ር. ሊ. ጳ. ፍራንቺስኮስ የኖርማንዲ ጥምር ሃይሎች ዓመታዊ በዓልን የሰላም ጥሪ በማቅረብ አስታወሱ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እ.አ.አ. ሰኔ 6 ቀን 1944 ዓ.ም. የጀርመን ጦርን ለመዋጋት የፈረንሳይ ከተማ በሆነችው ኖርማንዲ ያረፉትን የጥምር ጦር አባላትን ለማስታወስ ለባዩክስ እና ሊሲየስ ሊቀ ጳጳስ የጻፉት ደብዳቤ የሃይማኖት፣ የሲቪል እና ወታደራዊ ባለስልጣናት በተገኙበት በባዩክስ ካቴድራል በተካሄደው የማስታወሻ ሥነ ሥርዓት ላይ ተነቧል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ለተገኙት ሁሉ ያላቸውን ቅርበት በመግለጽ አውሮፓን ነፃ ለማውጣት በተደረገው የጋራ ወታደራዊ ጥረት እና የተከፈለውን ከፍተኛ መስዋዕትነትን ጠቅሰዋል።
“የጥምር ሃይሉ በዛ አከባቢ ማረፍ በአጠቃላይ ብዙ ወንዶች፣ ሴቶች እና ህጻናት የተሰቃዩበትን፣ ብዙ ቤተሰቦች የተበታተኑበትን እና በርካታ ውድመት የደረሰበትን የዚህን አስከፊ የሁለተኛ ዓለም ጦርነት ገፅታን ይፋ አድርጎታል” በማለት ጽፈዋል።
የኖርማንዲ ከተሞች የሆኑትን ካየን፣ ለሃቭሬ፣ ሴንት ሎ፣ ቼርበርግ፣ ፍለርስ፣ ሩየን፣ ሊሲየስ፣ ፋላኢዝ እና አርጌንታን ከተሞች የወደሙበትን እንዲሁም ለቁጥር የሚታክቱ በርካታ ንፁሀን ሰዎች ህይወት ያለፈበትን እና በቦምብ ፍንዳታው ምክንያት ከባድ መከራ ውስጥ የገቡትን ሰዎች አሳዛኝ ሁኔታ ይፋ አድርጓል ያሉት ብጹእነታቸው፥ ጦርነትን በማያሻማ ሁኔታ ለማውገዝ እና ላለመቀበል እነዚህን ክስተቶች ማስታወስ አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
ዳግመኛ ጦርነት አያስፈልግም!
እ.አ.አ. በ1965 ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ በተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ “ዳግመኛ ጦርነት አያስፈልግም!” ብለው ያቀረቡትን የሰላም ጥሪ በመጥቀስ፥ ብፁእ አባታችን ካለፈው ስሕተታቸው መማር ባለመቻላችን እንዳሳዘናቸው ገልፀው፣ ሰፊ ጦርነት የሚለው አስተሳሰብ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተለመደ በመሄዱ ያላቸውን ሥጋት ገልጸዋል።
“የአጠቃላይ ግጭት መላምት አንዳንድ ጊዜ በቁም ነገር መያዙ በጣም አሳሳቢ እንደሆነ እና ሰዎች ቀስ በቀስ ከዚህ ተቀባይነት በሌለው አስተሳሰብ ጋር እየተላመዱ ነው” ሲሉም ገልፀዋል።
ሰዎች ሰላም ይፈልጋሉ! ሁሉም ሰው በተረጋጋ ሁኔታ ግዴታውን የሚወጣበት የመረጋጋት፣ የደህንነት እና የብልጽግና ሁኔታዎችን ይፈልጋሉ” ብለዋል ብጹእነታቸው።
ከዚህም በተጨማሪ ይህንን ዕድል አደጋ ላይ የሚጥሉትን የርዕዮተ ዓለም፣ የብሔርተኝነት ወይም የኢኮኖሚ ምኞቶችን መፈለግ በሰው ልጆች ላይ ከባድ ጥፋት እንደሆነ እና በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአት እንደሆነ ገልፀዋል።
ጸሎቶች
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ አክለውም ጦርነትን ለሚቀሰቅሱ እና ለሚያስቀጥሉ ሰዎች ጸሎት እንዲደረግ ጥሪ በማቅረብ፥ “ጦርነትን ለሚፈልጉ፣ ለሚጀምሩት፣ በደመ ነፍስ ለሚያቀጣጥሉት እና ጦርነቱ በዘላቂነት እንዲራዘም ለሚያደርጉ ባለድርሻ አካላት ሁሉ እንጸልይላቸው” ካሉ በኋላ፥ “እግዚአብሔር ልባቸውን ያብራላቸው፣ የሚያደርሱትን የመከራ ሰልፍ ያሳያቸው!” በማለት ተማጽነዋል።
በተጨማሪም እርቅ ፈጣሪዎች ‘የእግዚአብሔር ልጆች’ ተብለው መጠራታቸውን በማስታወስ ለሰላም ፈጣሪዎች ጸሎት እንዲደረግ ጠይቀዋል። (ማቴ 5፡9)
የሰላም ፈላጊዎችም ሰላማዊ ግንኙነትና ውይይት እንዲያደርጉ በማበረታታት “አምላክ እነዚህን ሰዎች ያለ መታከት በብርታት እንዲጸኑ፣ ጥረታቸውም የስኬት ዘውድ እንዲጎናጸፍላቸው ያድርግ” ብለዋል።
በመጨረሻም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በሁሉም ጦርነቶች ውስጥ ሰለባ ለሆኑት ሰዎች ጸሎት እንዲደረግ በመጠየቅ፥ “ባለፈው እና አሁን ላይ እየተደረጉ ባሉ ጦርነቶች፥ በአጠቃላይ በሁሉም ጦርነቶች ሰለባ ለሆኑ ሰዎች እንጸልይ፣ በእነዚህ አስከፊ ግጭቶች ውስጥ የሞቱትን ሁሉ እግዚአብሔር በቸርነቱ ይቀባላቸው፣ ድሆች እና አቅመ ደካሞች፣ አረጋውያን፣ ሴቶች እና ህጻናት የእነዚህ አደጋዎች የመጀመሪያ ተጠቂዎች ናቸው፥ በመሆኑም በስቃይ ላይ የሚገኙትን ሁሉ አምላክ ብርታቱን ይስጣቸው” በማለት አጠቃለዋል።