ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ታማኝ ምስክርነት ተጨባጭ የፍቅር ተግባር ማከናወንን እንደሚጠይቅ ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የማኅበሩ መሥራች አባ ሊዮን ዴሆን፥ የተጠራበትን ጥሪ በማስታወስ ባሰሙት ንግግር፥ የማኅበሩ መሥራች፥ “ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አንድነትን በመፍጠር እና በእርሱ ፍቅር ከእግዚአብሔር አብ እና ከሁሉም ሰው ጋር አንድነትን መፍጠር” የሚለውን የሕይወታቸው መርህ እና ማዕከል አስታውሰዋል።
ገዳማውያኑ ወደ ሮም የመጡት፥ ‘ዓለም ያምን ዘንድ በአዲሱ ዓለም ውስጥ አንድ መሆን’ በሚል መሪ ርዕሥ የተዘጋጀውን የማኅበራቸው 25ኛ ጠቅላላ ጉባኤን ለመካፈል እንደሆነ ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለገዳማውያኑ ባሰሙት ንግግር በሁለት ርዕሠ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩት ሲሆን፣ እነርሱም አንድነት እና ስብከተ ወንጌል ናቸው።
'አንድ መሆን'
አንድነት በራሳችን ኃይል የሚገኝ ስጦታ ባይሆንም የበኩላችንን ጥረት ማድረግ ይኖርብናል በማለት ምክራቸውን የለገሡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ገዳማውያኑ ለምስጢራት ሕይወት ቅድሚያ እንዲሰጡ፣ በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ እንዲያስተነትኑ እና በተለይም ራሳቸውን ለግል እና ለጋራ ጸሎት እንዲሰጡ አበረታቷቸዋል። “የኢየሱስ ክርስቶስ ልብ ሁልጊዜ በፍቅር ይጨነቅልናል” ብለው ሁሉንም ነገር ወደ እርሱ ማቅረብ እንደሚገባ በመጋበዝ እና “ያለ ጸሎት ኃይል ምንም ነገር ማድረግ እንደማይቻል በማሳሰብ ለኢየሱስ ክርስቶስ ቦታን እንዲሰጡ ጠይቀዋል።
"ዓለም ያምን ዘንድ"
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስለ ስብከት ወንጌል ተልዕኮ በማንሳት ባሰሙት ንግግር፥ በዚህ ግዙፍ እና ውስብስብ ችግሮች ባሉበት ዓለም ውስጥ እንዴት ነው የወንጌል መልዕክተኞች መሆን የምንችለው በማለትም ጠይቀዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የገዳሙ መሥራች የሆኑት የአባ ሊዮን ዴሆንን፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ሕማማት ላይ በማሰላሰል፥ የኢየሱስ ክርስቶስ መከራ ለአብ እና ለሰው ዘር በሙሉ ያለው ፍቅር ውጤት እንደሆነ አስረድተዋል።
“ተአማኒ እና ውጤታማ የወንጌል ምስክርነት ምስጢር የሚገኘው እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ‘ፍቅር’ የሚለው ቃል በሥጋችን ላይ እንዲጻፍ ስንፈቅድ፣ ማለትም በሥራችን ተጨባጭነት ላይ ነው” በማለት ገልጸዋል።
ቅዱስነታቸው በመጨረሻም የልበ ኢየሱስ ማኅበር ገዳም መሥራች የሆኑትን አባ ሊዮን ዴሆንን ባነሳሳው ተመሳሳይ እምነት እና ልግስና በተልዕኮአቸው እንደሚጸኑ ያላቸውን ተስፋ በመግለጽ ንግግራቸውን ደምድመዋል