ፈልግ

በቫቲካን የሚገኝ የሥነ-ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ አባላት በቫቲካን የሚገኝ የሥነ-ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ አባላት  (Vatican Media)

ቫቲካን በቴክኖሎጂ ዕድገት እና በሰው ልጅ ማንነት ላይ የተወያየ ጉባኤን አስተናገደች

ከመላው ዓለም የተውጣጡ ከሃያ የሚበልጡ ምሁራን በሮም ተሰብስበው የሰው ልጅ ለሳይንስ እና ለቴክኖሎጂ ዕድገት በሚሰጠው ምላሽ ላይ ተወያይተዋል። “የሰው ልጅ የማንነት ትርጉሞች እና ተግዳሮቶቹ” በሚል መሪ ርዕሥ በሮም የተዘጋጀውን ጉባኤ ያስተባበረው በቫቲካን የሥነ-ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ እንደሆነ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቫቲካን በተካሄደው ጉባኤው ላይ የተገኙት የሳይንስ፣ የፍልስፍና፣ የሃይማኖት እና የምጣኔ ሃብት ሊቃውንት፥ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዕድገት ለሰው ልጅ አገልግሎት መስጠት በሚችሉባቸው መንገዶች ላይ ተወያይተዋል። ጉባኤው ከየካቲት 4-5/2016 ዓ. ም. ድረስ የተካሄደ ሲሆን፥ ጉባኤው በርካታ የጉባኤው አዘጋጆች እና ተሳታፊዎች ጉባኤው መልካም ውጤት እንደሚኖረው ያላቸውን ተስፋ ለጋዜጠኞች ገልጸውላቸዋል።

በሰብዓዊነት ችግሮች ላይ የሚወሰድ የጋራ እርምጃ

ከጉባኤው ተሳታፊዎች መካከል አንዷ እና የለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ማሪያና ማዙካቶ፥ በአሁኑ ጊዜ የሰው ልጅ እየተጋፈጣቸው የሚገኘው ችግሮች በጋራ ጥቅም ላይ ያነጣጠሩ በመሆናቸው የጋራ ዕርምጃን እንደሚፈልጉ ለማሳየት ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ይህንን አካሄድ የሚደግፍ ምንም ዓይነት የኢኮኖሚ ሞዴል የለም ያሉት ፕሮፌሰር ማሪያና ማዙካቶ፥ የጋራ ጥቅምን የሚያስከብር ምጣኔ ሃብታዊ ሥርዓት የለም ሲሉ ተናግረዋል። እንደ ዋና የምጣኔ ሃብት ንድፈ መሠረት መንግሥታት በገበያው ላይ ችግር በሚፈጠርበት ጊዜ ብቻ ጣልቃ በመግባት አብዛኛዎቹን ጉዳዮች ለገበያው መተው አለባቸው በማለት ፕሮፌሰር ማሪያና አስረድተዋል።

ችግሮችን እና አለመስማማቶችን አስወግደን ግንኝነቶችን ለማስተካከል ብቻ ማሰብ የምንቀጥል ከሆነ በአየር ንብረት እና በብዝሃ ሕይወት ቀውስ፣ በውሃ ቀውስ እና ወደ ፊት ሊዛመቱ በሚችሉ ወረርሽኞች ላይ የምናደርገውን ጥረት ወደ ግብ ማድረስ አይቻልም” ሲሉ ፕሮፌሰር ማሪያና ተከራክረዋል።

እንደ አማራጭ አቀራረብ፥ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” እና “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” የሚሉ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳኖች የጋራ እውቀትን እና ትብብርን ለማበረታታ የሚያደርጉትን ጥሪ ፕሮፌሰር ማሪያና ደግፈዋል።

የሰው ሠራሽ አስተውሎት እና የሰው ማንነት

ቀጥሎ ጉባኤው ላይ ንግግር ያደረጉት በእንግሊዝ የሱሪ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ጂም አል ካሊሊ ሲሆኑ፥የፊዚክስ ሥነ-ትምህርት ተመራማሪ እና ሊቅ ፕሮፌሰር አል ካሊሊ ስለ ሰው ሠራሽ አስተውሎት የማሰብ ችሎታ እና የዕለት ተዕለት ሕይወታችንን ሊለውጥ የሚችልባቸውን መንገዶች እና ሰው መሆን ምን ማለት እንደሆነ ባላቸው ግንዛቤ ላይ መወያየት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

