ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቁስጥንጥንያ የክርስቲያኖች አንድነት ፓትርያርካዊ ጽሕፈት ልኡካንን በቫቲካን ተቀበሉ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቁስጥንጥንያ የክርስቲያኖች አንድነት ፓትርያርካዊ ጽሕፈት ልኡካንን በቫቲካን ተቀበሉ  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቱርክ ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማካሄድ ተስፋ ማድረጋቸውን ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሰኔ 21/2016 ዓ. ም. ከቁስጥንጥንያ የክርስቲያኖች አንድነት ፓትርያርካዊ ጽሕፈት የመጡ ልኡካንን በቫቲካን ተቀብለዋቸውል። ቅዱስነታቸው ልኡካኑን በመንበራቸው ተቀብለው ባሰሙት ንግግር፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2025 ዓ. ም. በቱርክ ሐዋርያዊ ጉብኝት በማድረግ በኒቂያ ጉባኤ 1,700ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል ላይ ለመገኘት ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ325 በኒቂያ የተካሄደውን የመጀመሪያውን የክርስቲያኖች አንድነት ጉባኤ 1,700ኛ ዓመት መታሰቢያን በሥፍራው ተገኝተው ለማክበር መመኘታቸውን ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው ምኞታቸውን የገለጹት፥ የሮም ቤተ ክርስቲያን መሥራቾች የሆኑት የቅዱስ ጴጥሮስ እና ጳውሎስ ዓመታዊ በዓል ለማክበር ወደ ሮም ለመጣውን የቁስጥንጥንያ ፓትርያርክ ጽሕፈት ቤት የልዑካን ቡድንን ዓርብ ሰኔ 21/2016 ዓ. ም. ማለዳ ተቀብለው ባሰሙት ንግግር ሲሆን፥ ይህንም ለማድረግ በሙሉ ልብ መመኘታቸውን ተናግረዋል።

በሁለቱም አብያተ ክርስቲያን በኩል የሚደረግ ልማዳዊ ጉብኝት ሲሆን፥ በቁስጥንጥንያ ቤተ ክርስቲያንን እንደመሠረተ የሚታመን የቅዱስ እንድርያስ ዓመታዊ በዓል ላይ ለመገኘት ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የልኡካን ቡድን በየዓመቱ ወደ ቁስጥንጥንያ እንደሚጓዝ ይታወቃል።

የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ ከፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቴናጎረስ ቀዳማዊ ጋር በኢየሩሳሌም ሲገናኙ
የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ ከፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቴናጎረስ ቀዳማዊ ጋር በኢየሩሳሌም ሲገናኙ

ከወንድማዊ እርስ በርስ መጠያየቅ የሚገኝ ደስታ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ለልዑካን ቡድኑ ባደረጉት ንግግር፥ የወንድማማችነትን ደስታ ለማጣጣም እና ሁለቱን አብያተ ክርስቲያናት የሚያገናኝ ጥልቅ ትስስር እና በመካከላቸው ያለውን አንድነት ወደ ነበረበት ለመመለስ ያለውን ጽኑ ቁርጠኝነት ለመመስከር የሚያስችለውን ዕድል በደስታ መቀበላቸውን ገልጸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በንግግራቸው የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ በወቅቱ ፓትርያርክ ከነበሩት ከብጹዕ ወቅዱስ አቴናጎረስ ቀዳማዊ ጋር በኢየሩሳሌም ያደረጉት ታሪካዊ ስብሰባ 50ኛ ዓመት መታሰቢያን ላይ ከክርስቲያኖች አንድነት ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ በርተሎሜዎስ ቀዳማዊ ጋር እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2014 ዓ. ም. የተገናኙበትን እና ሌሎች ስብሰባዎችን አስታውሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሙሉ አንድነት እና በኅብረት ለመጓዝ ያላቸውን ቁርጠኝነት በማጉላት፥ “በአብያተ ክርስቲያናት መካከል የሚደረግ ውይይት ለእምነት ጠቃሚ እንደሆነ አስገንዝበዋል። “ይልቁንም ለእግዚአብሔር ባለን ታማኝነት ተነሳስተን እውነትን በስጦታ መለዋወጥ እና በመንፈስ ቅዱስ መመራት የግድ ነው” ብለዋል።

በቫቲካን የአትክልት ሥፍራ የተካሄደውን የሰላም ጸሎት ሥነ-ሥርዓት
በቫቲካን የአትክልት ሥፍራ የተካሄደውን የሰላም ጸሎት ሥነ-ሥርዓት

ለሰላም የሚደረጉ ጸሎቶች
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በየሩሳሌም ከተካሄደው ስብሰባ ብዙም ሳይቆይ በቫቲካን የአትክልት ሥፍራ የተካሄደውን የሰላም ጸሎት ሥነ-ሥርዓት አስታውሰዋል። በዕለቱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና ብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ በርተሎሜዎስ በጋራ በመሆን በቅድስት አገር፣ በመካከለኛው ምሥራቅ እና በመላው ዓለም ሰላም እንዲሰፍን የእስራኤል እና የፍልስጤም ተወካዮችን በክብር መቀበላቸው ይታወሳል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጦርነቱ ይቆም ዘንድ የሀገራቱ መሪዎች እና ግጭቶች ውስጥ የሚገኙ ወገኖች የስምምነት መንገዱን በድጋሚ እንዲያገኙ እና ሁሉም ወገኖች ወደ መግባባት ለመድረስ ለሰላም መጸለይ አስፈላጊ መሆኑን አሳይተውናል ብለዋል። ይህ የሰላም ጥሪ በሁሉም የግጭት አካባቢዎች በተለይም በዩክሬን እየተካሄደ ባለው ጦርነት ላይ እንደሚቀርብ ጠቁመዋል።

የፍቅር፣ የእርቅ እና የምሕረት መንገድ
ብዙ ሰዎች የፍርሃት እስረኞች በሆኑበት በዚህ ወቅት” የዓለም የተስፋ ፍላጎት ለመጪው የኢዮቤልዩ ዓመት እንዲሆን በማሰብ “የተስፋ ተሳላሚዎች” የሚል መሪ ርዕሥ ጠቁመዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት መጪው ቅዱስ ዓመት የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ፍሬ እንዳይጎድልበት በጸሎታቸው እንዲደግፉት ጋብዘዋል። በመጨረሻም፥ እግዚአብሔር ባመለከተን መንገድ መጓዛችንን እንድንቀጥል እርሱ የፍቅር፣ የእርቅ እና የምህረት መንገድ እንዲሰጠን በመለመን ንግግራቸውን ደምድመዋል።
 

28 June 2024, 16:35