ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ እግዚአብሔር ዕለት በዕለት በተአምራቱ የሚያድነን መሆኑን ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሠራቸውን የእንጀራ እና የዓሣ ተአምራትን በሚተርክ የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን አቅርበዋል። ይህን የወንጌል ክፍል መሠረት በማድረግ ባቀረቡት ስብከት፥ ምእመናን በሙሉ ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለት ተዕለት ጸጋዎቹ የሚባርከንን መንገድ በመገንዘብ እንዲያመሰግኑት አደራ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ ሐምሌ 21/2016 ዓ. ም. የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ለማቅረብ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ባሰሙት ስብከት፥ ኢየሱስ በመጨረሻው እራት ላይ የደገማቸውን ሦስቱ ምልክቶች በማስታወስ እነርሱም መባ፣ ምስጋናን ማቅረብ እና ማካፈል እንደሆኑ ገልጸው፥ በእያንዳንዱ ላይ ከማሰላሰላቸው በፊት ሁሉም በቅዱስ ቁርባን ላይ የተከናወኑ ድርጊቶች መሆናቸውን አስረድተዋል።

መባን ማቅረብ፣ ማመስገን እና መካፈል
በቅድሚያ ስለ መባ የተናገሩት ቅዱስነታቸው፥ ሁላችንም ለእግዚአብሔር የምንሰጠው መልካም ነገር እንዳለን በማመን ምንም እንኳን የምንሰጠው ከሚፈለገው ጋር ሲወዳደር በጣም ጥቂት ነው” ብለዋል። ይህም ካህኑ በመስዋዕተ ቅዳሴ ወቅት ኅብስቱን እና ወይኑን በመሠዊያው ላይ ሲያቀርብ እያንዳንዱ ሰው ራሱን እና ሕይወቱን ለእግዚአብሔር የሚያቀርብ መሆኑን አጽንዖት ተሰጥተዋል።

“የሰውን ልጅ ግዙፍ ፍላጎት ስናስብ ትንሽ ሊመስል ቢችልም፣ አምስት እንጀራ እና ሁለት ዓሳ በብዙ ሺህ ሕዝብ ፊት ትንሽ ቢመስልም ኢየሱስ ክርስቶስ በተአምራቱ ዓለምን ለማዳን በእኛ መካከል ራሱን አቀረበ” ብለዋል።

"የእኛ ደካማው ፍቅር"
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ምስጋና ማቅረብን በማስመልከት ሲናገሩ፥ “እግዚአብሔር እንዴት እንደባረከን በመገንዘብ ልንደሰት ይገባል” ብለዋል። ለእግዚአብሔር በትህትና እና በደስታ ልንነግረው የሚገባን፥ “ያለኝ ሁሉ ያንተ ስጦታ ነው፣ አንተን እንዳመሰግንህ መጀመሪያ የሰጠኸኝ ልጅህን ኢየሱስ ክርስቶስን በመሆኑ ልመልስልህ የምችለው 'ደካማ ፍቅሬን' ብቻ ነው ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህ ጊዜ እግዚአብሔርን ስለ ቸርነቱ የምናመሰግንበት 'የበረከት' ጊዜ እንደሆነ አስገንዝበው፥ እርሱ ሲቀድሰን እና ደካማ ጥረታችንን እንደ 'ሁለት የመዳብ ሳንቲሞች' ሲያበዛልን ልናመሰግነው ይገባል ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጨረሻም ወደ ሦስተኛው ምልክት ወደ ሆነው “መካፈል” በመዞር በመስዋዕተ ቅዳሴ ወቅት የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ እና ደም ለመቀበል አብረን ወደ መሠዊያው ስንቀርብ የሰው ሁሉ የጸጋ ፍሬ ለሁሉ ምግብ እንዲሆን መለወጡን አስታውሰዋል።

ይህም እያንዳንዱ የፍቅር ምልክት እንደ ጸጋ ስጦታ እንድንኖር የሚያስተምረን አስደሳች ጊዜ እንደ ሆነ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አድረድተው፥ የሚሰጡትም ሆኑ የሚቀበሉት እንደ ወንድሞች እና እህቶች አብረው የሚያድጉበት የበለጠ በበጎ አድራጊነት የሚያድጉበት ነው” ብለዋል።

ሊታሰብባቸው የሚገቡ አንዳንድ ጥያቄዎች
ቅዱስነታቸው ይህንን በማሰብ እንዲተባበሯቸው በማለት ምዕመናን ራሳቸውን አንዳንድ ጥያቄ እንዲጠይቁ ጋብዘዋል። “በእግዚአብሔር ቸርነት ለወንድሞቼ እና ለእህቶቼ የምሰጠው ልዩ ነገር እንዳለኝ በእውነት አምናለሁ? ወይስ ማንነቴ ሳይገለጽ ከብዙዎች መካከል አንዱ እንደሆንኩ ይሰማኛል? በተጨማሪም ጌታ ፍቅሩን ስለሚገልጥባቸው የማያቋርጡ ስጦታዎች አመሰግነዋለሁ? የምኖረው ያለኝን ከሌሎች ጋር በመካፈል በጋራ ለማደግ ነው?" በማለት ራሳቸውን እንዲጠይቁ አደራ ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጨረሻም፣ እያንዳንዱን የቅዱስ ቁርባን ሥነ-ሥርዓት በእምነት እንድንኖር እና በየዕለቱ የእግዚአብሔርን አዳኝ የጸጋ ተአምራትን መገንዘብ እንድንችል እናቱን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን በመማጸን ስብከታቸውን አጠቃልለዋል።

 

29 July 2024, 17:15