ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ከመስፋፋቱ አስቀድሞ እንዲቆም ተማጸኑ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የረመዳን ጾም መገባደጃን በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት፥ በእስራኤል እና በፍልስጤም መካከል እየተካሄደ ባለው ጦርነት እንዲሁም በሶርያ፣ በሊባኖስ እና በአካባቢው ባለው ሁከት እና ብጥብጥ መጨነቃቸውን ገልጸው፥ ጦርነት ዘወትር ሽንፈትን እንጂ የትም የማያደርስ አደገኛ መንገድ እና ተስፋን በሙሉ የሚያጨናግፍ እንደሆነ ያላቸውን እምነት በመድጋሚ ገልጸዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሚያዝያ 4/2016 ዓ. ም. በአል አረቢያ ዓለም አቀፍ የአረብ ዜና ቴሌቪዥን ጣቢያ አማካይነት ለመላው የሙስሊም ማኅበረሰብ ወንድሞች እና እህቶች የላኩት የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት፥ በአሁኑ ጊዜ በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ውስጥ እየፈሰሰ ባለው ደም ከተሰማቸው ሐዘን ጋር እንደሆነ ታውቋል።
ዘንድሮ የረመዳን ወር የተገባደደው የብርሃነ ትንሳኤው በዓል ከተከበረ ከጥቂት ቀናት በኋላ ሲሆን፥ ሁለቱም በዓላት ምዕመናን ዓይኖቻቸውን ወደ ሰማይ እንዲያነሱ እና መሐሪ እና ሁሉን ቻይ የሆነውን ጌታ በኅብረት እንዲያመልኩት ማድረጉ ተመልክቷል።
የሰላም አምላክ ሰላንም ይፈልጋል
እግዚአብሔር የሰላም አምላክ ሰላምን እንደሚፈልግ፣ በእርሱ የሚያምኑት ጦርነት መካድ እንደማይሳናቸው፣ ጦርነት ጠብን የሚጨምር እንጂ መፍትሄን ያማያመጣ፣ አዲስ ዕይታ እንዲከፈት የማያደርግ እና ተስፋን በሙሉ የሚያጨናግፍ እንደሆነ ገልጸዋል።
በፍልስጤም እና በእስራኤል መካከል በተፈጠረው ግጭት የተሰማቸውን ሐዘን የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ በጋዛ ሰርጥ ፈጣን የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ጥሪያቸውን በድጋሚ አቅርበው፥ በአካባቢው ሰብዓዊ እልቂት እየተከሰተ መሆኑንም ተናግረዋል።
ከዚህም ጋር በማያያዝ በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ ለሚገኝ የፍልስጤም ሕዝብ ዕርዳታን ማድረስ እንዲፈቀድለት እና በመስከረም ወር መጨረሻ አካባቢ በሐማስ ታጣቂዎች ታግተው የተወሰዱትም ይፈቱ ዘንድ ጠይቀዋል።
ለመላው የመካከለኛው ምሥራቅ ጥሪ አቅርበዋል
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጦርነት የተመሰቃቀሉትን ሶርያን፣ ሊባኖስን እና መላውን የመካከለኛው ምሥራቅ አገራትን ባስታወሱበት መልዕክታቸው፥ በጦር መሣሪያ እሽቅድምድም እና በቂም በቀል ነበልባል ምክንያት ጦርነት እንዲስፋፋ መፍቀድ እንደማይገባ አደራ ብለው፥ የክፋትን ኃይል ማስወገድ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ጦርነት ባሉባቸው አገራት ውስጥ የሚኖሩ ቤተሰቦችን፣ ወጣቶችን፣ ሠራተኞችን፣ አረጋውያን እና ሕፃናት ዘወትር እንደሚያስቧቸው የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በተራ ሕዝብ ልብ ውስጥ ታላቅ የሰላም ፍላጎት እንዳለ እርግጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የአገራቱ ሕዝቦች በመስፋፋት ላይ በሚገኘው ጦርነት ምክንያት በእንባ “ጦርነት ይብቃ!” በማለት ድምጽ በማሰማት ላይ እንደሚገኙ እና እርሳቸውም ይህን ድምጽ ከፍተኛ ኃላፊነትን ለተሸከሙት የመንግሥታት መሪዎች በድጋሚ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል።“ግጭቶችን እና ጦርነቶችን አቁማችሁ በከንቱ የሚሞቱ ንጹሃን ልጆችን እንደ ልጆቻችሁ አስቡ” በማለት የተማጸኑት ቅዱስነታቸው፥ መጪውን ጊዜ ጠላትን ከወዳጅ መለየት በማይችል የሕፃናት ዓይን እንዲመለከቱ አሳስበዋል። በማከልም ለሕጻናት የሚያስፈልጋቸው መኖሪያ ቤቶች፣ መናፈሻዎች እና ትምህርት ቤቶች እንጂ የጅምላ መቃብር እንዳልሆነም ተናግረዋል።
ማንኛውም ሕዝብ የራሱን መንግሥት የማግኘት መብት አለው
በተስፋ ቃል መልዕክታቸውን የደመድሙት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስበ፥ በረሃው እንደሚያብብ ሁሉ የሰዎች ልብ እና የአገራት ሕይወትም እንዲሁ እንዲያብብ ተመኝተው፥ መካከለኛው ምሥራቅ የጥላቻ አካባቢ ከመሆን ይልቅ የተስፋ ቡቃያዎች የሚያድጉበት እና ይህ ሊሆን የሚችለው አንዱ ከሌላው ጋር እንዴት ማደግ እንዳለበት ከተማረ ብቻ እንደሆነ አስረድተዋል። የሌሎችን እምነት ማክበርን ከተማርን፣ የእያንዳንዱን ሕዝብ የመኖር መብትን እና ማንኛውም ሕዝብ የራሱ መንግሥት የማግኘት መብትን ከተገነዘብን ብቻ እንደሆነ አስረድተዋል።
በመጨረሻም በመካከለኛው ምሥራቅ በችግሮች ውስጥ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች ባስተላለፉት መልዕክት፥ስለ ሰላም ስለ ወንድማማችነት የሚያስተምረውን እምነታቸውን ዘወትር በሁሉም ሥፍራ በነፃነት የመግለጽ መብት እና ብቃት እንዳላቸው በመናገር መልዕክታቸውን ደምድመዋል።