ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በ G7 ጉባኤ ላይ ከዓለም መሪዎች ጋር ተገናኙ!
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ- ቫቲካን
ሰኔ 7/2016 ዓ.ም አርብ ከሰአት በኋላ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በ G7 ስብሰባ ላይ ንግግር ያደረጉ የመጀመሪያው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነዋል። ከንግግራቸው በፊትም ሆነ በኋላ ከዓለም መሪዎች ጋር በርካታ የአንድ ለአንድ የሁለትዮሽ ስብሰባዎችን አድርገዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የመጀመሪያው የሆነውን ንግግራቸውን ከማድረጋቸው በፊት ከሚከተሉት ባለድርሻ አገራት እና የዓለም አቀፍ ድርጅት መሪዎች ጋር ተገናኝተው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
· ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ፣ የዓለም የገንዘብ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር
· ቮልዲያምር ዘሌኒስኪ የዩክሬን ፕሬዚዳንት
· ኢማኑኤል ማክሮን፣ የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት
· ጀስቲን ትሩዶ፣ የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር
ከንግግራቸው በኋላ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የሌሎች የዓለም መሪዎችን ንግግር ለማዳመጥ ብዙ ሰዓታት ወስደዋል። በመቀጠልም ከሚከተሉት ግለሰቦች ጋር ተነጋግሯል፡-
· የኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሳሞኢ ሩቶ
· ናሬንድራ ሞዲ የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር
· የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ባይደን
· ሉዊዝ ኢናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ፣ የብራዚል ፕሬዝዳንት
· ሬሲፕ ታይፕ ኤድሮዋን የቱርክ ፕሬዝዳንት
G7፡ ትኩረት በአፍሪካ ላይ ነው።
ቅዳሜ ሰኔ 8/2016 ዓ.ም የተጠናቀቀው የG7 የመሪዎች ጉባኤ በዋናነት በአፍሪካ እና በኢኮኖሚ ልማት ላይ ያተኮረ ቢሆንም በመካከለኛው ምስራቅ ስላለው ጦርነት እና ስደትን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በ G7 ለምን ተገኙ?
G7 (የቡድን ሰባት አገራት) በአሁኑ ጊዜ የፕሬዚዳንትነቱን ቦታ የያዘችውን ጣሊያንን እንዲሁም አሜሪካን፣ ካናዳ፣ ጃፓን፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ እና ጀርመንን ያጠቃልላል። ተሰናባቹ የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ፎን ደር ሌየንም ተገኝተዋል።
ቅድስት መንበር የቡድን ሰባት አገራት አባል አይደለችም፥ ነገር ግን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ተጋብዘው በስብሰባው ላይ እንዲገኙ ተደርጓል።