ፈልግ

ብሔራዊ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ ብሔራዊ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ  

የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ልዩ መልዕክተኛ በመጭው ዓመት የሚከበረውን የዓለም የተልዕኮ ቀን ይፋ አደረጉ

በኢንዲያናፖሊስ፣ ኢንዲያና በተካሄደው 10ኛው ብሔራዊ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ ጎን ለጎን በተካሄደው ልዩ አቀባበል፣ ብፁዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግሌ እና ብፁዕ ካርዲናል ክሪስቶፍ ፒየር በጥቅምት 10/2017 ዓ. ም የሚከበረውን የዓለም የተልዕኮ ዕለተ ሰንበት የመደገፍ ጠቀሜታን አስምረውበት ከ1,100 በላይ ግዛቶች በመንፈሳዊ አገልግሎት እጥረት ችግር ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

በቅድስት መንበር ለሕዝቦች የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ እና በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙት ብፁዕ ካርዲናል ክሪስቶፍ ፒየር በዓለም ዙሪያ ያሉ አማኞችን በእውነት የተቸገሩትን ለመርዳት የሚስዮናዊነት መንፈስ እንዲታደስ ጠይቀዋል።

በሐምሌ 13 በኢንዲያናፖሊስ ኢንዲያና በተካሄደው 10ኛው ሀገር አቀፍ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ ላይ ብፁዓን ካርዲናሎች 98ኛውን የዓለም ተልዕኮ እለተ ሰንበት በጥቅምት 10/2017 ዓ. ም እንደሚከበር ገልጸው፣ ይህንን ለማስተዋወቅ በዚህ ዓመት በአብዛኞቹ የአሜሪካ አህጉረ ስብከቶች የሚጠቅሙ ቁሳቁሶችን አቅርበዋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የዘንድሮው መሪ ቃል "ሂዱና ሁሉንም ሰው ወደ ማዕዱ ጋብዙ" የሚለውን መርጠዋል።

በሰሜን አሜሪካ የሚገኘው የጳጳሳዊ ተልእኮ ማኅበራት ባወጣው መግለጫ መሠረት፣ የጳጳሱ ልኡካን ዓለም አቀፍ የተልዕኮ ቀን እለተ ሰንበት የመሰብሰቢያ ቀን ብቻ ሳይሆን የቤተ ክርስቲያኒቱን የስብከተ ወንጌል ቃል ኪዳን ለማደስ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተልዕኮዎችን ለመደገፍ አጋጣሚውን የሚፈጥር መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። በአቀባበል ሥነ ሥርዓቱ ላይ የቦርድ አባሎቹን የቅዱስ ጳውሎስ እና የሚኒያፖሊስ ሊቀ ጳጳስ በርናርድ ሄብዳ እና የማያሚ ሊቀ ጳጳስ ቶማስ ዌንስኪን ጨምሮ 50 የሚጠጉ ጳጳሳት ከቦርድ አባል ባሪ ጃክሰን ጋር ተገኝተዋል።

የዓለም የተልዕኮ ዕለተ ሰንበት
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 11ኛ ከአራቱ ጳጳሳዊ ተልእኮ ማኅበራት አንዱ በሆነው የእምነት ማስፋፊያ ማኅበር ተነሳሽነትን በመውሰድ የዓለም ተልእኮ እለተ ሰንበት ቀን በ1926 እ. ኤ. አ. እንዲከበር በወሰኑት መሰረት በቀጣዩ አመት የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ ስብስብ መካሄዱ የሚታወስ ሲሆን፥ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ዓለም አቀፋዊ የአብሮነት ቀን መከበሩ መጀመሩ ይታወሳል። በአለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ በጥቅምት ወር የመጨረሻው እሁድ ላይ የሚካሄደው የአለም ተልዕኮ እለተ ሰንበት ለመላው ቤተ ክርስቲያን ከ1,100 በላይ አገረ ስብከቶችን ለመርዳት እና በተለይም በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት እና የክርስቶስ መስካሪዎች ለሆኑ ለድሆች ተግባራዊ እርዳታ ለመስጠት የሚደረግ ልዩ ጥረት አካል ነው።

