ር.ሊ.ጳ ፍራንችስኮስ ትህትና ለክርስቲያናዊ ሕይወት መሰረታዊ ነገር እና ለዓለም ሰላም ምንጭ ነው አሉ
የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን
በእለቱ የተነበበው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል
“ማርያምም እንዲህ አለች፤ “ነፍሴ ጌታን ከፍ ከፍ ታደርገዋለች፤ መንፈሴም በመድኀኒቴ በእግዚአብሔር ደስ ትሰኛለች፤ እርሱ የባሪያውን መዋረድ ተመልክቷልና። ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል” (ሉቃስ 1፡46-48)።
ክቡራት እና ክቡራን የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ረቡዕ በግንቦት 14/2016 ዓ.ም ያደረጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ትርጉሙን እንደሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከታተሉን...
የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!
ከሰባቱ መሰረታዊ ወይም ዐምደ ምግባራት እና መንፈሳዊ ምግባራት (ዐምደ ምግባራት የሚባሉት ዐራት ናቸው እነርሱም ‘ማስተዋል-ጥንቃቄ፣ ፍትሕ፣ ጽናት እና ትዕግስ፥ ሦስቱ መንፈሳዊ ምግባራት የሚባሉት ደግሞ ‘እምነት፣ ተስፋ እና ፍቅር) ውስጥ የማይመደበውብ ነገር ግን ለክርስቲያናዊ ሕይወት መሠረት የሆነውን ትሕትናን በመመልከት ይህንን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ዑደት እናጠቃልላለን። የታላቁ ኃጢያት ዋና ተቃዋሚ ነው፣ ማለትም የእብሪተኝነት መንፈስ ተቃዋሚ ነው። ትዕቢትና እብሪት የሰውን ልብ ስያሳብጡ፣ ከእኛ ከሆነው በላይ እደሆንን እንዲሰማን ሲያደርጉን፣ ትሕትና ግን ሁሉን ነገር ወደ ትክክለኛው ልኬቱ ይመልሳል፡ እኛ ድንቅ ፍጥረታት ነን፣ ነገር ግን ውስን ነን፣ ባሕርያትና ጉድለቶች አሉን። ገና ከመጀመሪያው፣ መጽሐፍ ቅዱስ አፈር መሆናችንን ያስታውሰናል፣ ወደ አፈርም እንመለሳለን (ዘፍ. 3፡19)። በእርግጥም “ትሑት” የሚለው ቃል የሚመነጨው “humus” ከሚለው የላቲን ቋንቋ ቃል ሲሆን እርሱም መሬት፣ አፈር ወይም ምድር የሚለውን ትርጉም ይሰጠናል። እናም አሁንም በጣም አደገኛ የሆነው ኃያልነት ቅዤት ማታለል ብዙውን ጊዜ በሰው ልብ ውስጥ ይነሳል!
ሁሉንም በትህትና መመለስ
እራሳችንን ከትዕቢት ጋኔን ነፃ ለማውጣት በጣም ትንሽ ጉልበት ነው የሚወስደው፣ መዝሙረ ዳዊት እንደሚለው በከዋክብት የተሞላውን ሰማይ ማሰቡ በቂ ነው፡- “የጣቶችህን ሥራ፣ ሰማያትህን ስመለከት፣ በስፍራቸው ያኖርሃቸውን፣ ጨረቃንና ከዋክብትን ሳይ፣ በዐሳብህ ስፍራ ትሰጠው ዘንድ ሰው ምንድን ነው? ትጠነቀቅለትም ዘንድ የሰው ልጅ ምንድን ነው? (መዝሙር 8፡3-4)። እናም ዘመናዊ ሳይንስ አድማሱን በብዙ እና በበለጠ ሁኔታ ለአድማሳችን ያለን ግንዛቤ እና በዙሪያችን ያለውን እና የምንኖርበትን ምስጢር እንድንሰማ ያስችለናል።
ከትምክህተኝነት መላቀቅ
ይህን የራሳቸው ትንሽነት ግንዛቤ በልባቸው የያዙ ብፁዓን ናቸው፡ ከትዕቢት ተጠብቀዋል። ኢየሱስ ስለብጽዕና ባስተማረው የተራራ ላይ ስብከት ኢየሱስ በትክክል ከእርሱ ይጀምራል፡- “በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው፣ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና” (ማቴ 5፡3)። ስለብጽዕና የተሰጠው የመጀመርያው ስብከት የሚጀምረው ከትህትና ነው፥ ምክንያቱም ከእዚያን ቀጥሎ የሚመጡት በሙሉ መሰረታቸውን የሚያደርጉት በእርሷ ላይ ነው፣ በእርግጥም የዋህነት፣ ምህረት እና የልብ ንፅህና የሚመነጨው ከዚያ ውስጣዊ የትንሽነት ስሜት ነው። ትህትና የጥሩነት ሁሉ መግቢያ በር ነው።
