ፈልግ

Pope Francis hears a confession during a meeting with the clergy of Rome at the Basilica of St. John in Lateran in Rome Pope Francis hears a confession during a meeting with the clergy of Rome at the Basilica of St. John in Lateran in Rome 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “ለእግዚአብሔር 24 ሰዓት እንስጥ” የሚል የጸሎት ዝግጅት እንደሚመሩ ተገለጸ

በዓብይ ጾም ወቅት በሚቀርብ የጸሎት እና የይቅርታ ዝግጅት ላይ የዓለም ምዕመናን እንዲሳተፉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጋበዙ ሲሆን፥ “24 ሰዓት ለእግዚአብሔር እንስጥ” በሚል መሪ ሃሳብ ለአሥራ አንደኛ ጊዜ የተዘጋጀው የጸሎት መርሃ ግብር በሮም በሚገኝ በቅዱስ ፒዮስ አምስተኛ ቁምስና ውስጥ እንደሚካሄድ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የፊታችን ዓርብ የካቲት 29/2016 ዓ. ም የሚካሄደውን መርሃ ግብር በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዛሬ ሰኞ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።

የላቲን ሥርዓተ አምልኮን በመትከተል ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ በዐቢይ ጾም አራተኛው እሑድ ዋዜማ ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ በየአገራቱ ሀገረ ስብከቶች ዘንድ የሚቀርበውን የጸሎት እና የዕርቅ ዝግጅት ውጥን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ የቤተ ክርስቲያን መሪነት ሥልጣን በተቀበሉበት ወቅት ማስጀመራቸው ይታወሳል።

ዘንድሮ ለ11ኛ ጊዜ የተዘጋጀው ሥነ-ሥርዓት ከዓርብ የካቲት 29 እስከ ቅዳሜ የካቲት 30/2016 ዓ. ም. ድረስ የሚቆይ ሲሆን፥ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ሮሜ ሰዎች በላከው መልዕክት ምዕራፍ 6 ላይ፥ “በአዲስ ሕይወት መመላለስ” የሚለውን ጥቅስ መሪ ያደረገ እንደሆነ ታውቋል።

መጭው ዓርብ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር የሚከበረው ዝግጅቱ በኢትዮጵያ የሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 12፡30 ላይ በሮም በሚገኝ በቅዱስ ፒዮስ አምስተኛ ቁምስና ውስጥ እንደሚጀመር መግለጫው አስታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የምዕመናን ንስሐ አድምጠው ከእግዚአብሔር ዘንድ የኃጢአት ይቅር እንደሚለምኑ ታውቋል።

ቤተ ክርስቲያናትን ክፍት የማድረግ ልዩ ዝግጅት

ለብርሃነ ትንሳኤው በዓል ዝግጅት በሚደረግበት መጭው ዓርብ ምሽት እና ሙሉ ቅዳሜ፥ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ካቶሊካዊ ቁምስናዎች ቤተ ክርስቲያናቸውን ክፍት እንዲያደርጉ ተጠይቀዋል። ይህም ምእመናን በማንኛውም ጊዜ መናዘዝ እና መስገድ እንዲችሉ ዕድል ለመስጠት መሆኑ ተነግሯል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በሮማ ውስጥ በመረጡት ቁምስና ውስጥ የምዕመናንን ተሳትፎ ለማበረታታት “24 ሰዓት ለጌታ እንስጥ” በሚል ሃሳብ የሚዘጋጀውን መርሃ ግብር ለመምራት መወሰናቸው ይታወቃል።

ለመርሃ ግብሩ እንዴት መዘጋጀት ይቻላል?

በጣሊያን እና በመላው ዓለም ውስጥ የሚገኙ ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቶች እና ቁምስናዎች በሙሉ በየአካባቢያቸው የጸሎት እና የይቅርታ መርሃ ግብሩን እንዲያከብሩ በማለት በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዛሬ ሰኞ በሰጠው መግለጫ ጥሪውን በድጋሚ አቅርቧል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅርቡ ያወጁትን የጸሎት ዓመት በማስመልከት ዘንድሮ ለሚከበረውን ዝግጅት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቱ አንዳንድ ሐዋርያዊ ድጋፎችን በማድረግ ምዕመናን የግል ጸሎታቸውን እንዲያቀርቡ እና በጋራ በዓላት ላይ እንዲሳተፉ የሚያስችላቸውን ሐዋርያዊ ድጋፎች ማድረጉ ታውቋል። በዚህ መሠረትም በእንግሊዝኛ፣ በጣሊያንኛ፣ በስፔን፣ በፖርቱጋል፣ በፖላንድ እና በፈረንሳይኛ ቋንቋዎች የተዘጋጁ ጸሎቶችን በድረ-ገጹ በኩል ይፋ ማድረጉ ታውቋል።

 

 

04 March 2024, 17:09