ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የሁሉ አባት መሆናቸውን ስደተኞች መሰከሩ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ቅዱስነታቸው ስደተኞችን እና ደጋፊዎቻቸውን በቫቲካን ሲቀበሉ የመጀመሪያቸው እንዳልሆነ የገለጹት የነፍስ አድን ድርጅቱ ሐዋርያዊ ተንከባካቢ አባ ማቲያ ፌራሪ፥ ወደ ቅዱስነታቸው የሚመጡባቸው ጊዜያት በሙሉ ታላቅ የጸጋ ጊዜያት እንደሆኑ ተናግረው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ካቶሊክ፣ ሙስሊም ወይም የሌላ እምነት ተከታይ ሳይሉ ያለ ልዩነት ሁሉንም በእኩል ዓይን የሚመለከቱ የሁሉ አባት ናቸው” ሲሉ አክለዋል።
ስቃይ እና ተስፋ ያለባቸው ታሪኮች
ስቃይ የበዛበትን የሊቢያ በረሃ አቋርጠው የመጡት የዕለቱ ዋና እንግዶች፥ ሴኔጋላዊው ኢብራሂም ሎ እና ጋምቢያዊው ኤብሪማ ኩያቴህ ተመሳሳይ መከራ የደረሰባቸው እንደሆነ በጻፉት መጽሐፋቸው ገልጸዋል። ወጣት ኢብራሒም የስደት ጉዞውን በማስመልከት በጻፏቸው ሁለት መጽሐፍት የመጀመሪያን “ዳቦ እና ውሃ” በሚል ርዕሥ፥ ሁለተኛውን “የእኔ ድምጽ” በሚል ርዕሥ እንደጻፋቸው ገልጿል።
ከቅዱስነታቸው በኩል የተደረገ የክብር አቀባበል
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የስደተኞቹን ታሪክ ለማድመጥ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው የተናገሩት አባ ማቲያ፥ ቅዱስነታቸው የስደተኛ ደጋፊ ድርጅቶች ለሚያቀርቡት ዕርዳታ እና ለሚሰጡት ተጨባጭ ምሥክርነት ማመስገናቸውን እና ጠንክረው ወደፊት እንዲራመዱ ብርታትን መመኘታቸውን ገልጸዋል።
አባ ማቲያ በመጨረሻም፥ ስደተኞች በሙሉ ከፍተኛ ስቃይ ያለበት ታሪካቸውን እና ተስፋቸውን በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዘንድ ማስቀመጥ እንደሚፈልጉ ገልጸው፥ በባሕርና በየብስ ላይ ያለው ተሞክሮ፥ ድሆችን እና ስደተኞችን ተቀብለው ሲያስተናግዷቸው እና ሲያግዟቸው ለራሳቸው ድነትን እንደሚያተርፉ፥ ከድሆች ጋር በፍቅር እና በወንድማማችነት በአንድነት ሲኖሩ የምሕረትን መንገድ እንደሚለማመዱት አስረድተዋል።