ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ክርስቲያኖች በሰው ልጆች ላይ የኢየሱስን ቁስል እንዲመለከቱ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ቅዱስነታቸው ለፍራንችስካውያን ወንድሞች ባስተላለፉት መልዕክት፥ ይቅርታን እና ፈውስን የተሸከሙ፣ በወንድማማችነት እና በደስታ ቀለል ያለ ሕይወት የሚኖሩ እንዲሆኑ፥ ሁሉም ከክርስቶስ ጎን በሚፈስ እና ከእርሱ ጋር በሚያደርጉት የግል ግንኙነት የፍቅር ጥንካሬን የሚያገኙ እንዲሆኑ አሳስበዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለፍራንችስካውያኑ ይህን የማበረታቻ መልዕክት ያስተላለፉት፥ የማኅበራቸው መሥራች የአሲሲው ቅዱስ ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያን በመስከረም 17/1224 ዓ. ም. የኢየሱስን ቁስል የተቀበለበት ስምንት መቶኛ ዓመት ለማክበር ከማዕከላዊ ጣሊያን ላ ቬርና ከተማ እና ከቶስካና ግዛት የመጡትን የማኅበሩ አባላት በቫቲካን በተቀበሉ ጊዜ ሲሆን፥ ማኅበርተኞቹ የቅዱስ ፍራንቸስኮን ደም ቅዱስ ቅርስ ስላመጡላቸውም ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።
ወደ ቆሰለው ዓለም የእግዚአብሔርን ፍቅር ማምጣት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለማኅበሩ አባላት ባሰሙት ንግግር፥ ክርስቲያኖች ድሃ እና ለእኛ ሲል የተሰቀለውን ኢየሱስን መምሰል እንደሚገባ አሳስበዋል። የአሲሲው ቅዱስ ፍራንችስኮስ በስጋው የተቀበለው የኢየሱስ ክርስቶስ ቁስሎች ለእኛ ሲል የተቀበለው መከራ እና በሞት ላይ ያደረገው ድል አስደናቂ ምልክት እንደሆነ አስረድተው፥ “በተሰቀለው እና ከሙታን የተነሳው የኢየሱስ ክርስቶስ ምሕረት ወደ እኛ የሚፈሰው በቁስሎቹ በኩል ነው” ሲሉ አስገንዝበዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው፥ እያንዳንዱ ክርስቲያን የሚያገኟቸው የቆሰሉ ሰዎች መከራ እና የፍትሕ መጓደል ያጋጠማቸው በመሆናቸው እነዚህን ሰዎች የመንከባከብ ግዴታ እንዳለብን ጠቁመዋል። “በቤተ ክርስቲያን የፍቅር ህብረት ውስጥ እያንዳንዳችን ማን እንደሆንን እንደገና ለማወቅ፥ ይህን በማድረጋችን በእግዚአብሔር የተወደድን፣ የተባረክን፣ የታረቅን፣ ድንቅ ጸጋውን ለመመስከር እና ወንድማማችነትን ለማሳደግ የተላክን ነን” ሲሉ ተናግረዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማከልም፥ ቅዱስ ፍራንችስኮስ የመንገዳችን አጋር በመሆን ችግሮችን እና ፍርሃቶችን እንድናሸንፍ አግዞናል ብለው፥ የመንፈስ ቅዱስ ጥማቱም ለእግዚአብሔር፣ ለወንድሞቹ እና ለእህቶቹ ፍላጎት እራሱን ክፍት እንዲያደርግ እና ዘወትር በእግዚአብሔር ፍቅር እንዲታመን አድርጎታል ብለዋል።
የእግዚአብሔርን ይቅርታ ለሌሎች መስጠት
በእያንዳንዱ ፍራንችስካዊ ሕይወት ውስጥ በሚታየው የቁስል ምልክት ላይ ያሰላሰሉት ቅዱስነታቸው፥ ፍራንቸስኮውያን በመካከላቸው አንድነት እንዲኖራቸው እና ቤተ ክርስቲያንን "ለመጠገን" እንደ ተልዕኳቸው አካል ዘወትር ይቅር መባባል አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል። “እናንተ ጥሩ አናዛዦች ናችሁ” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ፍራንችስካውያን በዚህ አገልግሎት ጥሩ ስም እንዳላቸው ገልጸው፥ ሁሉን ነገር ዘወትር ይቅር እንዲሉ፥ እኛ እግዚአብሔርን ይቅርታ መጠየቅ ቢሰለቸንም እርሱ ግን ይቅር ሊለን የማይታክተው መሆኑን አስረድተዋል።
የቅዱስ ፍራንችስኮስ ቁስል የኢየሱስ ክርስቶስ ተልዕኮ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለውን ማዕከላዊነት የሚያሳይ እንደሆነ ተናግው፥ እንዲሁም ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ በመስቀል ላይ እንዲሞት የገፋፋውን ያንን ታላቅ ፍቅር ወደ ቤተ ክርስቲያን እና ወደ ዓለም እንዲያመጡ በማለት ገዳማውያኑን አሳስበዋል።
የአሲዚ የቅዱስ ፍራንችስኮስ ጸጋዎች
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በንግግራቸው ማጠቃለያ፥ የፍራንችስኮስውያን የምንኩስና አልባስ ሰዎች ስለ ቅዱስ ፍራንችስኮስ እና እርሱ የተቀበላቸውን ጸጋዎች እንዲያስታውሱ የሚያደርግ መሆኑንም አስረድተዋል።
ወደ አሲሲው ቅዱስ ፍራንችስኮስ የሚቀርብ አዲስ ጸሎት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የአሲሲው ቅዱስ ፍራንችስኮስን አማላጅነት ለመጠየቅ በቬርና ከተማ በሚገኝ የቅዱስ ፍራንችስኮስ ቅንዋት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዲቀርብ የጻፉትን አዲስ ጸሎት በመድገም እንግዶችን ሸኝተዋቸዋል።
በፍቅር የቆሰልክ፣ በሥጋ እና በመንፈስ የተሰቀልክ፣ በቁስሎች ያጌጥክ ቅዱስ ፍራንችስኮስ ሆይ! ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን፣ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን በፍቅርህ እና በፍላጎት እንዴት መውደድ እንዳለብን ለመማር ወደ አንተ ቀርበናል። ከአንተ ጋር ስንሆን ድሃውን እና የተሰቀለውን ኢየሱስን ማሰላሰል እና መከተል እንችላለን።
ቅዱስ ፍራንችስኮስ ሆይ! የእምነትህን አዲስነት፣ የተስፋህን እርግጠኛነት፣ የበጎ አድራጎትህን ገርነትን ስጠን። በፈተናዎች መካከል መጽናትን እንድንለማመድ፣ የእግዚአብሔርን ርህራሄ እና የመንፈስ ማስታገሻ እንዲሆንልን፣ የሕይወት ሸክማችን ጣፋጭ እንዲሆንልን ለእኛ አማልድልን።
እንደ አንተ የምሕረት ምስክሮች ለመሆን እና ሕይወትን ለማደስ ዘወትር በቅንነት ለምንፈልግ በሙሉ ቁስላችንን የኢየሱስ ክርስቶስ ልብ ይፈውሰው።
ቅዱስ ፍራንችስኮስ ሆይ! የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድንመስል አድርገን። ቁስልህ ለእኛ እና ለዓለም የሕይወት እና የትንሳኤ፣ አዲስ የሰላም እና የእርቅ መንገዶችን የሚያሳይ ምልክት ይሁንልን። አሜን።