ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንችስኮስ በመዝሙረ ዳዊት ውስጥ ያሉ ጸሎቶች ሁሌም የማይሰለችሁ ናቸው ማለታቸው ተገለጸ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደሚያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በእዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በሰኔ 12/2016 ዓ.ም ያደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ከእዚህ ቀደም በአዲስ መልክ “መንፈስ እና ሙሽራይቱ፦ መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ሕዝቦች ወደ ኢየሱስ እና ወደ ተስፋቸው ይመራቸዋል” በሚል ዐብይ አርዕስት ሥር ‘የመዝሙር መጽሐፍት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የጸሎት ጣዕመ ዜማ ናቸው’ በሚል ንዑስ አርዕስ ባደረጉት የክፍል አራት አስተምህሮ “የመዝሙረ ዳዊት መጽሐፍት ውስጥ ያሉ ጸሎቶች ሁሌም የማይሰለቹ ናቸው” ማለታቸው ተገልጿል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ- ቫቲካን

በእለቱ የተነበበው የእግዛኢብሔር ቃል

“የክርስቶስ ቃል በሙላት ይኑርባችሁ፤ እርስ በርሳችሁ በጥበብ ሁሉ ተማማሩ፤ ተመካከሩ፤ በመዝሙርና በማሕሌት፣ በመንፈሳዊም ቅኔ በማመስገን በልባችሁ ለእግዚአብሔር ዘምሩ። በእርሱ በኩል ለእግዚአብሔር አብ ምስጋና እያቀረባችሁ፣ በቃልም ሆነ በተግባር የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት” (ቆላ 3፡16-17)።

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በወቅቱ ያደረጉትን የትምህርተ ክርስቶስ አስትምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

ለቀጣዩ ኢዮቤልዩ ለመዘጋጀት እ.አ.አ የ 2024 ዓ.ም የጸሎት ጣዕመ ዜማ የሚሰማበት ዓመት እንዲሆን እጠያቀለው። በዛሬው የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ቤተ ክርስቲያን የጸሎት ጣዕመ ዜማ እንዳላት ማስታወስ እፈልጋለሁ፣ አቀናባሪው መንፈስ ቅዱስ ነው፣ እና እሱ የመዝሙር መጽሐፍ ነው።

እንደማንኛውም ጣዕመ ዜማ የተለያዩ “እንቅስቃሴዎችን”፣ ማለትም የተለያዩ የጸሎት ዘውጎችን ይዟል፡- ውዳሴ፣ ምስጋና፣ ልመና፣ ሙሾ፣ ትረካ፣ ጥበባዊ አስተንትኖ እና ሌሎችም፣ በግላዊ መልክ እና በሁሉም ሰዎች የመዝሙር ቅላጼ የገለጻል። እነዚህ መዝሙሮች መንፈስ ራሱ በሙሽሪት፣ በቤተ ክርስቲያኗ ከንፈሮች ላይ ያስቀመጣቸው መዝሙሮች ናቸው። ባለፈው ጊዜ የጠቀስኳቸው ሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍቶች በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የተጻፉ ናቸው፣ ነገር ግን የመዝሙር መጽሐፍ እንዲሁ በግጥም ተመስጦ የተሞላ ነው።

መዝሙራት በአዲስ ኪዳን ውስጥ ልዩ ቦታ ነበራቸው። በእርግጥም አዲስ ኪዳንንና መዝሙራትን አንድ ላይ የያዙ እትሞች ነበሩ አሁንም አሉ። በጠረጴዛዬ ላይ በጦርነቱ ከሞተ ወታደር ወደ እኔ የተላከ የዚህ አዲስ ኪዳን የመዝሙር እትም በዩክሬንኛ ቋንቋ የተጻፈ እትም አለኝ። በዚህ መጽሐፍም ፊት ለፊት ጸለየ። አንዳንዴ የኛ ያልሆነውን ታሪካዊ ሁኔታ እና ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ያንፀባርቃሉ። ይህ ማለት ግን ተመስጧዊ አይደሉም ማለት አይደለም፣ ነገር ግን በአንዳንድ ገፅታዎች ከጊዜ እና ጊዜያዊ የመገለጥ ደረጃ ጋር የተቆራኙ ናቸው፣ ልክ እንደ ትልቅ የጥንታዊ ህግ አካልም ነው።

መዝሙረ ዳዊትን በትኩረት እንድንከታተል የሚያደርገን የኢየሱስ፣ የማርያም፣ የሐዋርያቱ እና ከእኛ በፊት የነበሩት የክርስቲያን ትውልዶች ሁሉ ጸሎት መሆናቸው ነው። ስናነባቸው፣ እግዚአብሔር በዚያ ታላቅ “ኦርኬስትራ” ወይም የሙዚቃ ባንድ የቅዱሳን ማኅበር ያዳምጣቸዋል። ወደ ዕብራውያን በተጻፈው ደብዳቤ መሠረት፣ ኢየሱስ ወደ ዓለም የገባው ከመዝሙረ ዳዊት ጥቅስ በልቡ በመያዝ ነው፡- “እነሆ፣ ፈቃድህን ላደርግ መጥቻለሁ” (ዕብ. 10:7፣ መዝ. 40:9) በማለት ሲሆን በሉቃስ ወንጌል ላይ እንደ ተጠቀሰው ደግሞ ዓለምን ትቶ የሄደው “አባት ሆይ መንፈሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ” (ሉቃስ 23፡46፣ መዝ. 31፡6) በማለት ነበር የተሰናበተው።  

