ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የጋዛን የሰላም ጥረት በማበረታታት አስቸኳይ እርዳታ እንዲደረግ ጠየቁ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በሚቀጥሉት ቀናት ዮርዳኖስ ለጋዛ መደረግ ስላለበት አስቸኳይ የሰብአዊ እርዳታ ላይ ያተኮረ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ታስተናግዳለች። ባለፈው እሁድ ከተደረገው የመልአከ እግዚያብሄር ጸሎት በኋላ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የዮርዳኖስ ንጉስ፣ የግብፅ ፕሬዝዳንት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ በጋራ ያዘጋጁትን ጉባኤ በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት፣ “ጉባኤው እጅግ አስፈላጊ” እንደሆነ በመግለጽ፥ ያዘጋጁትን መሪዎች አመስግነዋል። ብጹእነታቸው በጦርነቱ የተዳከመውን የጋዛን ህዝብ ለመርዳት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ “አስቸኳይ እርምጃ እንዲወስድ” እና የሚቻለውን ሁሉ እንዲጠቀም አጥብቀው ካሳሰቡ በኋላ፥ ሰብአዊ እርዳታው ለተጎጂዎቹ እንዳይደርስ መከልከል እንደሌለበት እና በፍጥነት “ለችግረኞች እንዲደርስም” ተማጽነዋል።
የሰላም ስጦታን መለመን
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ሰኔ 1 ቀን 2016 ዓ.ም. ሟቹ የእስራኤል ፕሬዝዳንት ሺሞን ፔሬዝ እና የፍልስጤም ፕሬዝዳንት አቡ ማዜን የተሳተፉበት እና በቫቲካን የተካሄደው ‘የሰላም ጥሪ ጸሎት’ 10ኛ ዓመት የሚከበርበት ቀን መሆኑን አስታውሰው፥ በጋራ መስራት “እጅ ለእጅ ተያይዞ ችግሮችን ማለፍ እንደሚቻል እና ሰላም ለማምጣት ድፍረት እንደሚያስፈልግ፥ ይሄም ጦርነትን ለመጀመር ከሚያስፈልገው ድፍረት ያነሰ እንደሆነ ያሳያል” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ በመቀጠልም ጉዳዩ በሚመለከታቸው አካላት መካከል የሚደረገውን ቀጣይነት ያለው ድርድር ምንም እንኳን “ቀላል ባይሆንም” አጥብቀው እንደሚያበረታቱት ገልጸው፥ ለሰላም የሚቀርቡ ሃሳቦች፣ በሁሉም አከባቢዎች የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ እና ታጋቾችን መፍታት “ለፍልስጤማውያን እና እስራኤላውያን” ጥቅም ሲባል በአስቸኳይ ተቀባይነት እንደሚያገኝ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
ዩክሬን እና ማይናማርን አስታውሰዋል
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ የሚገኙትን እና ሰላምን የሚናፍቁትን የዩክሬን ህዝቦችን በሃሳባችን እና በጸሎታችን እንድናስታውሳቸው ከጠየቁ በኋላ፥ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት የዩክሬናዊያን ቡድን ሰላምታ በመስጠት፣ “ሁሌም ከእናንተ ጋር ነን” ብለዋቸዋል።
ሰዎች ሁሌም ሰላምን ይፈልጋሉ ያሉት ብጹእነታቸው፣“የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እገዛ ታክሎበት እና ሁሉም ዓይነት ጥረት ተደርጎ በተቻለ ፍጥነት ሰላም እንዲሰፍን” በድጋሚ አበረታተዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በማጠቃለያቸውም፣ በማይናማር ስቃይ ውስጥ የሚገኙትን ህዝቦች በማስታወስ በሃሳቦቻችን እና በጸሎቶታችን እንድናስታውሳቸው አሳስበዋል።