ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለ155 ዓመታት አገልግሎት ሲያበረክት የቆየውን የቅዱስ ጴጥሮስ ማኅበር አመሰገኑ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ቅዱስነታቸው የማኅበሩ አባላትን ሰኞ ሰኔ 17/2016 ዓ. ም. በቫቲካን ውስጥ ተቀብለው ባስተላለፉት መልዕክት፥ ማኅበሩ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በመታቀፍ በቅርበት፣ በርህራሄ እና በገርነት ቤተ ክርስቲያንን በእጅጉ በማገልገል እንዲሁም የሮም ከተማን ለኢዮቤልዩ በዓል ማዘጋጀታቸውን አስታውሰዋል።
ቅዱስነታቸው በቫቲካን ውስጥ ለተቀበሏቸው የማኅበሩ አባላት ባሰሙት ንግግር፥ ለ155 ዓመታት የቤተ ክርስቲያኒቱን የበጎ አድራጎት ተግባራት ሲደግፉ እና የተቸገሩትን ሲረዱ ለቆዩት የቅዱስ ጴጥሮስ ማኅበር የበጎ ፈቃድ ማኅበርተኞች ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ማኅበሩ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1869 ዓ. ም. በሮም ከተማ ውስጥ በሚኖሩ ወጣቶች መመሥረቱ ይታወሳል።
ቅዱስነታቸው የማኅበሩ አባላት ለቀደሙት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የነበራቸውን የአገልግሎት ታሪክ በደስታ በማስታወስ ለማኅበሩ አባላት ደማቅ አቀባበል ያደረጉላቸው ሲሆን፥ በጤና መጓደል ምክንያት በሥነ ሥርዓቱ ላይ ሊገኙ ላልቻሉት ያማኅበሩ ፕሬዝዳንት ሰላምታቸው እንዲያደርሱላቸው ጠይቀው ሙሉ ጤናንም ተመኝተውላቸዋል።
ለወደፊት ተግባር ወሳኝ የሆኑትን የጥንት ተግባራትን አስታውሰዋል
“በሮም ከተማ ውስጥ ለሚኖሩት ድሆች ለምታደርጉት ድጋፍ በሙሉ ምስጋናዬን አቀርባለሁ” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ይህንን ድጋፍ የሚያደርጉትም በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት እና በቅድስት እናት ቤተ ክርስቲያን ስም እንደሆነ አምናለሁ” ብለዋል።
ያለፉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ከቅዱስ ጴጥሮስ ማኅበር አባላት ጋር የተገናኙባቸውን አጋጣሚዎች የሚዘግብ መጽሐፍ ተበርክቶላቸው እንደነበር አስታውሰው፣ እንዲህ የመሳሰሉ ማስታወሻዎች አንድ ሰው ከጥንት ጀምሮ ሲያበርክት የቆየውን በጎ ተግባራት ለማስታወስ እንደሚረዱ ገልጸው፥ መሠረታዊ እንደሆኑም አስረድተዋል።
"ሥር ከሌለ የወደፊት ሕይወት የለም" ያሉት ቅዱስነታቸው "የቅጠሎች ልምላሜ ከዛፉ ጤናማ ሥር ጋር የተያያዘ ነው" በማለት አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው በዚህም መሠረት ማኅበርተኞቹ ዘወትር ሥሮቻቸውን እንዲንከባከቡ በማሳሰብ፥ መልካም ሥራዎቻቸውም ፍሬ ያለው እንዲሆን አደራ ብለዋል።
ቅርሶችን እና እሴቶችን ለወጣቶች ማስተላለፍ
"እሴቶቻችሁን፣ ልምዶቻችሁን እና ቅርሶቻችሁን ለወጣቶች እንድታስተላልፉ የማበረታታችሁ ለዚህ ነው" ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ወጣቶች ወደፊት ለመራመድ ቁልፍ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
"የቀደሙት የቅዱስ ጴጥሮስ ማኅበር አባላት ልምዶቻቸውን ዳቸውን ለልጅ ልጅ ሲያስተላልፉ መመልከት ደስ ያሰኛል!" ሲሉ ቅዱስነታቸው አወድሰዋል።
ቅዱስነታቸው ይህን መልካም ተግባር በማስታወስ “የአረጋዊያን ምሳሌነት ህያው እምነትን፣ ተጨባጭ በጎ አድራጎትን እና ፍቅርን ለድሆች ማስተላለፍ እንደሚችል ማስታወስ ይገባል” ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመቀጠልም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2025 ዓ. ም. የሚከበረው የተስፋ ኢዮቤልዩ በዓል በጎ ተግባር የሚፈጸምበት አጋጣሚ ሊሆን እንደሚገባም አስታውሰዋል።
የተስፋ እና የበጎ አድራጎት ኢዮቤልዩ
"ወደ ሮም የሚመጡ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች ክርስቲያናዊ የበጎ አድራጎት አየርን 'መተንፈስ' አለባቸው" ብለው፥ ይህም ዕርዳታን ማቅረብ ብቻ ሳይሆን የእንግዶችን ሰብዓዊ ክብር በመንከባከብ፣ እርስ በርስ በመቀራረብ እና ያለንን ለሌሎች ከልብ በማካፈል የሚከናወን መሆን ይኖርበታል ብለዋል።
የማኅበሩ ዓባላት በቤተ ክርስቲያን አለኝታነታቸው፣ በቅርበታቸው፣ በርህራሄያቸው እና በለጋስነታቸው የሮም ከተማን ለኢዮቤልዩ በዓል እንዳዘጋጇት የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ ይህ ዝግጅት ከመንገድ ግንባታ ወይም ከመሠረተ ልማት ሥራ ያለፈ መሆኑን ጠቁመዋል።
ዝግጅቱ ይልቁንም ለድሆች ልብ እና ሥጋ የሚያስብ፥ ቅዱስ ሎረንስ እንደተናገረው፥ “የቤተ ክርስቲያን ውድ ሃብት ነው” ማለቱንም አስታውሰዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቫቲካን ለተቀበሏቸው የቅዱስ ጴጥሮስ ማኅበርተኞች እና ቤተሰቦቻቸው በሙሉ ቡራኬያቸው ሰጥተው፣ የሮም ከተማ ነዋሪዎች ጠባቂ የሆነች የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እርዳታን በመለመን ንግግራቸውን አጠቃለዋል።