“ሰው ሠራሽ አስተውሎት ሕይወታችንን ቀላል አድርጎታል” ያሉት ፕሮፌሰር አል ካሊሊ፥ ያለ እርሱ የሰው ልጅ ሕይወት ምን እንደሚመስል በፍጥነት እስከምንረሳው ድረስ የሚወስደን እንደሆነ ገልጸው፥ ነገር ግን ከሰዎች ያነስን አላደረገንም ሲሉ አስረድተዋል።

ሰው መሆናችን ከእኛ የማሰብ ችሎታ፣ አእምሮ ወይም ፈጠራ የበለጠ ነው ሲሉ የገለጹት ፕሮፌሰር አል ካሊሊ በማከልም፥ ይህ ሁሉ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ውስጥ አንድ ቀን ሊደገም እንደሚችል አስረድተዋል። ሰው መሆናችን ከባህሪያችን እና አካላዊ አካባቢያችን ጋር ያለንን ግንኙነት የሚገልጽ፣ ውስብስብ በሆኑ የጋራ መዋቅሮች እና ማኅበረሰቦች ውስጥ እርስ በርስ ያለንን ግንኙነት፤ የጋራ ባህሎቻችንን፣ እምነቶቻችንን፣ ታሪኮቻችንን እና ትውስታዎቻችንን የሚመለከት ነው” በማለት አስረድተዋል።

ጳጳሳዊ የሥነ-ሕይወት ጥናት አካዳሚ

ጳጳሳዊ የሥነ-ሕይወት ጥናት አካዳሚ ፕሬዝደንት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቪንቼንዞ ፓሊያ እንደተናገሩት፣ አካዳሚው ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ ከመደበኛው የጥናት ዘርፍ ባሻገር በውርጃ እና በሕክምና ድጋፍ ሕይወትን ወደ ፍጻሜ ማድረስ በሚሉ ጉዳዮች ላይ የተወሰነ ትኩረት ሲሰጥ መቆየቱን ገልጸዋል። ይህ አዲስ ሃላፊነት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዘንድ በቀጥታ የመጣው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2019 ዓ. ም. “ሂውማና ኮሙኒታስ” ወይም ሰብዓዊ ማኅበረሰብ በማለት ባስተላለፉት ሐዋርያዊ መልዕክት አማካይነት እንደ ሆነ ገልጸዋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፓሊያ እንዳሉት፥ ይህ አዲሱ ትኩረት አሁን እያጋጠመን ያለውን የዘመኑ ለውጥ መጋፈጥ ማለት እንደሆነ ተናግረው፥ የሰው ልጅ ዛሬ ላይ ቢያንስ በሦስት የተለያዩ መንገዶች:- እነርሱም በአየር ንብረት ለውጥ፣ በኒውክሌር ኃይል ግንባታ እና በማደግ ላይ የሚገኙ ቴክኖሎጂዎች ሊያስከትሉ በሚችሉት አደጋዎች ላይ መወያየት እንደሚገባ እና እነዚህ ስጋቶች ጠንከር ያለ ምላሽ መስጠትን የሚጠይቅ አቅም እንዳላቸው አሳስበዋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፓሊያ ምላሽ ሊሰጥበት የሚገባው ሠነድ በማለት የጠቀሱት፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2020 ዓ. ም. “የሰው ሠራሽ አስተውሎት ሥነ ምግባር” በሚል ርዕሥ በሮም ይፋ የሆነው በዓይነቱ የመጀመሪያው የሆነው እና በሊቃውንት ተቀናጅቶ በ “ማክሮሶፍት” ፕሬዝደንት፣ በ “IBM” ምክትል ፕሬዝደንት፣ በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት ዋና ጸሐፊ እና በጣሊያን መንግሥት ተፈርሞ የጸደቀ ሠነድ እንደሆነ አስረድተዋል።

 

13 February 2024, 16:55