ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት እ.አ.አ በመጪው 2025 ዓ.ም የሚከበረውን የኢዮቤልዩ ዓመት ይፋ አደረጉ!
የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ከተነሳ ከ40 ቀናት በኋላ ወደ ሰማይ ያረገበት የዕርገት በዓል በግንቦት 1/2016 ዓ.ም ተከብሮ ማለፉ የሚታወስ ሲሆን በዚህ መሰረት ይህ በዓል በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ሐሙስ ዕለት፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በእርሳቸው መሪነት ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ተክብሮ ማለፉ ተገልጿል። በእለቱ እ.አ.አ በመጪው 2025 ዓ.ም የሚከበረው የኢዮቤልዩ ዓመት በይፋ ቅዱስነታቸው አውጀዋል፣ መጪው የኢዩቤሊዩ አመት ‘ተስፋ ሕይወታችንን ይሙላው’ ማለታቸው የተገለጸ ሲሆን በወቅቱ ቅዱስነታቸው በእንግሊዜኛ ቋንቋ “Bull of Induction” (የድንጋጌ ሰነድ ስርፀት) -በላቲን ቋንቋ “Spes non confundit” (ተስፋ ለዕፍረት አይዳርገንም) ሮሜ 5፡5 ይፋ አድርገዋል።
የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን
“ተስፋ” እ.አ.አ የ2025 ዓ.ም የመጪው መደበኛ ኢዮቤልዩ ዋና ጭብጥ ሐሳብ ነው፣ በግንቦት 1/2016 ዓ.ም የሰነዱ መግቢያ መነበቡ የተገለጸ ሲሆን ሰነዱ ለአራቱ በሮም ከተማ የሚገኙ የጳጳስ ባዚሊካ ሊቀ ካህናት፣ ስብከተ ወንጌል እንዲስፋፋ የሚሰራው ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት እና የዓለም ኤጲስ ቆጶሳት ተወካዮች በክብር በተሰጠበት ሥነ-ሥርዓት ላይ የሰነዱ መግቢያ ተነቧል።
በላቲን ቋንቋ “Spes non confundit” (ተስፋ ለዕፍረት አይዳርገንም) በተሰኘው ሰነድ ውስጥ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እ.አ.አ በ2025 ዓ.ም የሚከበረው የኢዮቤልዩ ዓመት፣ አሁንም እ.አ.አ በ2024 ዓ.ም የገና በዓል ዋዜማ ላይ የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ የቅዱስ በር የመከፈት ሥነ-ስረዓት አስታውቀዋል።
በመቀጠል እ.አ.አ በታህሳስ 29 ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የሮማ ካቴድራል የቅዱስ ዮሐንስ ላተራን ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ በር ይከፍታሉ። በእለቱም በዓለማችን የሚገኙ ሁሉም ካቴድራሎች እና ንዑስ ካቴድራሎች ሊቀ ጳጳሳት የኢዮቤልዩ በር መከፈት ምክንያት በማድረግ ቅዳሴ እንደ ሚያሳርጉም ተገልጿል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጥር 1/2025 ዓ.ም በአውሮፓዊያኑ አዲስ አመት ላይ የሚከበረው “ማርያም የእግዚአብሔር እናት ናት” በተሰኘው አመታዊ በዓል ላይ በሮም ከተማ ውስጥ የሚገኘውን የቅድስት ማርያም ማጆሬ ባዚሊካ ቅዱስ በር እንደሚከፍቱ የሚጠበቅ ሲሆን ከእዚያም እንደ እ.አ.አ በጥር 5/2025 ዓ.ም ላይ በሚከበረው የጎርጎሮሳዊያኑ የጥምቀት በዓል ዋዜማ ላይ ደግሞ የቅዱስ ጳውሎስ ባዚሊካ ቅዱስ በር እንደሚከፍቱ ከወጣው መርዓ ግብር ለመረዳት ተችሏል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “በዓመቱ ውስጥ፣ የእግዚአብሔር ሕዝብ በእግዚአብሔር ጸጋ ላይ ባለው የተስፋ አዋጅ እና ውጤታማነታቸውን በሚያረጋግጡ ምልክቶች ላይ ሙሉ በሙሉ እንዲሳተፉ ለማድረግ ሁሉም ጥረት መደረግ አለበት” ሲሉ ጽፈዋል።
የኢዮቤልዩ በዓል እ.አ.አ በታህሳስ 28/2025 ዓ.ም በአለም ዙሪያ ባሉ አብያተ ክርስቲያናት በሚደረገው መስዋዕተ ቅዳሴ ይጠናቀቃል ፣ የቅዱስ ዮሐንስ ላተራን ፣ የቅድስት ማርያም ሜጀር እና የቅዱስ ጳውሎስ ባዚሊካ ቅዱስ በሮች በተመሳሳይ ቀን ይዘጋሉ።
እናም በመጨረሻ እ.አ.አ ጥር 6/2026 ዓ.ም የኢዮቤልዩ ዓመት በሮም የጥምቀት በዓል ላይ ይጠናቀቃል።