ር.ሊ.ጳ ፍራንችስኮስ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለረሃብ በተጋለጡባት ለሱዳን ሰላም ጸሎት አድርገዋል!
የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ- ቫቲካን
“ከአንድ አመት በላይ የዘለቀ ጦርነት እስካሁን ሰላማዊ መፍትሄ ባላገኘባት ለሱዳን እንድትጸልዩ ጋብዛለሁ።እባካችሁን የጦር መሳሪያዎች ጸጥ እንዲሉ አድርጉ” በማለት ከእዚህ ቀደም አቅርበውት የነበረውን ተማጽኖ ቅዱስነታቸው በድጋሚ ያደሱ ሲሆን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህንን የተናገሩት እሁድ ግንቦት 25/2016 ዓ.ም በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ መላኩ ገብርኤል ማርያምን ያበሰረበት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ከምዕመናን ጋር በመቀባበል ከደገሙ በኋላ ባቀረቡት የሰላም ጥሪ መልእክት ላይ እንደ ነበረ ተገልጿል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ዓለም አቀፍ መሪዎች እና የሱዳን ባለስልጣናት ሱዳንን እና በርካታ የተፈናቀሉ ህዝቦቿን እንዲረዱ አሳስበዋል።
የሱዳን ስደተኞች በአጎራባች አገሮች ውስጥ እንኳን ደህና መጣችሁ እንዲባሉ እና ጥበቃ እንዲደረግላቸው ቅዱስነታቸው ጥሪ አቅርበዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተጨማሪም “ሰማዕት በሆነችው ዩክሬን፣ ፍልስጤም፣ እስራኤል እና ምያንማር” ሰላም እንዲሰፍን ጸለዩ።
"የጦርነት መባባስ እንዲቆም እና ሁሉም ጥረት በውይይት እና በድርድር እንዲፈታ የመሪዎችን ጥበብ እጠይቃለሁ" ብለዋል ።
በሱዳን ሚሊዮኖች ለረሃብ አደጋ ተጋልጠዋል
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የሰላም ጥሪ እንዳቀረቡ፣ በሱዳን ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለረሃብ አደጋ ተጋልጠው የሚገኙበት ጊዜ እየተፋጠነ እና እያሽቆለቆለ ይገኛል ያሉ ሲሆን ሀገሪቱ በሁለተኛው አመት በተቀናቃኝ ወታደራዊ አንጃዎች መካከል ግጭት ውስጥ የምትገኝ ሲሆን በአለም ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የተፈናቀሉ ዜጎች መኖሪያ ነች።
አሁን ጦርነቱ እየገፋ በሄደ ቁጥር የሰብአዊ ድርጅቶች ተፋላሚ ወገኖች ዕርዳታ ወደ ህዝቡ እንዳይደርስ እየከለከሉ ነው በማለት ከባድ ማስጠንቀቂያ አስተላልፈዋል።
ይህ የቅርብ ጊዜ ማስጠንቀቂያ የመጣው 12 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኤጀንሲዎችን ጨምሮ 19 አለምአቀፍ የሰብአዊ ድርጅቶች ተፋላሚ ወገኖች በረሃብ ለሚሰቃዩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የምግብ እርዳታ እንዳይደርስ መከልከላቸውን እንዲያቆሙ አሳስበዋል።
በቅርቡ የችግሩን ስፋት የሚያመላክት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ቃል አቀባይ ጄንስ ላየርኬ የሱዳን 18 ሚሊዮን የተራቡ ሰዎች ዕርዳታው መድረስ ካልጀመረ ይሞታሉ ብለዋል።
3.6 ሚሊዮን ታዳጊዎች በረሃብ እየተሰቃዩ ያሉት ህጻናት ዋነኛ ተጠቂዎች ሆነው ይታያሉ።
"በሱዳን በፍጥነት እና በመጠን ዕርዳታ እንዳይሰጡ መከልከላቸውን ከቀጠሉ፣ በሀገሪቱ ሰፊ ክፍሎች ውስጥ ረሃብ ሊከሰት ይችላል" ብለዋል ሚስተር ላየር። “ብዙ ሰዎች ወደ ጎረቤት አገሮች ይሰደዳሉ። ሕጻናት በበሽታና በተመጣጠነ ምግብ እጦት እየተጠቁ ይገኛሉ፣ ሴቶችና ልጃገረዶች ደግሞ የከፋ መከራና አደጋ ይደርስባቸዋል።
ከአንድ አመት በላይ ጦርነት
ሱዳን ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ላይ ነች። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባደረገው ስሌት መሰረት ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጉ ከመኖሪያ ቤታቸው የተፈናቀሉ ዜጎች በሀገሪቱ ውስጥ ስደተኞች ናቸው።
ይባስ ብሎ ደግሞ ሁለት ሚሊዮን ሰዎች ለደህንነታቸው ሰግተው ወደ ጎረቤት ሀገራት ተሰደዋል።
ሱዳን እ.አ.አ ከሚያዝያ 15 ቀን 2023 ዓ.ም ጀምሮ በሱዳን ጦር እና በአርኤስኤፍ መካከል አሰቃቂ የትጥቅ ግጭቶችን እያስተናገደች ሲሆን ሁለቱ ወገኖች ግጭቱን አነሳስተዋል ሲሉ እርስ በርሳቸው ሲወነጃጀሉ ቆይተዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከዚህ ቀደም እየተባባሰ የመጣው ሁኔታ በአጎራባች ሀገራት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረ ሲሆን ብዙዎቹም የራሳቸውን ቀውሶች እየተቋቋሙ ነው ብሏል።