ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የቪድዮ መልእክት ባስተላለፉበት ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የቪድዮ መልእክት ባስተላለፉበት ወቅት  (Vatican Media)

ር.ሊ.ጳ ፍራንችስኮስ ዳኞች መብቶችን ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት ኢየሱስ እንደሚያግዛቸው ገለጹ!

በዘመናችን ከሚፈጸሙ ጥልቅ ኢፍትሃዊ ድርጊቶች በማስጠንቀቅ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአርጀንቲና ለሚገኙት የማህበራዊ መብቶች ተሟጋች የፓን-አሜሪካን ዳኞች ኮሚቴ እና በአርጄንቲና የፍራንችስኮስ አስተምህሮ ተከታይ የሆኑ ማሕበር አባላት በቪዲዮ በላኩት መልእክት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጎጂዎችን እና የተጎጂዎችን መብት ለመጠበቅ የሚያደርጉት ስራ ቅዱስነታቸው አወድሰዋል፣ በእዚሁ እንዲቀጥሉ አበረታቷቸዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

"እኛ የምንኖረው በጥልቅ ኢፍትሃዊነት ውስጥ ነው፡ ጥቂት ሀብታሞች እየበዙ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ድሆች እየተገለሉ እና እየተጣሉ ነው። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህጻናት የሚበላ ነገር ተትረፍርፎ ሳለ በብክነት ምግብ በሚጣልበት ዓለም ውስጥ ሆነው በርሃብ አደጋ ውስጥ ይገኛሉ፣ አለም የወደፊት፣ የልማት፣ የፍትህ፣ የዲሞክራሲ ዓለም ትሆን ዘንድ የበኩላችሁን አስተዋጾ እንድታደርጉ” ሲሉ ቅዱስነታቸው በቪዲዮ ባስተላለፉት መልእክት ገልጸዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ረቡዕ የካቲት 20/2016 ዓ.ም ለፓን አሜሪካን የዳኞች የማህበራዊ መብቶች ተሙጋቾች እና የፍራንችስኮስ አስተምህሮ ተከታዮች (COPAJU) በላኩት የቪዲዮ መልእክት ላይ ይህንን ከባድ ማሳሰቢያ ነበር ቅዱስነታቸው የተጠቀሙት።

የማሕበሩ ታሪክ

እ.አ.አ ከ 2017 ዓ.ም ጀምሮ በአርጀንቲና ዋና ከተማ በቦነስ አይረስ የመጀመሪያውን አካባቢውን መነሻ ያደረገው በአርጀንቲና ለሚገኙት የማህበራዊ መብቶች ተሟጋች የፓን-አሜሪካን ዳኞች ኮሚቴ እና በአርጄንቲና የፍራንችስኮስ አስተምህሮ ተከታይ ማሕበር (COPAJU) በመላው አርጄንቲና በፍጥነት የተስፋፋ እና መሕበራዊ ችግሮችን በከፍተኛ ደረጃ እየቀረፈ የሚገኝ ማሕበር ነው። እ.ኤ.አ. ሰኔ 2019 በጳጳሱ ትእዛዝ ማሕበሩ በቫቲካን ውስጥ በይፋ የተመሰረተ እና ከአሜሪካ የመጡ 120 ዳኞች በተገኙበት በቫቲካን ካሲና ፒዮ ውስጥ በቫቲካን የቅድስት መንበር ከፍተኛ የሳይንስ ተቋም ውስጥ በተካሄደው ስብሰባ ነበር አገልግሎቱን በይፋ የጀመረው።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ማሕበሩ በተዘነጉ እና የመብት ጥሰት በሚታይባቸው ማህበራዊ ዘርፎች ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት የማህበራዊ መብቶችን ከመብት ጥበቃ ጋር በማስተዋወቅ ላይ ያተኮረ ድንቅ ስራዎችን አከናውኗል። በአርጀንቲና፣ ቺሊ፣ ኮሎምቢያ፣ ፔሩ፣ ብራዚል፣ ሜክሲኮ፣ ዩናይትድ ስቴትስ እና ፓራጓይ ውስጥ ብሔራዊ ማሕበሮችን መስርቷል እናም መስፋፋቱን ቀጥሏል።