የጸሎት እና የስጦታ ቀን መነሻ የሆነው በ19ኛው ክፍለ ዘመን በፈረንሳይ አገር ሲሆን መእመን የነበሩ ብፅዕት ፓውሊን ያሪኮት ጓደኞቿ በየቀኑ ለተልእኮው እንዲጸልዩ እና በሳምንት አንድ ሳንቲም እንዲሰጡ በጠየቁ ጊዜ ነበር እለቱ የተጠነሰሰው። ያ በመጀመሪያ የተሰበሰበው መባ ወደ ሉዊዚያና ሀገረ ስብከት ተልኳል፣ ከዚያም ከፍሎሪዳ ወደ ካናዳ፣ እንዲሁም ወደ ባርድስታውን፣ ኬንታኪ ተነሳሽነቱ መስፋፋቱ ይታወሳል።
በሰሜን አሜሪካ ውስጥ ያሉ ጳጳሳዊ ተልእኮ ማኅበራት ለሚስዮን ግዛቶች የሰበሰበውን መባ በቀጥታ ያሰራጫሉ።

ጳጳሳዊ ተልእኮ ማኅበራት (TPMS) በሊቀ ጳጳሱ አገልግሎት የሚስዮን እና አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናትን በጸሎት እና በበጎ አድራጎት ለመደገፍ የተዘረጋ ዓለም አቀፍ ትሥሥር ነው። እነዚህም የእምነት ማስፋፊያ ማኅበር፣ የሐዋርያው የቅዱስ ጴጥሮስ ማኅበር፣ የሚስዮናውያን የልጅነት ማኅበር (ኤም.ሲ.ኤ)፣ እና የካህናትና የሃይማኖት ሚስዮናውያን ማኅበርን ያካትታሉ።

በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ ጳጳሳዊ ተልእኮ ማኅበራት በእያንዳንዱ አብያተ ክርስቲያናት ፍላጎቶች ላይ ተመስርተው ሀብቶች በፍትሃዊነት እና በእኩልነት እንዲከፋፈሉ በአጥቢያ ጳጳሳት፣ አብያተ ክርስቲያናት እና ሚስዮናውያን ጉባኤዎች በኩል ይሰራሉ። ገንዘቡ በቀጥታ ከዩናይትድ ስቴትስ ወደ ሚሲዮን ግዛቶች ጳጳሳት ይደርሳል፣ ይህም በሁለቱ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ቀጥተኛ ግንኙነት እንዲኖር ያስችላል።

ካርዲናል ፒዬር፥ “የቤተ ክርስቲያንን ሚስዮናዊ ገጽታ እንደገና ማንቃት ያስፈልጋል!”
የጳጳሳዊ ተልእኮ ማሕበር የቦርድ አባል የነበሩት ካርዲናል ፒየር በንግግራቸው የማህበራቱን አስፈላጊነት አፅንዖት ሰጥተው በሰጡት አስተያየት በተለያዩ ሀገራት ውስጥ በንዑስነት ያገለገሉትን የግል ልምዳቸውን አካፍለዋል፣ ከእነዚህም መካከል ብዙዎቹ የጳጳሳዊ ተልእኮ ማሕበር ድጋፍ ተጠቃሚ ሆነዋል ሲሉ ተናግረዋል።

“በዓለም ተልዕኮ ዕለተ ሰንበት ላይ እያዘጋጀን ያለነው ስብስብ ወሳኝ ነው” በማለት አጽንኦት ሰጥተው ሲገልጹ፣ “ይህን የቤተ ክርስቲያን ገጽታ እንደ ሁለንተናዊ ተልእኮ እንደገና ማነቃቃት አለብን፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የመጀመሪያው ሚስዮናዊ በመሆናቸው በእነዚህ ጥረቶች ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን መደገፍ አለብን” ሲሉ ተናግረዋል።

