲስ ትውልዶችን ለማፍራት አስፈላጊ እንደሆነ አፅንዖት ሰጥተዋል።

ለውይይት እና ለግንኝነት ትምህርት የሚሰጠው ጥቅም

ለጦርነት ቀዳሚው ምክንያት እርስ በርስ አለመተዋወቅ እና አለመግባባት እንደሆነ የጠቀሰው የቅዱስነታቸው መልዕክት፥ እርስ በርስ መተማመንን ማሳደግ እና በሰብዓዊ ወንድማማችነት ላይ ያለውን አሉታዊ አመለካከቶች በመቀየር፥ ተቀባይነት ያለው የሰላም ሂደት መጀመር እንደሚያስፈልግ አመልክቷል። “ሰላም ያለ ትምህርት በመከባበር እና በመግባባት ላይ ብቻ የተመሠረተ ከሆነ ዋጋ የለውም” ሲሉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አሳስበዋል። ቅዱስነታቸው አክለውም፥ “እንግዲህ የጋራ ውይይትን እንደ ዋና መንገድ በመውሰድ፥ ትብብርን እንደ የሥነ ምግባር ደንብ በመቀበል የምንመኘውን ዓለም ለመገንባት የምንፈልግ ከሆነ የመግባቢያ ዘዴ እና መለኪያ የውይይት እና የግንኙነት ትምህርት ሊሆን ይገባል” ብለዋል።

ሌላውን ማዳመጥ

የሰው ልጅ እውቀትን ከሰው ሠራሽ አስተውሎት ተቃራኒ መሆኑን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ሌላውን የማዳመጥ ኃይል እና የእውነተኛ ውይይት የተለያዩ አመለካከቶችን በመረዳት ረገድ ያለውን ሚና አጉልተዋል። በእርግጥም የመደማመጥ አለመኖር “ወንድማማችነትን የሚጎዳ ሁለተኛው ወጥመድ ነው” ብለው፥ በክርክር ወቅት መደማዳመጥን መማር አለብን ብለዋል።

የአዕምሯዊ ተለዋዋጭነት አስፈላጊነት

ቅዱስነታቸው መልዕክታቸውን በመቀጥል፥ ክርክር የግለሰቦችን አዕምሮአዊ ተለዋዋጭነት እና ወንድማማችነትን መሠረት ያደረገ ምሁራዊ ትምህርት እንደሆነ ገልጸው፥ ጥበብ ከሁሉም ጋር ለመወያየት እንደምትፈልግ እና ዋጋን እንደምትሰጥ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2017 ዓ. ም. በአል-አዝሃር ካይሮ በተካሄደው ዓለም አቀፍ የሰላም ጉባኤ ላይ ያደረጉትን ንግግር አስታውሰዋል።

የወንድማማችነት ሰላም ህልም በቃላት ተወስኖ መቅረት የለበትም

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው ማጠቃለያ፥ የጉባኤው ተሳታፊዎች በሰላም ውስጥ ያለው የወንድማማችነት ሕልም በቃላት ተወስኖ እንዲቆይ አሳስበው፥ በሁሉም ዓይነት ብልጽግና ውስጥ ውይይትን ተቀብለው ማዳበር እንደሚገባ እና ዓለምን እንዲያዳምጡ አበረታተዋል።

በአቡ ዳቢ ውይይት ሊደረግባቸው የሚገቡ ጭብጦች

ለአራት ቀናት በሚቆየው ኮንፈረንስ ላይ የሰው ልጅ ወንድማማችነትን በማስተዋወቅ ረገድ፥ ልዩ ልዩ ገፅታዎችን እና ተግዳሮቶችን በሚዳስሱ በሦስት ጭብጦች ላይ ማብራሪያ ይሰጥባቸዋል። ማኅበራዊ እና ሕጋዊ ጭብጥ በመድብለ ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ ማኅበረሰቦች ውስጥ ያለውን የሙሉ ዜግነት ጉዳይን የሚመረምር ሲሆን፥ በተለይም ለአናሳ ሃይማኖቶች ሕጋዊ ጥበቃ በማድረግ ትኩረትን ይሰጣል። ዓላማው መልካም ተግባራትን፣ የሃይማኖት ነፃነትን እና በአናሳ ሕዝቦች መብቶች እውቅናን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ግምገማ ያካሂዳል። የሁለተኛው ጭብጥ ዘመን ጂኦፖለቲካዊ ሲሆን፥ በዚህ ወቅት ተሳታፊዎች በወቅታዊ ግጭቶች ውስጥ የሃይማኖት እና ርዕዮተ ዓለም ሚናን የሚፈትሹበት ይሆናል። የሃይማኖት አክራሪነትን እና አለመቻቻልን ለመዋጋት የታለሙ ሂደቶች አወንታዊ ምሳሌዎችን መለየት ይሆናል። እንዲሁም መንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እንደ ዘላቂ ልማት፣ ሰብዓዊ መብቶችን እና የሰላም የጋራ ግቦችን በማስተዋወቅ ረገድ ሃይማኖታዊ ተዋናዮችን እንዴት ማሳተፍ እንደሚችሉ ይዳስሳል።

በመጨረሻም የነገረ መለኮታዊ ውይይት ጭብጥ በሰብዓዊ ወንድማማችነት ሠነድ ላይ የተገለጸውን ሥነ-መለኮታዊ አስተንትኖ በመዳሰስ፥ ክርስቲያኖች እና ሙስሊሞች ለሁሉ አቀፍ ወንድማማችነት አመለካከቶች ወንድማማችነትን እና ተልዕኮቸውን እንደገና እንዴት እያሰቡ እንደሚገኙ ይቃኛል።

 

 

05 February 2024, 16:44