የዳኞች ወሳኝ ሚና

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለማሕበሩ አዲስ ዋና መሥሪያ ቤት በቦነስ አይረስ እና በላቲን አሜሪካ የሚገኘው የፍራይ ባርቶሎሜ ዴ ላስ ካሳ ተቋም የመጀመሪያ ቅርንጫፍ ቢሮ እንዲከፈት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በመልዕክታቸው እንደተናገሩት በፍትህ ላይ የተሰማሩ ጠበቆች፣ ዳኞች፣ አቃቤ ህጎች እና የሰብዓዊ መብት ተከላካዮች በተለይም መብቶችን ለማስጠበቅ እና ማህበራዊ ስምምነትን ለማስጠበቅ ተልእኮው መሰረታዊ እና ወሳኝ ነው ሲሉ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልእክት ገልጸዋል።

ማህበራዊ መብቶች እና ፍትህ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ "ማህበራዊ መብቶች ነጻ አይደሉም" "እነሱን ለመደገፍ የምያስችል ሀብት ግን አለ" ያሉት ቅዱስነታቸው "ነገር ግን በቂ ምክንያታዊ እና ፍትሃዊ የፖለቲካ ውሳኔዎችን ይጠይቃል። ግዛቱ ዛሬ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አስፈላጊ ነው፤ "ይህንን ማሕበራዊ የሆኑ ሐብቶችን ፍትሃዊ እና እኩል በሆነ መልኩ እንዲከፋፈል የማድረግ ግዴታ አለባችሁ፣ ይህንን ማዕከላዊ ሚና ተግባራዊ እንዲያደርጉ ተጠርቷል፣ ማህበራዊ ፍትህ እንዲሰፍን የበኩላችሁን ጥረት እንድታደርጉ እፈልጋለሁኝ" ሲሉ ቅዱስነታቸው በመልእክታቸው አስተላልፏል።

"የገበያ 'አምልኮ' እና ትርፋማነትን እንደ አምልኮ አድርጎ መቁጠር እነዚህ "የውሸት አማልክቶች ናቸው" ሲሉ አጥብቆ ተናግሯል፣ ታሪክ ይህንን በይፋ ገልጿል "ወደ ሰብአዊነት ማጣት እና ዓለማችንን ወደ ማጥፋት ይመራናል" ሲሉ ቅዱስነታቸው ተናግረዋል።

ዐይናችንን ልንጨፍን አንችልም

"የቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ የተመሰረተበት የኢየሱስ ቃል፣ በህግ ውስጥ በትክክል ለመሳተፍ አስተማማኝ እና ብሩህ መንገድ ነው" ሲሉ ጳጳሱ አስምረውበታል።

ዳኞች የሚጠበቅባቸውን ስነ-ምግባር እና የሞራል ሀላፊነታቸውን በማስታወስ "እባካችሁ በየቀኑ በመስታወት ፊት ራሳችሁን ጠይቁ እና ሌሎችንም ጠይቁ" ብሏል።

ከሰብአዊነት ዝቅጠት አንፃር ጥብቅነት እና ቆራጥነት

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ዳኞች ፍትሃዊነት ላይ እና የተከበሩ ማህበረሰቦች ላይ እንዲሰሩ አሳስበዋል፣ እናም አንድ ሰው የሌላውን ስቃይ ላለማየት ዐይኑን ሊጨፍን በፍጹም አይችልም ብለዋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማጠቃለያው መልእክታቸው ዳኞች “ሰብዓዊነት የጎደላቸው እና የዓመፀኛ ሰው ምሳሌ የሆኑ” ሰዎች ሲገጥሟቸው ቆራጥነት እና ብርታት እንዲኖራቸው እና ለሰላም የዕለት ተዕለት ጥረቶችን እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል ።

"ሰላም የዕለት ተዕለት ግንባታ ነው እናንተም የሰላም ሠራተኞች ናችሁ" ብለዋል።

29 February 2024, 16:39