ፈልግ

እ.አ.አ በ2023 ዓ.ም ሦስተኛው የዓለም የአያቶች እና የአዛውንቶች ቀን በቫቲካን በተከበረበት ወቅት እ.አ.አ በ2023 ዓ.ም ሦስተኛው የዓለም የአያቶች እና የአዛውንቶች ቀን በቫቲካን በተከበረበት ወቅት   (Vatican Media)

ር.ሊ.ጳ ፍራንችስኮስ ለ4ኛው የአረጋዊያን እና የአያቶች ቀን ያስተላለፉት መልእክት

ር.ሊ.ጳ ፍራንችስኮስ በሐምሌ 21/2016 ዓ.ም ለሚከበረው 4ኛው የዓለም የአያቶች እና የአረጋውያን ቀን ያስተላለፉት መልእክት

“በእርጅናዬ ዘመን አትጣለኝ” (መዝ. 71፡9)

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ

እግዚአብሔር በጭራሽ ልጆቹን አይጥልም። እድሜያችን ሲገፋና ኃይላችን እያሽቆለቆለ ሲሄድ፣ ጸጉራችን ሲነጣና በህብረተሰቡ ውስጥ ያለን ሚና ሲቀንስ፣ ህይወታችን ፍሬያማ መሆኑ እየቀነሰ ሲመጣና ምንም ጥቅም እንደሌለው ወደ መምሰል ልያዘነብል ይችላል። ‘እግዚአብሔር መልክን አይመለከትም’ (1 ሳሙ 16፡7)፣ ለብዙ ሰዎች የተገቡ የማይመስሉ ሰዎችን እርሱ ያለመናቅ ይመርጣቸዋል። እግዚአብሔር የሚንቀው ድንጋይ የለም፣  በእርግጥም “ከሁሉ የቀደሙት” መንፈሳዊ ሕንፃ ለመሥራት “አዲስ” ድንጋዮች የሚያርፍባቸው ጽኑ መሠረት ናቸው (1 ጴጥሮስ 2፡5)።

መጽሐፍ ቅዱስ በአጠቃላይ የጌታን ታማኝ ፍቅር የሚገልጽ ታሪክ ነው። እግዚአብሔር ምሕረቱን ዘወትር እንደሚያሳየን የሚያጽናና ማረጋገጫ ይሰጠናል፣ ሁልጊዜ፣ በማንኛውም የሕይወት ደረጃ፣ ራሳችንን ባገኘንበት በማንኛውም ሁኔታ፣ በክህደታችንም ውስጥ ሳይቀር ማለት ነው። መዝሙረ ዳዊት ምንም ዓይነት ሰዎች ብንሆንም ለእኛ የሚያስብልን የእግዚአብሔር ፊት በሰው ልብ ድንቅ ተሞልተዋል (መዝ. 144፡3-4)። እግዚአብሔር እያንዳንዳችንን ከእናታችን ማኅፀን ጀምሮ እንደፈጠረን አረጋግጦልናል (መዝ. 139፡13) እናም በገሃነምም ቢሆን ህይወታችንን እንደማይጥል (መዝ. 16፡10) ይነግረናል። እንግዲያው በእርጅና ወቅት ወደ እኛ እንደሚቀርብ እርግጠኞች መሆን እንችላለን፤ ምክንያቱም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ማርጀት የበረከት ምልክት ነው።

ይህንን ዝግጅት በድምጽ ለማዳመጥ ተጫወት የሚለውን ምልክት ይጫኑ

በተመሳሳይ ጊዜ፣ በመዝሙረ ዳዊት ውስጥ፣ “በእርጅናዬ ዘመን አትተወኝ” (መዝ. 71፡9) የሚለውን ለእግዚአብሔር የሚቀርበውን ልመና እናገኛለን። እነዚህ ጠንከር ያሉ፣ ጨዋ የሆኑ ቃላት ናቸው። በመስቀል ላይ “አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ?” ሲል የተናገረውን የኢየሱስን አስከፊ መከራ እንድናስብ ያደርጉናል (ማቴ 27፡46)።