የኢየሱስንና የማርያምን ምሳሌ መከተል
በወንጌል የመጀመሪያ ገጾች ላይ ትህትና እና የመንፈስ ድህነት የሁሉም ነገር ምንጭ ይመስላል። የመልአኩ ገብርኤል ብሥራት የተነገረው በኢየሩሳሌም ደጃፍ ሳይሆን በገሊላ በምትገኝ ራቅ ባለ መንደር ነበር፤ ስለዚህም ሰዎች “ከናዝሬት መልካም ነገር ሊወጣ ይችላልን?” እስኪሉ ድረስ እዚህ ግባ የሚባል ነገር አልነበረም። ( ዮሐ 1:46 ) ነገር ግን ዓለም እንደገና የተወለደችው በትክክል ከዚያ ነው። የተመረጠችው ጀግና ሴት ተሞላቃ ያደገች ትንሽ ንግሥት አይደለችም፣ ነገር ግን በሰዎች ዘንድ ያልታወቀች ልጅ: ማርያም ነበረች። መልአኩ የአምላክን ብሥራት ሲያመጣ የተደነቀችው እሷ ራሷ ነች። በጸሎትዋ ዝማሬ፣ የማርያም የውዳሴ መዝሙር ውስጥ በእውነትም ይህ አስደናቂ ነገር ነው፡- “ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች፣ የባሪያይቱን ውርደት ተመልክቶአልና” (ሉቃ 1፡ 46-48)። እግዚአብሔር - ለማለት ይቻላል - በማርያም ትንሽነት ይሳባል፣ ይህም ከሁሉም በላይ ውስጣዊ ትንሽነት ነው። በወንጌላት ታሪክ ውስጥ በጥቂቱ የሚወጡት ሌሎች ብዙ ባሕርያት ነበሯት፣ ነገር ግን ስሟ የሚጠቀሰው በዋነኝነት በትሕትና ነው።
ትህትናን መላበስ
ከዚህ በመነሳት ማርያም ማእከላዊ መድረክ እንዳትሆን ተጠነቀቀች። ከመልአኩ ብሥራት በኋላ የመጀመርያ ውሳኔዋ ወደ ይሁዳ ተራሮች ኤልዛቤትን ለመጎብኘት መሄድ ነበር፣ በእርግዝናዋ የመጨረሻ ወራት ላይ ትረዳታለች። ነገር ግን ይህንን እንቅስቃሴ ማን ይገነዘበዋል? ከእግዚአብሔር ሌላ ማንም የለም። ድንግል ከዚህ መደበቂያ መውጣት የምትፈልግ አይመስልም። ልክ ከሕዝቡ ውስጥ የሴት ድምጽ በፅዕነቷን ሲያውጅ፡- “የተሸከመችህ ማሕፀንና የጠባሃቸው ጡቶች ብፁዓን ናቸው” (ሉቃስ 11:27) በማለት ስለእርሷ መስክራለች። ኢየሱስ ግን ወዲያው እንዲህ ሲል መለሰ፡- “ይልቁንስ ብፁዓን የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው በተግባር ላይ የምያውሉ ናቸው” (ሉቃስ 11፡28) በማለት ይመልሳል። በሕይወቷ ውስጥ በጣም የተቀደሰ እውነት እንኳን - የእግዚአብሔር እናት መሆን - በሰው ፊት እንድትመካ ምክንያት አይሆንም። ውጫዊ ውበትን በማሳደድ፣ ራስን ከሌሎች የበላይ እንደሆነ በማሳየት በተገለጸው ዓለም ውስጥ፣ ማርያም በቆራጥነት፣ በእግዚአብሔር ጸጋ ኃይል፣ በተቃራኒ አቅጣጫ ትጓዛለች።
እሷም አስቸጋሪ ጊዜያትን፣ እምነቷ በጨለማ የገዘፈባቸውን ቀናት እንዳወቀች መገመት እንችላለን። ነገር ግን ይህ ትህትናዋን በጭራሽ አላወዛገበም፣ ይህም በማርያም ውስጥ እንደ በጣም የከበረ ድንጋይ ዓይነት ዋጋ ያለው ምግባር ነበር፥ ሁል ጊዜ ትንሽ ነች፣ ሁል ጊዜ እርሷን በጣም ጠቃሚ አድርጋ የማትቆጥር፣ ከፍላጎት የጸዳች ነች። ይህ የትንሽነቷ ባሕሪይ የማይበገር ኃይሏ ነበር፣ የድል አድራጊ መሲህ ቅዠት መስሎ ሲሰባበር በመስቀሉ ስር የምትቀረው እሷ ነች። ከኢየሱስ ጋር አንድ ሰዓት ብቻ ነቅተው መጠበቅ ያልቻሉትን ደቀ መዛሙርት መንጋ የምትሰበስብ እና ማዕበሉ በመጣ ጊዜ ጥሏት የሄዱትን ደቀ መሳሙርቱን ከጴንጤቆስጤ በፊት ባሉት ቀናት የሰበሰበችው ማርያም ትሆናለች።
ትህትና ሁሉም ነገር ነው። ከክፉት የሚያድነን እና የእሱ ተባባሪዎች ከመሆን አደጋ የሚያድነን ነው። በዓለም እና በቤተክርስቲያን ውስጥ የሰላም ምንጭ ነው። እግዚአብሔር ለደህንነታችን እና ለደስታችን ሲል በኢየሱስ እና በማርያም ምሳሌ ሰጥቶናል።