ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ “ገንዘብ ሊያገለግለን እንጂ ሊገዛን አይገባም” አሉ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
‘ሴንቴሲመስ አኑስ ፕሮ ፖንቲፊስ ፋውንዴሽን’ የሚባለው ተቋም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እ.አ.አ. በ 1993 ዓ.ም. ነጋዴ እና ምሁራን ከሆኑ ካቶሊካዊያን ምዕመናን ጋር በመተባበር የመሰረቱት ሲሆን፥ ዓላማውም የካቶሊክን ማህበራዊ ትምህርት ለማስተዋወቅ እና በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ ያለመ ነው።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ፋውንዴሽኑ የጣሊያን የፋይናንስ ማዕከል በሆነችው ሚላን ከተማ ውስጥ በፋይናንስ፣ በባህል እና ሃይማኖት ላይ ያተኮሩ ውይይቶችን ሲያካሂድ ቆይቷል።
ወሳኝ ውይይት
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ሰኞ ዕለት ከተቋሙ ተወካዮች ጋር በቫቲካን ተገናኝተው በተወያዩበት ወቅት ይህ ጥረት “ቀላል ላይሆን ይችላል” ነገር ግን የምነፈልገውን ነገር ልናሳካ እንችላለን ብለዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በሴንቴሲመስ አኑስ ተቋም እና በኢጣሊያን የገንዘብ ተቋማት ተወካዮች መሃከል የተጀመረው ውይይት ትልቅ አቅም እንዳለው ገልጸዋል።
ይህንንም አስመልክተው ለተወያዮቹ እንደተናገሩት “በሚላን ውስጥ የሰራችሁት ስራ አበረታች ነው፥ ይሄንን ጅማሮ ወደ ሌሎች የፋይናንስ ማእከላት ማስፋፋቱ የበለጠ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል፥ ይህን አጠናክሮ መቀጠሉ የውይይት ባህልን የሚያስፋፋ ብሎም የሚያበረታታ ነው” ብለዋል።
ብጹእነታቸው “በሙያው በሰለጠኑ ሰዎች የሚሰራ ሥራ አሁንም የበላይነት አለው” ካሉ በኋላ፥ “ለጠንካራ እና ጤናማ ሥነ ምግባር፣ ባህል እና መንፈሳዊነት ቦታ የሚፈጥር አዲስ ባህል ያስፈልገናል” በማለት አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።
ብቃት እና ስነምግባር
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ፋውንዴሽኑ “እየተገበረ ያለውን የውይይት ባህል እና ዘይቤ አጠናክሮ እንዲቀጥል እና ወደ ሌሎችም እንዲያስፋፋ” በማሳሰብ፥ ውይይት “ሁልጊዜ የተሻለው መንገድ ነው” ብለዋል።
ከዚህም ባለፈ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እንዳሉት ፋውንዴሽኑ ኢኮኖሚያዊ ግቦችን ከሥነ ምግባራዊ ጉዳዮች ጋር በማዋሃድ ከከፍተኛ የገንዘብ ተቋማት ሥራ አስፈፃሚዎች ጋር ባደረገው ውይይት መገረማቸውንም ገልጸው፥ ለእንግዶቹ ባደረጉት ንግግር “ውጤታማነትን እና ብቃትን ከሁለገብ ዘላቂነት፣ ውህደት እና ስነምግባር ጋር በማጣመር ራሳችሁን ለተከበረ ተግባር አዘጋጅታችኋል” በማለት አበረታተዋል።
አስፈላጊ እውቀት
የቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ ትምህርት በዚህ ዘርፍ እንደ “አቅጣጫ ጠቋሚ” ሆኖ እንዲያገለግል፣ “መምከር ብቻ ሳይሆን የፋይናንስ አሠራርን መረዳት፣ ድክመቶችን መለየት እና ተጨባጭ የማስተካከያ እርምጃዎችን ማቅረብ አስፈላጊ ነው” ሲሉ ሊቀ ጳጳሱ አሳስበዋል።
አንዳንድ የታሪክ ምሳሌዎች እንደሚያሳዩት የሃይማኖት መሪዎች የሚናገሩትን ሲያውቁ ብቻ የኢኮኖሚውን ዘርፍ በታማኝነት ሊመክሩት እንደሚችሉም ጠቁመዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የ16ኛው ክፍለ ዘመን የሃይማኖት ምሁራንን በምሳሌነት ጠቅሰው፥ በወቅቱ በስፔን እየተስፋፋ የመጣውን የሱፍ ንግድ እና ያስገኝ የነበረውን ከፍተኛ የገንዘብ ጥቅምን ተከትሎ ሃይማኖታዊ ምሁራኑ ለበግ አርቢዎችና ሱፍ አምራቾች ኢኮኖሚያዊ ፍትህ እንዲሰፍን በመጠየቅ፥ ለዚህም መፍትሄ የሚሆን ተጨባጭ ማሻሻያዎችን ያቀረቡበትን የታሪክ አጋጣሚ አንስተዋል።
ይሄንን ጉዳይ አስመልክተው እንደተናገሩት “የስፔን የሃይማኖት ሊቃውንት በወቅቱ ጣልቃ መግባት የቻሉት የኢኮኖሚውን ሂደት በሚገባ ስለሚያውቁ ነው፥ ስለዚህም “የጋራ ጥቅምን መፈለግ አለብን” ብለው ብቻ አልነበረም የተነሱት፥ ስህተቱን አስረድተው የተለየ እርምጃ እንዲወስዱ ጠይቀዋል” በማለት አስረድተዋል።
ተልዕኮ
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ለእንግዶቻቸው በመጨረሻም ባስተላለፉት መልዕክት “የፋይናንስ ሂደቶችን ተረድታችኋል፣ ይህ ማለት ደግሞ ለእናንተ ትልቅ ጥቅም ነው፥ ነገር ግን ትልቅ ኃላፊነትም ጭምር እንዳለባችሁ መረዳት አለባችሁ” ካሉ በኋላ፥ “ኢፍትሃዊነት የሚቀንስበትን መንገዶች መፈለግ የእናንተ ድርሻ ነው… ገንዘብ ሊያገለግለን እንጂ ሊገዛን አይገባም” “አሁን ያደረጋችሁት ነገር በጣም አስፈላጊ ተግባር ነው” ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የውውይት ሂደቱን አጽንኦት ሰጥተው አበረታተዋል።