ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጪው መስከረም ወር የእስያ እና ኦሺኒያ 4 ሀገራትን ይጎበኛሉ።
የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጪው መስከረም ወር መጀመሪያ ላይ በኤዥያ የሚገኙ ሦስት አገሮችን እና አንድ በኦሽንያ አህጉር የሚገኝ አገር እንደሚጎበኙ የቅድስት መንበር የዜናና ኅትመት ክፍል አስታውቋል።
የመጪውን ከጣሊያን ውጪ ቅዱስነታቸው የሚያደርጉትን 45ኛውን ሐዋርያዊ ጉዟቸውን እንዲያካሂዱ የሀገር መሪዎች እና የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ባለስልጣናት ያቀረቡትን ጥሪ ቅዱስነታቸው ተቀብለዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እ.አ.አ በመጪው መከረም 2/2024 ዓ.ም ከሮም ተነስተው መስከረም 13/2024 ዓ.ም ወደ ሮም እንደሚመለሱ ተገልጿል። መጀመሪያ ወደ የኢንዶኔዢያ ዋና ከተማ ጃካርታ ይጓዛሉ፣ እዚያም እ.አ.አ በመስከረም 3/2024 ዓ.ም ይደርሳሉ ተብሎ የሚተበቅ ሲሆን በእዚያው እ.አ.አ እስከ መስከረም 6/2024 ዓ.ም ድረስ እንደሚቆዩም ተገልጿል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የፓፑዋ ኒው ጊኒ ዋና ከተማ ፖርት ሞርስቢን እና ቫኒሞን እ.አ.አ ከመስከረም 6 እስከ መከረም 9/2024 ዓ.ም ድረስ ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ ወደ ምስራቅ ኢሲያ አህጉር ይጓዛሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከእዚያም ቀጥሎ ቅዱስነታቸው የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ወደ ዲሊ በቲሞር-ሌስቴ ዋና ከተማ እንደ ሆነ ከተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን በእዚያም እ.አ.አ ከመስከረም 9 እስከ መስከረም 11/2024 ቆይታ እንደሚኖራቸው ተገልጿል።
ከዚያ በመቀጠል የቅዱስነታቸው ከጣሊያን ውጪ የሚያደርጉት የ45ኛው ሐዋርያዊ ጉብኝት መዳረሻ ሲንጋፖር ሲሆን ይህም የሚከናወነው እ.አ.አ ከመጪው መስከረም 11 እስከ 13/2024 ዓ.ም እንደ ሚሆን ተገልጿል። የቅድስት መንበር የዜና ማሰራጫ ጽ/ቤት እንዳስታወቀው፣ የሐዋርያዊ ጉዞው ሙሉ መርሃ ግብር በቀጣይ ቀናት ይፋ እንደሚሆን አስታውቋል።
የቀጠናው የካቶሊክ ምዕመናን ብዛት
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጀመሪያ እ.አ.አ በታህሳስ ወር 2023 ዓ.ም ገደማ ወደ ክልሉ የመጓዝ እድል እንዳላቸው መጥቀሳቸው የሚታወስ ሲሆን ከሜክሲኮ ብሮድካስት N+ ጋር በተደረገ ቃለ ምልልስ እ.አ.አ በነሐሴ ወር ወደ "ፖሊኔዥያ" (በኦሺኒያ አህጉር ውስጥ የሚገኙ በርካታ ደሴቶች) እና ወደ ትውልድ አገራቸው አርጀንቲና ለመጓዝ ተስፋ እንዳላቸው መናገራቸው ይታወሳል።
ከዚያም በመቀጠል እ.አ.አ በጥር 2024፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ቲሞር-ሌስቴን፣ ፓፑዋ ኒው ጊኒን፣ እና ኢንዶኔዢያን እንደሚጎበኙ ከጣሊያኑ ጋዜጣ ላ ስታምፓ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ መግለጻቸው የሚታወስ ሲሆን ኢንዶኔዥያ ከዓለም ትልቁ የሙስሊም እመነት ተከታዮችን የያዘች አገር ስትሆን ካቶሊኮች ከ8 ሚሊዮን በላይ ማለትም ከህዝቡ ጠቅላላ ቁጥር አንጻር ሲታይ 3.1 በመቶ በላይ ናቸው።
ከፓፑዋ ኒው ጊኒ ነዋሪዎች 32 በመቶው ካቶሊኮች ሲሆኑ ቁጥራቸውም ወደ 2 ሚሊዮን ይደርሳል።
የቲሞር-ሌስቴ ሕዝብ በአብዛኛው የካቶሊክ እምነት ተከታይ ነው፣ ወደ 96 ከመቶ የሚሆነው ህዝብ የእመነቱ ተከታይ ሲሆን ከ1 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን አቅፎ የያዘ እንደሆነም ተገልጿል።
ወደ 395,000 የሚጠጉ ካቶሊኮች በሲንጋፖር ውስጥ ይኖራሉ፣ ይህም ከህዝቡ 3 በመቶውን ይወክላል።