ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የወጣቶች ሐዋርያዊ አገልግሎት ዓለም አቀፍ ጉባኤ ተሳታፊዎችን ሲያገኟቸው ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የወጣቶች ሐዋርያዊ አገልግሎት ዓለም አቀፍ ጉባኤ ተሳታፊዎችን ሲያገኟቸው  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “ማኅበረሰብ የሚገነባው በወጣቶች እና በአረጋውያን ጥምረት ነው!”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ ካቶሊክ ምዕመናን ዘንድ ሐምሌ 19/2015 ዓ. ም የሚከበረውን የቅድስት ድንግል ማርያም ወላጆች እና የኢየሱስ ክርስቶስ አያቶች፥ የቅዱስ ኢያቄም እና የቅድስት ሐና ዓመታዊ በዓልን በማስመልከት መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው በዚህ መልዕክታቸው፥ “ማኅበራዊ ወዳጅነት የሚገነባው በወጣቶች እና በአረጋውያን መካከል ባለው ጥምረት ነው!” ሲሉም አስገንዝበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከበዓሉ ዕለት ቀደም ብለው፥ “@Pontifex” በሚለው በ “ኤክስ” ማኅበራዊ ገጻቸው አማካይነት ረቡዕ ዕለት ባስተላለፉት መልዕክት፥ የፊታችን እሑድ ሐምሌ 21/2016 ዓ. ም. የአያቶች እና የአረጋውያን ዓለም አቀፍ ቀን የሚከበር መሆኑን አስታውሰው፥ የወንድማማችነት ማኅበረሰብን መገንባት የሚቻለው ከአረጋውያን የሕይወት ውበት በመማር እንደሆነ አስረድተዋል።

የኢየሱስ ክርስቶስ አያቶች
የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ በ1961 ዓ. ም. አዲሱን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ግጻዌ ይፋ ባደረጉበት ወቅት፥ ሐምሌ 19 የኢየሱስ ክርስቶስ አያቶች የቅዱስ ኢያቄም እና የቅድስት ሐና መታሰቢያ ዕለት እንዲሆን ማወጃቸውን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስታውሰዋል። ቀደም ሲል የእነዚህ ሁለቱ የኢየሱስ ክርስቶስ አያቶች መታሰቢያ ዕለት በተለያዩ ቀናት እንደሚከበር፥ የቅድስት ሐና መታሰቢያ ዕለት ሐምሌ 19 ሲሆን የቅዱስ ኢያቄም ነሐሴ 10 እንደ ነበር ይታወሳል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ሐምሌ 26/2013 ዓ. ም. በብራዚል ሪዮ ዴ ጄኔሮ ሐዋርያዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕከት፥ ቅዱስ ኢያቄም እና ቅድስት ሐና እግዚአብሔርን ማፍቀር እና እርሱን ማመንን ለሌሎች የማስተላለፍ የረጅም ጊዜ ታሪክ አካል እንደሆኑ አስረድተው፥ ቅድስት ድንግል ማርያም የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስን በማኅጸኗ ተሸክማ ለዓለም በሙሉ በስጦታነት ማበርከቷን አስታውሰው፥ “ዋናው የቤተሰብነት እሴት እምነትን ለሌሎች ማስተላለፍ በመሆኑ ልዩ ቦታ ይሰጠዋል” በማለት አክለዋል።

ዓለም አቀፍ የአያቶች እና አረጋውያን ቀን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለዘንድሮው ዓለም አቀፍ የአያቶች እና አረጋውያን ቀን የመረጡት መሪ ጥቅስ፥ “በእርጅናዬ ዘመን አትጣለኝ፥ ጕልበቴም ባለቀ ጊዜ አትተወኝ” (መዝ. 71፡9) የሚል ሲሆን፥ ቅዱስነታቸው በዚህ ጥቅስ አማካይነት ብቸኝነት የብዙዎችን ሕይወት መራራ የሚያደርግ መሆኑን ለማስመር ያለሙ ሲሆን፥ ብዙውን ጊዜ አረጋውያን የብቸኝነት ባሕል ሰለባ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።

በዘፍ. 2፡18 ላይ፥ “ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም” የሚለውን ጥቅስ ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በዘንድሮው ዓለም አቀፍ የአያቶች እና የአረጋውያን ቀን መልዕክታቸው፥ “እግዚአብሔር ልጆቹን ፈጽሞ አይጥልም” ሲሉ አስምረውበት፥ “አሮጌ ድንጋይ አይጠቅምም ተብሎ እንደማይጣል ነገር ግን መንፈሳዊውን ሕንፃ በጋራ ለመገንባት የሚያስችል አስተማማኝ መሠረት ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

ዮሐንስ ጳውሎስ ቀዳማዊ፥ “የአረጋውያንን ልብ እናስብ!”

የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ብጹዕ ዮሐንስ ጳውሎስ ቀዳማዊ ከሐዋርያዊ አገልግሎታቸው ጋር በተያያዘ አረጋውያን በኅብረተሰቡ ውስጥ ባላቸው ሚና ላይ በማትኮር እንደ ጎርጎሮሳውያኑ መስከረም 6/1978 ዓ. ም. ባቀረቡት የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው፥ አረጋውያንን መመገብ እና ማልበስ ብቻውን በቂ እንዳልሆነ ነገር ግን ምንም እንኳን አረጋውያን ቢሆኑም ከልብ መውደድ እና ማክበር እንደሚገባ እግዚአብሔር ማዘዙን አስታውሰዋል።

ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፥ “አረጋዊ መሆን መታደል ነው!”

“የአረጋውያን የመጨረሻዎቹ የሕይወት ደረጃዎች እንኳ ዋጋ ያላቸው እና በክብር የተሞሉ ናቸው” ያሉት የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ መጋቢት 23/1984 ዓ. ም. ለአረጋውያን ባሰሙት ንግግር፥ አረጋዊ መሆን ትልቅ መብት እንደሆን በማሳሰብ፥ “እናንተ ከሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች እና ባሕሎች የተወጣጣችሁ ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ! የአረጋውያን ምድብ ሆናችሁ ልዩነቶችን በማስወገድ ለሰው ልጅ በሚሰጥ ልዩ ክብር ወንድማማቾች ሆናችኋል” ብለዋል።

ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በማከልም፥ “ወደ እርጅና መግባት እንደ ልዩ መብት ሊቆጠር የሚገባው፣ ወደዚህ ግብ ለመድረስ ሁሉ ሰው ዕድለኛ ስላልሆነ ብቻ ሳይሆን ከሁሉም በላይ ያለፈውን ጊዜ በተሻለ ሁኔታ ለማጤን እና በጥልቀት ለመኖር ተጨባጭ ዕድሎች ያሉበት፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለሁሉም የእግዚአብሔር ሰዎች ምሳሌ የመሆን የፋሲካ ምስጢር ነው” በማለት አስገንዝበዋል።

በነዲክቶስ 16ኛ፥ “የአረጋውያን ጥበብ ሃብት ነው!”

“አረጋውያንን መቀበል ማለት ሕይወትን መቀበል ማለት ነው” ያሉት የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ኅዳር 12/2012 ዓ. ም. አንድ የአረጋውያን መንከባከቢያ ማዕከልን በጎበኙበት ወቅት ባሰሙት ንግግር፥ “የዕድሜ ባለጸግነት የእግዚአብሔር በረከት እንደሆነ ስለሚቆጠር ዛሬ ይህ በረከት የተስፋፋ በመሆኑ ሊመሰገን እና ሊወደስ የሚገባ ስጦታ ነው” ብለዋል። ብዙውን ጊዜ በችሎታ እና በትርፍ የሚያምን ማኅበረሰብ የዕድሜ ባለጸግነትን እንደ ስጦታ እንደማይቀበል፣ አረጋውያን ምርታማ እንዳልሆኑ እና እንደማይጠቅሙ አድርጎ የሚቆጥራቸው እንደሆነ ተናግረዋል።

አረጋውያን ብዙውን ጊዜ ከማኅበረሰብ የተገለሉ፣ ከቤታቸው ርቀው የሚኖሩ ወይም የብቸኝነት ስቃይ የሚሰማቸው በመሆኑ ወደ ሌላ ሥፍራ ሳይወሰዱ በቤታቸው ውስጥ እንዲቆዩ ለማድረግ ከቤተሰብ እና ከመንግሥት ተቋማት ጀምሮ ትልቅ ሥራ መሰራት እንደሚገባ አደራ ብለው፥ የአረጋውያን የሕይወት ልምድ እና ጥበብ ትልቅ ሃብት እንደሆነ፥ የአንድ ማኅበረሰብ ጥራት እና ሥልጣኔ የሚለካው ለአረጋውያን በሚደረግ እንክብካቤ እና ለጋራ ሕይወት በሚሰጠው ቦታ እንደሆነ በመግለጽ፥ “ለአረጋውያን ቦታ የሚሰጥ ለሕይወት ቦታ ይሰጣል፣ አረጋውያንን የሚቀበል ሕይወትን ይቀበላል” በማለት አስረድተዋል።

“በማኅበረሰባችን ውስጥ የንቀት ባሕል እየጨመረ መጥቷል ያሉት” ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ አረጋውያን ብዙውን ጊዜ ወደ ጎን እንደሚባሉ፣ በብቸኝነት ሕይወት እንደሚጠቁ እና አቅመ ደካማነታቸውን ተገን በማድረግ የሚጠቀሙባቸው ሰዎች መኖራቸውንም አስታውሰዋል። ብዙ ሰዎች በእርጅና ዘመናቸው የማጭበርበር እና የማታለል ወንጀሎች ሰለባ እንደሚሆኑ እና የሕመም ስቃይ ጩኸታቸው ተደማጭነትን እንደማያገኝ ነገር ግን በእነዚህ ‘አሮጌ እና ተሰባሪ ድንጋዮች’ ላይ የኅብረተሰቡ የወደፊት ዕጣ ፈንታ እንደሚገነባ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስረድተዋል።

 

25 July 2024, 14:27