ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የበጎ ተግባር ተልዕኮ ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ ቀረበ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
እሑድ ሰኔ 23/2016 ዓ. ም. የሚቀርበው የቅዱስ ጴጥሮስ የዕርዳታ ማሰባሰብ መርሃ ግብር ጥሪ ቅዱስነታቸው በመከራ ውስጥ ለሚገኙት ሰዎች ዕርዳታን እንዲያደርጉ የሚያግዝ እና ሁሉም ሰው እንዲሳተፍበት ዕድል የሚሰጥ እንደሆነ ታውቋል።
ዓለም አቀፍ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የበጎ አድራጎት እንቅስቃሴ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሰዎች በቅዱስ ጴጥሮስ የዕርዳታ ማሰባሰብ መርሃ ግብር አማካይነት ዕርዳታቸውን እንዲለግሱ እና የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን የበጎ ተግባር ተልዕኮን እንዲደግፉ የሚጋብዝ ከመሆኑ በተጨማር የሰላም፣ የበጎ አድራጎት እና ለተቸገሩት ሰዎች የሚያሳዩት የአብሮነት ምሳሌ እንደሆነ ታውቋል።
በዚህ ልዩ ቀን ወይም በዓመቱ ውስጥ በማንኛውም ቀን በሚደረግ ልገሳ ማንኛውም ሰው በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሁለንተናዊ ተልዕኮ ላይ በንቃት መሳተፍ ይችላል። ይህ ተልዕኮ በጦርነት አደጋ፣ በጦር መሣሪያ እሽቅድምድም፣ በፍትሕ መጓደል፣ በድሆች ስቃይ እና በሰው ሕይወት ቅድስና እና ክብር ላይ በሚሰነዘር ጥቃት በተጨነቀ ዓለም ውስጥ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አስፈላጊ እንደሆነ ታምኖበታል።
በቅድስት መንበር ሥር የሚገኝ የጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት እንቅስቃሴ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በየዕለቱ ለሚያሰሙት ድምጽ ተጨባጭ ድጋፍ በማድረግ፣ በብዙ ከባድ ሁኔታዎች ውስጥ ለሚገኙ የተቸገሩ ግለሰቦችን እና ቤተሰቦችን በመርዳት እና የበጎ አድራጎት ሥራዎችን በመደገፍ፣ በተፈጥሮ አደጋዎች እና በጦርነት የተጎዱ ሰዎችን ለመርዳት ያግዛል።
የቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ የሆኑት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መልዕክት ዓለም አቀፋዊ፣ ሥር የሰደደ እና በቅዱስ ወንጌል ላይ የተመሠረተ ነው። ዕርዳታውን ለሁሉም ለማዳረስ የእያንዳንዳችን ድጋፍ ያስፈልገዋል። የእኛ ልገሳ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ ተልዕኮ አስተዋፅኦን በማድረግ ሌሎችን ሊረዳቸው ይችላል። ከሁሉም የዓለማችን ክፍሎች እና ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር እንዲቀራረብ ያስችላቸዋል። ትንቢታዊ መልዕክታቸውን እና ድምፃቸውን በዓለም አቀፍ ደረጃ በማሰራጨት ለሰላም እና ለወንድማማችነት የሚያደርጉትን ያላሰለሰ ጥረት ለመደገፍ የመተባበር እድልን ይሰጣል።
በቅዱስ ጴጥሮስ የዕርዳታ ማሰባሰብ መርሃ ግብር የሚገኝ የገንዘብ መጠን ትንሽ ሊሆን ቢችልም ነገር ግን ትልቅ ምሳሌያዊ እሴት ያለው ልገሳ እንደሆነ ይታወቃል። የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አባል የመሆናችንን ስሜት ለማጠናከር እና አብያተ ክርስቲያናትን በበጎ አድራጎት ለሚመሩት ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ያለንን ፍቅር ለማጠናከር የሚያስችል ተጨባጭ መንገድ እንደሆነ ይታመናል።
በቅዱስ ጴጥሮስ የዕርዳታ ማሰባሰብ መርሃ ግብር በመሳተፍ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የሚሰቃዩትን ለመርዳት የሚያደርጉትን ጥረት መደገፍ ብቻ ሳይሆን ወንጌልን ለማወጅ፣ የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትን፣
በቅድስት መንበር የእርዳታ ማስተባበሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤትን እና በመላው ዓለም የሚገኙ ተወካይ ጽሕፈት ቤቶችን በማገዝ እና በተልዕኮው በመሳተፍ ወሳኝ የሰው ልጅ ዕድገትን፣ የትምህርት ዕድሎችን፣ የሰላም፣ የፍትህ እና የወንድማማችነት ጥረቶችን እናበረታታለን።