ፈልግ

ከኔፕልስ ሀገረ ስብከት የመጡ የዘርዓ ክህነት ተማሪዎች እና የትምህርት ቤቱ ማኅበረሰብ አባላት ከኔፕልስ ሀገረ ስብከት የመጡ የዘርዓ ክህነት ተማሪዎች እና የትምህርት ቤቱ ማኅበረሰብ አባላት  (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ቤተ ክርስቲያንን መገንባት የማያቋርጥ ሥራ እንደሆነ ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጣሊያን ከኔፕልስ ሀገረ ስብከት የመጡ የዘርዓ ክህነት ተማሪዎችን እና የትምህርት ቤቱ ማኅበረሰብ አባላትን ዓርብ የካቲት 8/2016 ዓ. ም. ጠዋት በቫቲካን ተቀብለው ንግግር አድርገውላቸዋል። ቅዱስነታቸው በዕለቱ ለአባላቱ ባደረጉት ንግግር፥ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን መንፈስ ቅዱስን እና የዘመናችንን ምልክቶች እያዳመጡ በሲኖዶሳዊነት መንፈስ አብረው የሚጓዙባት መሆኗን አስታውሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቤተ ክርስቲያን ከምንም በላይ በርካታ ሐዋርያዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎቶች በቀጣይነት የሚቀርቡባት፣ እራሷን እና ጥቅሟን ለማስጠበቅ በምታደርገው ጥረት ውስጥ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በማሸነፍ ያለማቋረጥ በጉዞ ላይ የምትገኝ እና ለመንፈሳዊ ተሃድሶ ክፍት እንደሆነችም አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህን ያስገነዘቡት በጣሊያን ኔፕልስ ሀገረ ስብከት ውስጥ ለሚገኝ እና የምሥረታውን 90ኛ ዓመት የመታሰቢያ በዓል ላከበረው የ “አሌሲዮ አስካሌሲ” የዘርዓ ክኅነት ተማሪዎች እና ለትምህርት ቤቱ ማኅበረሰብ አባላት ንግግር ባደረጉበት ወቅት ነው።

በመገንባት ላይ የምትገኝ ሲኖዶሳዊት ቤተ ክርስቲያን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቫቲካን ቅሌሜንጤዎስ አዳራሽ ውስጥ ለቡድኑ አባላት ባደረጉት ንግግር፥ ለዘመናችን ሕዝቦች የቅዱስ ወንጌልን ውበት ለማዳረስ እንዲቻል መንፈስ ቅዱስ የሚለውን እና የሕዝቦችን ጥያቄዎች ለማዳመጥ ዘላቂነት ያለው የክህነት ዝግጅት አስፈላጊነት ላይ አሰላስለዋል።

“የክኅነት ዝግጅት መቼም ቢሆን የሚያቆም እናዳልሆነ እና የዕድሜ ልክ ጥረት መሆኑን እናስታውስ” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ነገር ግን የሚያቆም ከሆነ ባለንበት ሳንቆም ወደ ኋላ እንመለሳለን ብለዋል። “በመስቀል ላይ ከተሰቀለው እና ከሞት ከተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አብራ የምትጓዝ እና መንፈስ ቅዱስን የምታዳምጥ ሲኖዶሳዊት ቤተ ክርስቲያን፥ በእያንዳንዱ ሁኔታ ውስጥ የእረኝነት አገልግሎት ስልትን እንዴት መለማመድ እንደሚገባ የሚያውቁ አገልጋዮችን ትፈልጋለች” በማለት ቅዱስነታቸው ተናግረዋል።

"ለዛሬው ውስብስብ እውነታ ነጠላ እና ቀድሞ የተዘጋጁ መልሶችን መስጠት አንችልም” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ነገር ግን ኃይላችንን አስፈላጊ የሆነውን የእግዚአብሔርን ምህረት ለሕዝቦች ለማወጅ እና ለመቀራረብ፣ በአባትነት እና በየዋህነት የማስተዋል ጥበብን ማሳደግ አለብን" ብለዋል።

