ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በዕድሜ ምክንያት የሚመጣውን አቅመ ደካማነት በጸጋ መቀበል እንደሚገባ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “የመልካም አቀባበል መንበር” በሚል ርዕሥ ዙሪያ “ተጋላጭነትን፣መልካም የማኅበረሰብ አቀባበልን እና አካታችነትን በማስመልከት በተጋጀው ጉባኤ ላይ ለተካፈሉት አባላት ባደረጉት ንግግር፥ የጉባኤው መርሃ ግብር ብዙ ሃብት ያለው እና አስደሳች እንደሆንም ገልጸው፥ በጉባኤው ላይ ተጋላጭነት በሁሉም ዓይነት አቅጣጫ ውይይት የተካሄደበት እንደ ነበር ተናግረው፥ የወንጌል ተልዕኮ ባለው በዚህ ርዕሥ ላይ አንዳንድ የአስተንትኖ ነጥቦችን ከማቅረባቸው በፊት ለርዕሡ ምርጫ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
ተጋላጭነት በኢየሱስ ተቀባይነትን ስለ ማግኘቱ
የመጀመሪያ ርዕሥ ወንድሞቼ እና እህቶቶቼ ሆይ! ተጋላጭነትን በጸጋ ለመቀበል አቅመ ደካማነታችን ሊሰማን እና በኢየሱስ ክርስቶስም ተቀባይነት እንዳለን መገንዘብ ይገባል ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “የወይኑ ቅርንጫፎች በግንዱ ላይ እንደሚደገፉ ሁሉ እኛም በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ብንሆን መልካም ፍሬን ልናፈራ እና ሰፊ ተቀባይነትን ልናገኝ እንችላለን ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመቀጠልም ሁለተኛው ፍንጭ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ አብዛኛውን የአደባባይ አገልግሎቱን በተለይም በገሊላ ከድሆች እና ሁሉም ዓይነት በሽታ ካላቸው ሰዎች ጋር በመገናኘት ያሳለፈ መሆኑን አስታውሰው፥ "ይህ የሚነግረን ተጋላጭነት በፖለቲካዊው አስተሳሰብ ትክክል ባይሆንም ወይም ተራ የተግባር አደረጃጀት ጉዳይ ቢሆንም ጥሩ ሊሆን እንደሚችል አስረድተዋል።
በወንጌል መሠረት ላይ መቆም
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጉባኤው ተካፋዮች፥ ደቀ መዛሙርቱ የታመሙትን እና ድሆችን ለመንከባከብ የሚያስችል በቂ ትምህርት ከኢየሱስ ክርስቶስ ባይሰጣቸውም ነገር ግን በእርሱ እንደ ተመኩ ሁሉ በቅዱስ ወንጌል ጸንተው እንዲቆዩ” ጋብዘዋል። መንፈስ ቅዱስ ቅዱሳን ወንዶችንና ሴቶችን የሚያዘጋጀው በዚህ ዓይነት መንገድ እንደሆነ እና እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ እነርሱም አቅመ ደካሞችን እንደሚወዱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ገልጸዋል።
ሦስተኛው እና የመጨረሻው የማስተንተኛ ሃሳብ፥ በቅዱስ ወንጌል ውስጥ የተጠቀሱት ድሆች እና አቅመ ደካሞች ግዙፍ ዕቃ ሳይሆኑ ነገር ግን በእግዚአብሔር መንግሥት ብሥራት ውስጥ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ዋና ተዋናዮች መናቸውን አስረድተዋል። የቅዱስ ወንጌል ታሪክ በመጥቀስ እንድናስብበት የጋበዙን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “በሰባት አጋንንት ሰቃይ የደረሰባት መግደላዊት ማርያም ከሙታን የተነሳው የኢየሱስ ክርስቶስ የመጀመሪያ ምስክር እንደሆነች አስታውሰዋል።
በተልዕኮ ወደፊት መጓዝ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ፥ “ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የተገናኙት እና የእርሱን ጸጋ እና የሕይወት ዘይቤውን የተቀበሉት ተጋላጭ እና አቅመ ደካማ የሆኑ ሰዎች በአማኞች እና በመላው ማኅበረሰብ መካከል ሕያው ወንጌል ሆነው ሊገኙ እንደሚችሉ አስረድተዋል።
ቅዱስነታቸው በመጨረሻም፥ ውድ ወንድሞች እና እህቶች ዘወትር በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ታጅበው በተልዕኮአቸው ወደፊት እንዲጓዙ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።