ካርዲናል ታግለ፥ “ለመንፈሳዊ ተልዕኮዎች ጸልዩ!”
ይህ በእንዲህ እንዳለ ብፁዕ ካርዲናል ታግሌ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና
ከስብከተ ወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት የተላከውን ሰላምታ ካደረሱ በኋላ እነዚህን አስተያየቶች አስተላልፈዋል። የኢየሱስ ክርስቶስን የምሥራች ለመካፈል በሚፈልጉ ምእመናን እና ሃይማኖተኛ በሆኑ ሰዎች በተቋቋመው የሚስዮን ማኅበራት መሠረታዊ አመጣጥ ላይ ተመሥርተው አስተያየት የሰጡ ሲሆን፥ "የተልእኮ ማኅበራት ኢየሱስን ለማሳወቅ ባላቸው ጥልቅ መንፈሳዊ ቁርጠኝነት ላይ ነው" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

“የተልእኮ ማኅበራት ኢየሱስን ለማስታወቅ ባለው ጥልቅ መንፈሳዊ ቁርጠኝነት ላይ የተመሰረቱ ናቸው” ያሉት ካርዲናል ታግለ፥ ሚስዮናውያን በእስያ፣ በአፍሪካ፣ በኦሽንያ፣ በአማዞን ክልል እና በላቲን አሜሪካ ሐዋርያዊ ወንጌላውያን ምን እንደሚሠሩ መረጃን በማካፈል በአብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ያለውን የሚስዮናዊነት መንፈስ ማደስ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

ከ1,150 በላይ ግዛቶች
ብፁዕ ካርዲናል ታግለ በዓለም ሚስዮን እለተ ሰንበት ላይ በብዙዎቹ 1,150 ግዛቶች ካጋጠሟቸው ተሞክሮዎች ታሪኮችን አካፍለዋል። "እስያ በዓለም ላይ በሕዝብ ብዛት ዋነኛ አህጉር ነች። ከዓለም ሕዝብ ውስጥ ሁለት ሦስተኛው በእስያ ውስጥ ነው የሚገኘው፣ ነገር ግን በእስያ ውስጥ ከሚገኙት ሕዝቦች መካከል ሦስት በመቶው ብቻ ክርስቲያን ናቸው" በማለት በካምቦዲያ አንድ ምዕመናን ብቻ ያለውን ደብር ሲያስታውሱ እና አምስት ምእመናን ብቻ ካለው የኔፓል አንድ ካኅን ጋር መገናኘታቸውን አስታውሰዋል።

በዓለም የተልዕኮ ዕለተ ሰንበት ላይ የሚተማመኑ
“ከኤሽያ እና ከአፍሪካ የሚመጡ ጳጳሳት ጥሪዎች ይደርሱኛል፣ ብዙ ጊዜ በመጀመሪያዎቹ ሦስት ደቂቃዎች ውስጥ፣ ምንም አይነት ቃል አልሰማም፣ ማልቀስ ብቻ ነው። በዓለም ተልዕኮ እሁድ የሚተማመኑ ናቸው” ያሉት ካርዲናል ታግለ "እነዚህን እውነታዎች እና ታሪኮች ለህዝቦቻችሁ ብታካፍሉ ልባቸው በእሳት እንደሚቃጠል እርግጠኛ ነኝ" ብለዋል። “እነሱም የምሥራቹን አጥብቀው ለሚፈልጉት ብዙ ሰዎች ለማካፈል መርዳት እንደሚፈልጉ አውቃለሁ” ሲሉ አክለው፥ “ከሁሉ የሚበልጠው የምሥራች ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” ብለዋል።


 

24 July 2024, 15:57