እንግዲያው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ፣ በእያንዳንዱ የሕይወት ደረጃ ላይ፣ በተለይም በእርጅና ጊዜ እና በህመም ጊዜ አምላክ ይተወናል የሚል ፍርሃት ቢኖርም ነገር ግን የአምላክ ወደ እኛ የመቅረብ እርግጠኝነትን እናያለን። እዚህ ላይ ምንም ተቃርኖ የለም። ዙሪያውን ከተመለከትን ቃላቶቹ ፍጹም ግልጽ የሆነ እውነታ እንደሚያንጸባርቁ ለማየት ምንም ችግር የለብንም። ብዙውን ጊዜ ብቸኝነት እንደ አረጋውያን እና አያቶች የሕይወታችን መጥፎ ጓደኛ ነው። የቦነስ አይረስ ኤጲስ ቆጶስ በነበርኩበት ጊዜ፣ ብዙ ጊዜ፣ የአረጋዊያን መጦሪያ ቤቶችን እጎበኝ ነበር እናም እነዚያ ሰዎች እምብዛም እንደማይጎበኙ እገነዘብ ነበር። አንዳንዶች ለብዙ ወራት የቤተሰባቸውን አባላት አላዩም።

ለዚህ ብቸኝነት ብዙ ምክንያቶች አሉ፡ በብዙ ቦታዎች ከምንም በላይ በድሃ አገሮች አረጋውያን ልጆቻቸው ለስደት በመዳረጋቸው ብቻቸውን ይሆናሉ። ብዙ የግጭት ሁኔታዎችንም አስባለሁ። ልጆቻቸው ወደ ጦር ሜዳ በመሄዳቸው ብቻቸውን የቀሩ ብዙ አረጋዊያን አሉ። ከሁሉም በላይ ትናንሽ ልጆች ያሏቸው ሴቶች ለልጆቻቸው ደህንነት ሲሉ ከሀገር ወጥተዋል። በጦርነት በወደሙ ከተሞችና መንደሮች ብዙ አረጋውያን ብቻቸውን ይቀራሉ፣ መተው እና ሞት የበላይ ሆኖ በሚታይባቸው አካባቢዎች የህይወት ምልክቶች እነሱ ብቻ ናቸው። በሌሎች የዓለማችን ክፍሎች፣ በአንዳንድ የአካባቢ ባሕሎች ውስጥ ሥር የሰደደ፣ በአረጋውያን ላይ ጥላቻን የሚፈጥር፣ ጥንቆላ የሚመስል ነገር በመጠቀም የወጣቶችን አስፈላጊ ኃይል በመበዝበዝ ላይ ይገኛሉ በሚል የተሳሳተ እምነት ያጋጥመናል፣ ያለጊዜው ሞት ወይም ሕመም ወይም ሌላ ማንኛውም መጥፎ አጋጣሚ ወጣቱን ሲያጋጥመው ጥፋቱ የሚቀመጠው በአረጋውያን ደጃፍ ላይ ነው። ይህን አስተሳሰብ መታገል እና ማስወገድ አለብን። የክርስትና እምነት ነፃ ካወጣቸው ነገሮች መካከል በወጣቶችና በአረጋውያን መካከል ትውልዳዊ ግጭት እንዲፈጠር ከሚያደርጉት መሠረተ ቢስ ጭፍን ጥላቻዎች አንዱ ነው።

ነገር ግን ጉዳዩን ካሰብን ይህ አረጋውያን "የወጣቶችን የወደፊት ሕይወት እጣ ፈንታ ይዘርፋሉ" የሚለው ክስ በአሁኑ ጊዜ በሁሉም ቦታ አለ። በጣም በላቁ እና ዘመናዊ ማህበረሰቦች ውስጥም ቢሆን በሌሎች ነገሮች ተሸፍኖ ይታያል። ለምሳሌ በአሁኑ ወቅት አረጋውያን ወጣቶችን ከፍተኛ የማህበራዊ አገልግሎት ወጪ እያሸከሙት ነው፣ በዚህም ህብረተሰቡን ከልማትና ወጣቱን ከሥራ በማስወገድ ላይ ናቸው የሚል እምነት በስፋት እየተስተዋለ ይገኛል። ይህ ስለ እውነታው የተዛባ ግንዛቤ ነው። የአረጋውያን ሕልውና የወጣቶችን ሕልውና አደጋ ላይ እንደሚጥል፣ ለወጣቶች ሞገስን ለመስጠት አረጋውያንን ችላ ማለት አልፎ ተርፎም ማፈን እንደሚያስፈልግ ይገምታል። የትውልዶች ግጭት የተሳሳተ እና የተመረዘ የግጭት ባህል ፍሬ ነው። ወጣቱን በአረጋውያን ላይ ማነሳሳት ተቀባይነት የሌለው የማታለያ ዘዴ ነው፡- “አስፈላጊው ነገር የሰውን ልጅ ሕይወት ሙሉ በሙሉ ለመረዳት እና ለመገመት ትክክለኛው የማጣቀሻ ነጥብ የሆነው የተለያየ የሕይወት ዘመን አንድነት ነው”።

ከላይ የተጠቀሰው መዝሙር - በእርጅና ጊዜ መተው ወይም መጣል እንደሌለበት በመማጸን - በአረጋውያን ህይወት ዙሪያ ስላለው ሴራ ይናገራል። ይህ የተጋነነ ሊመስል ይችላል፣ ነገር ግን የአረጋውያን ብቸኝነት እና መተው በአጋጣሚ ወይም የማይቀር ሳይሆን የውሳኔዎች ፍሬ - ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ ፣ ማህበራዊ እና የግል ውሳኔዎች - የእያንዳንዳቸውን ማለቂያ የሌለውን የሰው ልጅ ክብር፣ ከማንኛው ሁኔታ በላይ የሆነው የሰው ክብር እውቅና በቅድሚያ መስጠት ይገባናል። ይህ የሚሆነው የእያንዳንዱን ግለሰብ ዋጋ ካጣን በኋላ ሰዎች ከዋጋቸው አንፃር ሲመዘኑ ይህም በአንዳንድ ሁኔታዎች ለመክፈል በጣም ከፍተኛ ነው ተብሎ ይታሰባል። በጣም ይባስ ተብሎ ብዙውን ጊዜ አረጋውያን ራሳቸው የዚህ አስተሳሰብ ሰለባ ይሆናሉ፣ እራሳቸውን እንደ ሸክም እንዲቆጥሩ እና ወደ ጎን ለመውጣት የመጀመሪያ መሆን እንዳለባቸው እንዲሰማቸው ይደረጋሉ።

በአሁኑ ጊዜም ብዙ ሴቶች እና ወንዶች በተቻለ መጠን ራሳቸውን ችለው ከሌሎች ሰዎች የተላቀቀ ህይወት ውስጥ የግል እርካታን ይፈልጋሉ። የቡድን አባል ሆኖ መኖር አደጋ ላይ እየወደቀ ይገኛል፣ እናም በአንጻሩ ግለሰባዊነት ይከበራል፡ ከ "እኛ" ወደ "እኔ" ያለው ምንባብ የዘመናችን በጣም ግልጽ ከሆኑ ምልክቶች አንዱ ነው። ‘ራሳችንን በራሳችን ማዳን እንችላለን’ የሚለውን አስተሳሰብ በመቃወም የመጀመሪያው እና በጣም ሥር ነቀል ክርክር የሆነው ቤተሰብ የዚህ ግላዊ ባህል ሰለባ ከሆኑት መካከል አንዱ ነው። ነገር ግን አንዴ ካረጀንና ኃይላችን ማሽቆልቆል ከጀመረ በኋላ፣ ማንም አያስፈልገንም እናም ያለ ማህበራዊ ትስስር መኖር የምንችለው የግለሰባዊነት ቅዠት ይገለጣል። በእርግጥ ሁሉንም ነገር በመፈለግ እንቃትታለን፣ ነገር ግን በሕይወታችን ውስጥ አንድ ነጥብ ላይ ብቻችንን ስንሆን፣ ከአሁን በኋላ ሌሎች ሊረዱኝ አይችሉም፣ የምንተማመንበት ማንም የለም ብለን ተስፋ እንቆርጣለን። ብዙ ሰዎች በጣም ሲዘገዩ ብቻ የሚያገኙት አሳዛኝ ግኝት ነው።

ብቸኝነት እና መተው በዛሬው የማህበራዊ ገጽታ ውስጥ ተደጋጋሚ ነገሮች ሆነዋል። ብዙ ሥሮች አሏቸው። በአንድ በኩል እነሱ የተሰላ መገለል ውጤት ናቸው፣ አንድ ዓይነት አሳዛኝ "ማህበራዊ ሴራ" ሲሆኑ በሌሎች ውስጥ በሚያሳዝን ሁኔታ የግለሰብ የግል ውሳኔ ጉዳይ ጭምር ይሆናሉ። በሌሎች ሁኔታዎች አረጋውያን ነፃ ምርጫቸው እንደሆነ በማስመሰል ለዚህ እውነታ ይገዛሉ። ይበልጥ "የወንድማማችነትን ጣዕም" አጥተናል፣ አማራጭ ማሰብ እንኳን ያስቸግረናል።

በብዙ አረጋውያን ውስጥ በሩት መጽሐፍ ላይ የተገለጸውን የተስፋ መቁረጥ ስሜት መመልከት እንችላለን፣ አረጋዊቷ ኑኃሚን፣ ባሏና ልጆቿ ከሞቱ በኋላ ሁለቱ ምራቶቿን ዖርፋንና ሩትን አበረታታች። ወደ ትውልድ መንደራቸውና ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ጠየቀች (ሩት 1፡8)። ኑኃሚን - ልክ እንደ ዛሬ ብዙ አረጋውያን - ብቻዋን ለመቆየት ትፈራለች፣ ነገር ግን የተለየ ነገር ማሰብ አትችልም። መበለት እንደመሆኗ መጠን በኅብረተሰቡ ዘንድ ብዙም ዋጋ እንደሌላት ታውቃለች፥ ራሷን እንደ ሸክም ትመለከታለች ከራሷ በተለየ መልኩ ሙሉ ሕይወቷን በፊቷ ላሉት ሁለት ወጣት ሴት ለመስጠት ትፈልጋለች። በዚህ ምክንያት፣ ወደ ጎን መውጣቷ የተሻለ እንደሆነ ታስባለች፣ እናም ስለዚህ ትናንሽ ምራቶቿን ርሷን ትተው እንዲሄዱ እና ወደፊት በሌሎች ቦታዎች ሕይወታቸውን እንዲመሰርቱ ትነግራቸዋለች (ሩት 1፡11-13)። ንግግሯ የራሷን እጣ ፈንታ የሚሸፍኑ የዘመኗን ግትር ማኅበራዊ እና ሃይማኖታዊ ስምምነቶችን ያንፀባርቃሉ።

መጽሐፍ ቅዱሳዊው ትረካ ለኑኃሚን ቃል እና ለእርጅና እራሱ ሁለት የተለያዩ ምላሾችን ይሰጠናል። ከሁለቱ ምራቶች አንዷ ኑኃሚንን የምትወደው ዖርፋ ሳመቻትና ብቸኛው መፍትሔ የሚመስለውን በመቀበል ወደ ፊት ሄደች። ሩት ግን ኑኃሚን ወደ ጎን አልተወችም እና በመገረም እንዲህ አለቻት:- " ተልይቼሽ እንዲሄድ አትለማመጭኝ" (ሩት 1: 16) አለቻት። ሩት ልማዶችን እና የተዳቀሉ የአስተሳሰብ ንድፎችን ለመቃወም ድፍረት ነበራት። አሮጊቷ ሴት እንደሚፈልጓት ተረድታለች እናም ለሁለቱም አዲስ ጉዞ በሚጀመሩበት ጊዜ በድፍረት ከጎኗ ትቆማለች። ብቸኝነት የማይቀር ዕጣ ፈንታችን ነው የሚለውን አስተሳሰብ ለለመድነው ሁላችን ሩት “ብቻዬን ጥለሽኝ አትሂጂ” ለሚለው ተማጽኖ ምላሽ “ጥዬሽ አልሄድም” ማለት እንደሚቻል ታስተምረናለች። ሩት ሊቀለበስ የማይችል የሚመስለውን ሁኔታ ለመቀልበስ ወደ ኋላ አትልም፣ ብቻችንን መኖር አማራጭ የሌለው አማራጭ ነው የሚለውን ሐሳብ ትቀይራለች! በአጋጣሚ አይደለም፣ ሩት – ከአረጋዊቷ ኑኃሚን ጎን የሆነችው – የመሲሑ ቅድመ አያት ነበረች (ማቴ 1፡5)፣ የኢየሱስ፣ የአማኑኤል፣ “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር”፣ የእግዚአብሔርን ቅርበት የሚያመጣ ለሁሉም ሰዎች በሁሉም ዕድሜዎች እና የህይወት ሁኔታዎች ቅርብ የሚሆነው የእርሱ ቅድመ አያት ነበረች።

የሩት ነፃነት እና ድፍረት አዲስ መንገድ እንድንከተል ይጋብዘናል። የእርሷን ፈለግ እንከተል። ከዚህች ወጣት ባዕድ ሴት እና አሮጊት ኑኃሚን ጋር እንሂድ፤ እናም ልማዶቻችንን ለመለወጥ እና ለአረጋውያን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ምን እንደሚሆን ለመገመት አንፍራ። አረጋዊያንን የሚንከባከቡ ወይም ሌላ ሰው ከሌላቸው ዘመዶቻቸው ወይም ከሚያውቋቸው ሰዎች ጋር የዕለት ተዕለት ቅርበት ለሚያሳዩ ብዙ መሥዋዕትነት ከፍለው የሩትን ምሳሌ የሚከተሉ ሁሉ እናመሰግናለን። ከኑኃሚን ጋር ለመቀራረብ የመረጠችው ሩት አስደሳች ትዳር፣ ቤተሰብና አዲስ ቤት በማግኘት ተባርኳል። ሁሌም ይህ ነው፡ ከአረጋውያን ጋር በመቀራረብ እና በቤተሰብ፣ በማህበረሰብ እና በቤተክርስቲያን ውስጥ ያላቸውን ልዩ ሚና በመገንዘብ፣ እኛ እራሳችን ብዙ ስጦታዎችን፣ ብዙ ፀጋዎችን፣ ብዙ በረከቶችን እንቀበላለን!

ለእነሱ በተሰጠ በዚህ አራተኛው የአለም ቀን፣ ለአያቶች እና ለቤተሰቦቻችን አረጋውያን አባላት ያለንን ጥልቅ ፍቅር እናሳይ። ተስፋ ከቆረጡ ሰዎች ጋር ጊዜ እናሳልፍ እና ከአሁን በኋላ የተለየ የወደፊት ዕድል ተስፋ ከማያደርጉት ጋር አብረን በመሆን ልናግዛቸው ይገባል። ወደ ብቸኝነት እና ወደ መተው በሚወስደው ራስን ብቻ ከማሰብ ይልቅ “አልጥልህም” ለማለት ድፍረት ያላቸውን ወንዶች እና ሴቶችን የተከፈተ ልብ እና የደስታ ፊት እናሳይ እና ወደ አንድ አቅጣጫ እንሂድ። የተለየ መንገድ እንከተል።

ለሁላችሁም ፣ ውድ አያቶች እና አረጋውያን ፣ እና ለእናንተ ቅርብ ለሆኑት ሁሉ ፣ በጸሎቴ የታጀበ ቡራኬዬን ልኬላችኋለሁ። እባካችሁን ለእኔ መጸለይ እንዳትዘነጉ።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ

ሚያዝያ 17/2016 ዓ.ምሮም፦

ከቅዱስ ዮሐንስ ላተራን

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ- ቫቲካን

 

16 May 2024, 16:14