ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በኢትዮጵያ ለነቀምቴ ሀገረ ስብከት አዲስ ጳጳስ ሰየሙ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ክቡር አባ ጌታሁን ፋንታ በነቀምቴ ሀገረ ስብከት፣ ምዕራብ ወለጋ ውስጥ አለኩ ሳሲ በተባለች መንደር የካቲት 18/1965 ዓ. ም ተወልደዋል።
አዲስ አበባ በሚገኝ የማኅበራቸው ዘርዓ ክህነት ትምህርት ቤት ገብተው በቅዱስ ፍራንችስኮስ መንፈሳዊ ትምህርት ማዕከል የሚሰጡ የፍልስፍና እና የነገረ-መለኮት ትምህርቶችን ከተከታተሉ በኋላ ሰኔ 24/1993 ዓ. ም. የክኅነት ማዕረገ ተቀብለዋል።
ለከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት ወደ ሰሜን አሜሪካ ተልከው ቺካጎ ከሚገኝ ቅዱስ ቪንሴንት ዴፖል ዩኒቨርሲቲ በሰው ሃብት የማስተርስ ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል።
ክቡር አባ ጌታሁን ፋንታ ለቤተ ክርስቲያን ካበረከቷቸው ሐዋርያዊ አገልግሎቶች መካከል በነቀምቴ ሀገረ ስብከት ለሳኮ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን እና ለሜጫ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቁምስና መሪ ካኅን ሆነው አገልግለዋል።
የማኅበራቸው ከፍተኛ የዘርዓ ክኅነት ትምህርት ቤት ዋና አለቃ ሆነው ከማገልገላቸው በተጨማሪ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ የላዛሪስት ማኅበር የበላይ አለቃ በመሆን ለሁለት የኃላፊነት ጊዜያት (ከ 2002-2005 እና ከ 2005-2008) አገልግለዋል።
ክቡር አባ ጌታሁን ፋንታ በተጨማሪም አዲስ አበባ የሚገኝ የጽዮን ማርያም ቁምስና መሪ ካኅን ሆነው ያገለገሉ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም በአዲስ አበባ የሚገኝ የላዛሪስት ትምህርት ቤት ዳይሬክተር እና በኢትዮጵያ የፍቅር ሥራ እህቶች ማኅበር መንፈሳዊ መሪ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ።