ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “የአስተዋይነት በጎ ምግባር ወደ ቅድስና መንገድ ይመራናል” ሲሉ አስገነዘቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ረቡዕ መጋቢት 11/2016 ዓ. ም. ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ክፍል ለመከታተል በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች ቃለ ምዕዳንን አሰምተዋል። ቅዱስነታቸው በዕለቱ ባቀረቡት አስተምህሮ፥  “የአስተዋይነት በጎ ምግባር ወደ ቅድስና መንገድ ይመራናል” ሲሉ አስገንዝበዋል። ክቡራት ክቡራን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ረቡዕ መጋቢት 11/2016 ዓ. ም. ያቀረቡትን አስተምህሮ ትርጉም ከማቅረባችን አስቀድመን ለአስተንትኖ ይሆናቸው ዘንድ የመረጡትን የሚከተለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ እናስነብባችኋለን:-

“የአዋቂ ልብ እውቀትን ይፈልጋል፥ የሰነፎች አፍ ግን በስንፍና ይሰማራል። ልብ ለሌልው ሰው ስንፍና ደስታ ናት፥ አስተዋይ ግን አካሄዱን ያቀና። ምክር ከሌለች የታሰበው ሳይሳካ ይቀራል፥ መካሮች በበዙበት ግን ይጸናል። ሰው በአፉ መልስ ደስ ይለዋል፥ ቃልም በጊዜው ምንኛ መልካም ነው! ጌታን መፍራት የጥበብ ትምህርት ነው፥ ትህትናም ክብረትን ትቀድማለች።” (መጽ. ምሳ. 15: 14፣ 21-22፣ 33) 

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ እንደምን አረፈዳችሁ! በዛሬው አስተምህሮ ከበጎ ተግባሮች መካከል አንዱ የሆነውን ‘አስተዋይነት’ እንመለከታለን። አስተዋይነት ከፍትህ፣ ከቻይነት እና ራስን ከመግዛት ጋር የሚመደብ፥ የክርስቲያኖች ብቸኛው መብት ሳይሆኑ በተለይም የግሪክ ፈላስፋዎች የጥንታዊ ጥበብ ቅርስ ከሚባሉት ዓቢይ በጎ ምግባሮች አንዱ ነው። ስለዚህ እርስ በርስ ከመገናኘት እና ከማዳበር ሥራዎች መካከል አስፈላጊ ከሆኑት ጭብጦች አንዱ ነው።

በመካከለኛው ዘመን ሥነ-ጽሑፎች ውስጥ በጎ ምግባር ከጥሩነት እና ከአወንታዊነት ባህሪያት ዝርዝር ብቻ የሚመደብ አይደለም። ወደ ጥንታዊ የግሪክ እና የሮማዊያን የሥነ-ጽሑፍ ሥራዎች ስንመለስ የነገረ-መለኮት ሊቃውንት በክርስቲያናዊ ዕይታ በመታገዝ ሰባት ዓይነት በጎ ምግባራት እንዳሉ ያስተምራሉ። እነርሱም ሦስት ነገረ-መለኮታዊ እና ሌሎች አራት ዓቢይ የሚባሉ ናቸው። እነዚህ ሰባቱ በጎ ምግባራት ሕያው እንደሆኑ እና እያንዳንዱ የራሱ ትክክለኛ ቦታ እንዳለው ይገምታሉ። እንደ ምሰሶነት፣ ዓምድነት እና ዋናነት የሚቆጠሩ እጅግ አስፈላጊ እና ሌሎች ተጨማሪ የበጎ ምግባር ዓይነቶች አሉ። በእርግጥ ምናልባት በሰው እና ቀጣይነት ባለው መልካም ምኞቱ መካከል ያለውን ግንኙነት ከመካከለኛው ዘመን ጋር በማመሳሰል መመልከቱ የተሻለ ሊሆን ይችላል።

ስለዚህ የዛሬ አስተምህሮን ‘አስተዋይነት’ ከሚለው ርዕሥ እንጀምር። አስተዋይነት እርምጃን ለመውሰድ ዘወትር የሚያመነታ የፈሪ ሰው በጎ ምግባር አይደለም። አስተዋይነትን በዚህ መንገድ የምንተረጉም ከሆነ የተሳሳተ ትርጉም እንሰጠዋለን። ለአስተዋይነት ቅድሚያ መስጠት ማለት የሰው ልጅ ተግባር በዕውቀት እና በነጻነት ውስጥ ነው ማለት ነው። አስተዋይ ሰው ብልህ ነው። አስተዋይ ሰው፥ ወንድም ይሁን ሴት ነገሮችን  ያመዛዝናል፣ ይገመግማል፣ የእውነታውን ውስብስብነት ለመረዳት ይሞክራል። በስሜቶች፣ በስንፍናዎች፣ በጫናዎች እና በቅዠቶች ለመሸነፍ ራሱን አይፈቅድም።

በመልክ፣ ተጨባጭነት በሌላቸው ሃሳቦች፣ መልካምም ሆነ መጥፎ፣ በማይረቡ ነገሮች በተሞላ ዓለም ውስጥ፣ ጥንታዊነት ያለው የአስተዋይነት ጥበብ ሊታደስ ይገባዋል።

