ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለሐምሌ ወር ባቀረቡት የጸሎት ሐሳብ ሕሙማንን ማስታወስ እንደሚገባ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ቅዱስነታቸው ሰኔ 25/2016 ዓ. ም. በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ አውታረ-መረብ በኩል ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት፥ በከባድ ሕመም ውስጥ ለሚገኙት ሰዎች የሚሰጥ የቀንዲል ምስጢር ለታመሙት በሙሉ የእግዚአብሔርን ኃይል እና ጥንካሬ በመስጠት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የርህራሄ እና የተስፋ ምልክት እንዲሆናቸው መጸለይ እንደሚገባ አደራ ብለዋል።
መጽናናትን እና ተስፋን መስጠት
ካህን ለታመ ሰው የቀንዲል ምስጢር ለመስጠት ሲቀርብ፣ በሕይወት ፍጻሜ ወቅት የሚሰጥ ዕርዳታ ብቻ ሆኖ መወሰድ እንደሌለበት ተናግረው፥ በዚህ መንገድ ማሰብ ተስፋን በሙሉ የሚያስቆርጥ መሆኑን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቪዲዮ መልዕክታቸው መጀመሪያ ላይ ተናግረዋል።
“የቤተ ክርስቲያን ምስጢራት በሙሉ ስጦታዎች፣ ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ሊባርከን፣ ሊያበረታታን፣ ከእኛ ጋር ሆኖ ሊያጽናና የሚጠቀምባቸው መንገዶች ናቸው” ብለው፥ ካህን ምስጢር ቀንዲልን በመስጠት እኛን እና ቤተሰቦቻችንን ለመርዳት እንዲሁም የታመሙትን ለማጽናናት እንደሚመጣ ቤተ ክርስቲያን ታምናለች ብለዋል።
ምስጢረ ቀንዲል ማኅበረሰብ ገጽታ ያለው ምስጢር ነው
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መላው ቤተ ክርስቲያን እንዲጸልይ ያቀረቡት ጥሪ፥ ለሕሙማን የሚሰጥ ምሥጢረ ቀንዲል በባሕርው ማኅበረሰባዊ እና ተያያዥነት እንዳለው የሚታይበት መንገድ እንደሆነ አስረድተዋል።
“በሕመም እና በስቃይ ወቅት ብቻችንን እንዳልሆንን ማወቅ ዘወትር መልካም ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ አንድ የታመመ ሰው ምስጢረ ቀንዲልን ሲቀበል በሥፍራው የሚገኙት ካህን እና ምዕመናን የክርስቲያን ማኅበረሰብን በመወከል በታማሚው ዙሪያ በመሰባሰብ እምነታቸውን እና ተስፋቸውን በማሳደግ በጸሎታቸው የሚያግዙ መሆናቸውን፥ ይህን ምስጢር በማስመልከት ያቀረቡትን የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተህሮአቸውን ለተከታተሉት በሺዎች ለሚቆጠሩ ምእመናን አረጋግጠዋል።
የኢየሱስ ክርስቶስ ቅርበት የሚገለጥበት ምስጢር
ለሕሙማን ወይም ለአረጋውያን የሚሰጥ ይህ ቅዱስ ምስጢር ኢየሱስ ክርስቶስ ለሕመማቸው እፎይታን እና ለኃጢአታቸው ስርየትን እንደሚሰጥ ዋስትና የሚሆን ቢሆንም ነገር ግን ከፈውስ ተአምር ጋር ተመሳሳይነት የለውም። ለሕሙማን የሚሰጥ ይህ ቅዱስ ምስጢር ብዙውን ጊዜ የተረሳ ወይም የማይታወቅ እንደሆነ ቅዱስነታቸው ተናግረው፥ ቢሆንም የታመሙትን ከሕመማቸው ሊገላግላግል፣ ኃይልን ሊሰጣቸው፣ ተስፋ ሊሆናቸው እና ሊረዳቸው እንዲሁም ኃጢአታቸውን ይቅር ሊላቸው የሚመጣው ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ እንደሆነ በመግለጽ ለሕሙማን የሚሰጥ የሐዋርያዊ አገልግሎት ጠቀሜታን አስረድተዋል።
ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክቶች ጋር አብረው የተላኩ ምስሎች በሁለቱ የሰሜን አሜሪካ ሀገረ ስብከቶች ማለትም በፔንሲልቫኒያ ከአሌንታውን ሀገረ ስብከት እና በካሊፎርኒያ ከሎስ አንጀለስ ሀገረ ስብከቶች የተሰብሰቡት የቪዲዮ ምስሎች ምስጢረ ቀንዲል የሚፈጸምባቸውን የተለያዩ አውዶች የሚያስዩ ናቸው። በሎስ አንጀለስ ሀገረ ስብከት የባለሙያዎች ቡድን ተዘጋጅቶ የቀረበው የቪዲዮ ምስሎች በታማሚው ሰው ዕድሜ እና በሕክምናው ዘርፍ ላይ ያሉ ሁለት የተለያዩ ታሪኮችን በማዛመድ የሚያሳይ፣ ምስጢረ ቀንዲልን በሚቀበል ታማሚ እና በቤተሰቡ መካከል ያለውን ታላቅ ፍቅር አንድ ላይ በማድረግ የሚያሳይ እንደሆነ ተመልክቷል።
በቅዱስ ወንጌል ብርሃን በመታገዝ የታመሙን ሰዎች መቀባት
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዓለም አቀፍ የጸሎት አውታረ መረብ አስተባባሪ አባ ፍሬደሪክ ፎርኖስ፥ የቅዱስነታቸውን መልዕክት በማስመልከት በስጡት አስተያየት፥ ብዙዎች የምስጢረ ቀንዲልን ጥልቀት ቢያውቁትም፥ ሕሙማን ለሞት የሚያዘጋጁበት መንገድ እንደሆነ ይገነዘቡታል ብለው፥ አንድ ሰው በጠና ሲታመም የቀንዲል ምስጢር ለመስጠት ጊዜ መውሰድ እንደምንፈልግ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መናገራቸውን በማስታወስ፥ ይህ ከመሆን ይልቅ የዚህን ምስጢር ሙሉ ጥልቀት እና ትክክለኛ ትርጉም እንደገና በማወቅ፥ አንድ በጠና የታመመ ሰው ለሞት ሲዘጋጅ ብቻ የሚሰጥ ሳይሆን ታማሚውን የሚያጽናና እና ለቤተሰቦቹም ጭምር ብርታትን የሚሰጥ ምስጢር መሆኑ አስረድተዋል
የታመመ ሰው ብቻውን አለመሆኑን፣ በአጠገቡ የሚገኙ ሰዎች ከካህኑ ጋር በመሆን መላው የክርስቲያን ማህበረሰብ በመወከል ግለሰቡን በጸሎታቸው በመደገፍ እምነታቸውን እና ተስፋቸውን በማሳደግ ለቤተሰባቸውም ጭምር በመከራቸው ውስጥ ብቻቸውን እንዳልሆኑ የሚያረጋግጡበት በመሆኑ ሕሙማንን እና አረጋውያንን በጸሎት ከመደገፍ ወደኋላ አንበል በማለት፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዓለም አቀፍ የጸሎት አውታረ መረብ አስተባባሪ አባ ፍሬደሪክ ፎርኖስ መል ዕክታቸውን ደምድመዋል።