በአዲስ ኪዳን ውስጥ መዝሙራትን መጠቀም የአባቶች እና መላው ቤተ ክርስቲያን ተከትሎ የመጣ ሲሆን ይህም በቅዳሴ እና በሥርዓተ አምልኮ ላይ ቋሚ አካል ያደርጋቸዋል። “ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የእግዚአብሔርን ቸርነት ይተነፍሳሉ” ይላል ቅዱስ አምብሮዝዮስ “በተለይ ግን ጣፋጭ የመዝሙር መጽሐፍ” በማለት ይገልጸዋል። እኔ የሚገርመኝ፡ አንዳንድ ጊዜ ከመዝሙር መጽሐፍት ጋር ትጸልያላችሁን? መጽሐፍ ቅዱስን ወይም አዲስ ኪዳንን ወስዳችሁ መዝሙረ ዳዊትን በመጠቀም ጸልዩ። ለምሳሌ ኃጢአት በመሥራትህ ትንሽ ስታዝን መዝሙር 50ን ትጸልያለህ? ለመቀጠል የሚረዱ ብዙ መዝሙሮች አሉ። ከመዝሙር መጽሀፍት ጋር የመጸለይን ልማድ አዳብሩ። በመጨረሻ ደስተኛ እንደምትሆኑ አረጋግጣለሁ።

እኛ ግን ያለፈውን ትሩፋት ብቻ መኖር አንችልም፤ መዝሙረ ዳዊትን ጸሎታችን ማድረግ ያስፈልጋል። በተወሰነ መልኩ እኛ ራሳችን የመዝሙረ ዳዊት “ጸሐፍት” እንድንሆን፣ የኛ በማድረግና ከእነሱ ጋር መጸለይ እንዳለብን ተጽፏል። ልባችንን የሚናገሩ መዝሙራት ወይም ጥቅሶች ካሉ በቀን ውስጥ ደጋግመን መጸለይ ጥሩ ነው። መዝሙራት “ለሁሉም ወቅቶች” ጸሎቶች ናቸው፡ ወደ ጸሎት የሚቀየሩትን ምርጥ ቃላት በውስጣቸው የማያገኝ የአዕምሮ ሁኔታ ወይም ፍላጎት የለም። እንደሌሎች ጸሎቶች፣ መዝሙራት በመደጋገም ውጤታማነታቸውን አያጡም። በተቃራኒው ይጨምራሉ። ለምን? ምክንያቱም በእግዚአብሔር መንፈስ ተነሳስተው እና እግዚአብሔርን "እስትንፋስ" ስለሚያደርጉ በእምነት በተነበቡ ቁጥር ጣዕም ይሰጣሉ።

ኃጢአተኞች በመሆናችን በጸጸት ወይም በበደለኛነት እንደተጨነቅን ከተሰማን ከዳዊት ጋር፡- “አቤቱ እንደ ቸርነትህ መጠን ማረኝ” (መዝ 51፡1) በማለት መዝሙረ ዳዊት 51 የተጠቀሰውን ልንገልጽ እንችላለን። ከፍቅር ጋር ጠንካራ ግላዊ ትስስር መፍጠር ከፈለግን “እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ አምላኬ ነህ፤ አንተን ከልብ እሻለሁ፤ ውሃ በሌለበት፣ በደረቅና በተራቈተ ምድር፣ ነፍሴ አንተን ተጠማች፤ ሥጋዬም አንተን ናፈቀች” (መዝ. 63፡1) በማለት መዝሙረ ዳዊት 63 እንጸልይ። የሥርዓተ አምልኮ ሥነ-ሥረዓት ይህን መዝሙር በእሁድ እና በበዓላት ላይ እንዲደገም ያደርገው በከንቱ አይደለም። ፍርሃትና ጭንቀት ቢያንዣብብብን፣ እነዚህ አስደናቂ የመዝሙር 23 ቃላት እኛን ለማዳን ይመጣሉ፡- “እግዚአብሔር እረኛዬ ነው… በሞት ጥላ መካከል እንኳ ብሄድ፣ ክፉን አልፈራም።” ( መዝ 23:፣ 4)።

መዝሙረ ዳዊት ጸሎታችንን ወደ ልመና ብቻ በመቀነስ፣ ያለማቋረጥ “ስጠኝ፣ ስጠን…” በማለት ጸሎታችንን እንዲደኸይ አይፈቅድልንም። ከጌታ ጸሎት እንማራለን፣ “የዕለት እንጀራችንን” ከመለመናችን በፊት፣ “ስምህ ይቀደስ፣ መንግሥትህ ትምጣ፣ ፈቃድህ ትሁን። መዝሙረ ዳዊት እራሳችንን በራሳችን ላይ ያላተኮረ ጸሎት እንድንከፍት ይረዳናል፡ የምስጋና፣ የበረከት፣ የምስጋና ጸሎት። እና ደግሞ ለፍጥረታት ሁሉ ድምጽ እንድንሰጥ ይረዱናል፣ ይህም ውዳሴያችን ውስጥ ይካተታል።

ወንድሞች እና እህቶች፣ ሙሽሪት የሆነችው ቤተ ክርስቲያን ወደ መለኮታዊ ሙሽራዋ እንድትፀልይ ቃሉን የሰጠን መንፈስ ቅዱስ ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ድምፃቸውን እንድናሰማ እና ይህንንም የኢዮቤልዩ የዝግጅት አመት እውነተኛ የጸሎት መዝሙር እንዲሆንልን ይርዳን። አመሰግናለሁ!

20 June 2024, 12:28

በቅርብ ጊዜ ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር የተደረገው ግንኙነት

ሁሉንም ያንብቡ >