ወደ ክህነት አገልግሎት የሚወስደው መንገድ

ወደ ክህነት አገልግሎት የሚወስደው መንገድም ለክኅነት የሚዘጋጁት በሙሉ እውነትን እንዲካፈሉ የተጠሩትበት እና እግዚአብሔር ለዓመታት ሥራውን እንዲያከናውን የሚፈቅዱበት ቦታ እንደሆነ ገልጸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የዘርዓ ክኅነት ተማሪዎች እግዚአብሔር በውስጣቸው እንዲሠራ ለመፍቀድ መፍራት እንደሌለባቸው ጠይቀው፥ “ለክኅነት አገልግሎት የሚዘጋጁት ግልጽ ያልሆነውን ውስጣዊ ማንነት ካጸዱ በኋላ መንፈስ ቅዱስ አዲስ ልብ ይሰጣችኋል፣ ሕይወታቸውንም እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት በማድረግ አዲስ ፍጥረት እና ሚስዮናዊ ደቀ መዛሙርት ያደርጋችኋል” ብለዋል።

“ይህ በእርግጥ ከባድ ሥራ ሊሆን ይችላል” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ነገር ግን የዘርዓ ክኅነት ተማሪዎች ጠንካሮች እና እውነተኞች፣ ለራስ ሳይሰስቱ ለመንፈስ ቅዱስ ተግባር ክፍት የሚሆኑ ከሆነ፥ በድካማቸው መካከል የእግዚአብሔር ርኅራኄ መኖሩን እና ንጹሕ የአገልግሎት ደስታን መረዳት ይችላሉ" ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የዘርዓ ክህነት ተማሪዎች ጥሪያቸውን በጥልቀት እንዲያሰላስሉት፣ እውነትን በመከተል ውስጣዊ ሕይወታቸውን እንዲኮተኩቱ፣ በእግዚአብሔር ቃል ላይ በማሰላሰል በጊዜያችን ለሚነሱ ጥያቄዎች መልስ እንዲፈልጉ፣ ሥነ-መለኮታዊ እና ሐዋርያዊ ጉዳዮችን በጥልቀት እንዲመረምሩ አበረታተዋቸዋል። ስሜትን እና የሰዎችን ብስለት በሚመለክቱ ጉዳዮች ላይ ጠንክረው እንዲሠሩ መክረው፥ ያለዚህ የትም መድረስ የማይችሉ መሆኑን ተናግረዋል።

የዘርዓ ክኅነት ትምህርት ቤቶች የክኅነት አገልግሎትን ከዘመናችን ፍላጎት ጋር ለማስማማት አዳዲስ የዝግጅት መርሃ ግብሮች የሚገኙባቸው ቦታዎች መሆናቸውን በመጥቀስ፣ አዳዲስ መርሃ ግብሮች  በእግዚአብሔር ህልውና ላይ በማሰላሰል የጸጋ እና የአገልግሎት ዕድሎች የሚገኙበት እንደሆነ ቅዱስነታቸው አስረድተዋል።

ወንድማማችነት ካኅናት ለዓለም ማቅረብ ከሚችሉት ታላቅ ምስክርነቶች አንዱ ነው።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በጣሊያን ኔፕልስ ሀገረ ስብከት ለሚገኝ ለ “አሌሲዮ አስካሌሲ” የዘርዓ ክኅነት ተማሪዎች እና ለትምህርት ቤቱ ማኅበረሰብ አባላት ያደረጉትን ንግግር ለማጠቃለል የዘንድሮውን የዓብይ ጾም መልዕክታቸውን በማስታወስ፥ አባላቱ የመለወጥ እና የመታደስ መንገድን እንዲከተሉ በማበረታታት በእግዚአብሔር ፍቅር እንዲሸነፉ፣ አስደሳች የማስታወስ ጣዕምን እንዲያውቁ፣ ድሆችን እንዲንከባከቡ፣ ፍትህን እና ፍጥረትን፣ በሰላም እና በስምምነት መኖርን፣ በወንድማማችነት መንፈስ በትህት መኖርን እንዲማሩ አደራ ብለዋል። “ወንድማማችነት በተለይ ዛሬ ለዓለማችን ከምንሰጣቸው ታላላቅ ምስክርነቶች አንዱ ነው” ሲል አፅንዖት ሰጥቷል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጨረሻም በሂደት ላይ የሚገኙ የክህነት ዝግጅት ሥራዎች አደራን ለኔፕልስ ከተማ ባልደረባ ቅዱስ ጄናሮ፣ የዘርዓ ክህነት ተማሪ ለነበረው የቁምስና ካኅን ቅዱስ ቪንቼንሶ ሮማኖ እና በዓላቸው በየዓመቱ የካቲት 8 ለሚከበረው ለብፁዕ ማሪያኖ አርቼሮ በመስጠት ንግግራቸውን ደምድመዋል።

 

 

17 February 2024, 16:21