ቅዱስ ቶማስ፣ ከአርስቶትል የማነሳሻ ሃሳብ በመነሳት አስተዋይነትን በላቲን ቋንቋ፥ ‘recta ratio agibilium’ ወይም ‘ትክክለኛው የድርጊት ሥርዓት’ ብሎታል። አስተዋይነት ወደ መልካም ነገር የሚመሩ ድርጊቶችን የመቆጣጠር አቅም ነው። በዚህ ምክንያት በጎ ምግባር በእጥፍ ይጨምራል። አስተዋይ ሰዎች ምርጫን ማድረግ የሚችሉ፣ በመጻሕፍት ውስጥ እስከተጠቀስ ድረስ ሕይወት ሁል ጊዜ ቀላል እንደሆነ፥ ነገር ግን በነፋስ እና በዕለት ተዕለት የሕይወት ማዕበል ውስጥ ሌላ ጉዳይ ይሆናል። ብዙ ጊዜ እርግጠኞች ባለመሆናችን የትኛውን መንገድ መሄድ እንዳለብን አናውቅም። አስተዋይ ሰዎች ምርጫቸውን በአጋጣሚ አያደርጉም። በመጀመሪያ የሚፈልጉትን ያውቃሉ፤ ከዚያም ሁኔታዎችን ያመዛዝናሉ፣ ምክርን ይጠይቃሉ፤ በሰፊ ዕይታ እና ውስጣዊ ነፃነት የትኛውን መንገድ መጀመር እንዳለባቸው ይመርጣሉ። ስህተት አይሠሩም ማለት አይደለም። ከሁሉም በኋላ ሁላችንም ሰዎች ነን፤ ነገር ግን አስተዋይ ሰዎች ቢያንስ ዋና ዋና መሰናክሎችን ከፊታቸው ያስወግዳሉ። አለመታደል ሆኖ ችግሮችን በቀልዶች የሚያስወግድ ወይም ውዝግብን የሚቀሰቅስ ሰው በየአካባቢው አለ። አስተዋይነት ለአስተዳዳሪነት የተጠሩት ሰዎች መለያ ነው። ማስተዳደር ከባድ መሆኑን ማወቅ፣ ብዙ አመለካከቶች እንዳሉ እና እነርሱን ለማስማማት መሞከር፣ አንዳንድ መልካም የሆኑ አመለካከቶችን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ዓይነት አመለካከቶችን አንድ ላይ ማድረግ አለበት።

አስተዋይነት ‘እጅግ መልካም ለሆነው ነገር ጠላት መሆንን ያስተምራ’ ይላሉ። በእርግጥም በአንዳንድ ሁኔታዎች ከልክ ያለፈ ቅንዓት አደጋ ሊያስከትል ይችላል። እርጋታ እንዲኖር የሚፈልገውን ግንባታ ሊያበላሽ ይችላል። ግጭቶችን እና አለመግባባቶችን ሊያስከትል ይችላል። አልፎ ተርፎም ብጥብጥ ሊያስነሳ ይችላል።

አስተዋይ ሰው ያለፈው ትዝታ ሳይጠፋ እንዴት ማቆየት እንዳለበት ያውቃል። ይህን የሚያደርገው  ለመጭው ጊዜ በመፍራት ሳይሆን ትውፊት የጥበብ አባት መሆኑን ስለሚያውቅ ነው። ሕይወት በማያቋርጥ ያለፉትን እና አዳዲስ ነገሮችን ደራርቦ ያቀፈ ነው። ስለዚህ ዓለም በእኛ ይጀምራል ብሎ ዘወትር ማሰብ ጥሩ አይደለም። ከመነሻው ጀምሮ ችግሮችን መቋቋም አለብን። አስተዋይ ሰው ደግሞ ወደ ፊት የሚሆነውን  የሚያውቅ ነው። አንድ ሰው ወደ ግብ ለመድረስ ከወሰነ፥ ወደዚያ ግብ ለመድረስ የሚያስችሉ ሁሉ  መንገዶችን ማግኘት አስፈላጊ ነው።

ስለ አስተዋይነት የሚያስተምሩ ብዙ የወንጌል ክፍሎች አሉ። ለምሳሌ፡- ‘ቃሌን ሰምቶ የሚያደርገው ሁሉ ቤቱን በዓለት ላይ የሠርራ ጥቢብ ሰውን ይመስላል። ቃሌን ሰምቶ የማያደርግ ሁሉ ቤቱን በአሸዋ ላይ የሠራ ሰነፍ ሰውን ይመስላል። ዝናብ ዘነበ፥ ጎርፍም ጎረፈ፥ ነፋስም ነፈሰ ያንንም ቤት መታው፤ ወደቀም፤ አወዳደቁም ታላቅ ሆነ’ (ማቴ. 7፤ 24 ፣ 27)። ከመብራታቸው ጋር ዘይት ይዘው የወጡት ደናግል ጥበበኞች ሲሆኑ፥ ለመብራታቸው የሚሆን ዘይት ሳይዙ የውጡት ሰነፎች ናቸው (ማቴ. 25: 1-13)።

የክርስትና ሕይወት የትሁትነት እና የብልህነት ጥምረት ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ለተልዕኮ ሲያዘጋጅ እንዲህ ሲል ይመክራል፡- ‘እነሆ እንደ በጎች በተኵላዎች መካከል እልካችኋለሁ። እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብም የዋሆች ሁኑ’ (ማቴ 10:16)። እግዚአብሔር ቅዱሳን እንድንሆን ብቻ አይፈልግም ለማለት ሳይሆን አስተዋይ ቅዱሳን እንድንሆንም ይፈልጋል። ምክንያቱም ካለማስተዋል የተነሳ በተሳሳተ መንገድ መጓዝ ስህተት ነውና!”

 

 

20 March 2024, 13:03