ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ  በፓፗ ኒው ጊኒ፣ በኢንዶኔዥያ ፣ በምሥራቅ ቲሞር እና በሲንጋፖር የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ዓርማ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በፓፗ ኒው ጊኒ፣ በኢንዶኔዥያ ፣ በምሥራቅ ቲሞር እና በሲንጋፖር የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ዓርማ 

የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የእስያ እና የኦሼኒያ አኅጉራት ሐዋርያዊ ጉብኝቶች መርሃ ግብር ይፋ ሆነ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከሰኞ ነሐሴ 27/2016 እስከ መስከረም 3/2017 ዓ. ም. በእስያ እና ኦሼኒያ አኅጉራት ሐዋርያዊ ጉብኝት እንደሚያደርጉ የቅድስት መንበር በመግለጫ አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ቅዱስነታቸው ከሁለት ሳምንታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በሁለቱ አህጉራት ውስጥ የሚገኙ አራት አገራትን እነርሱም ኢንዶኔዥያን፣ ሲንጋፖርን፣ ፓፑዋ ኒው ጊኒን እና ቲሞር-ሌስቴ እንደሚጎበኟቸው የቅድስት መንበር መግለጫ ገልጾ፥ ይህም ቅዱስነታቸው ከጣሊያን ውጭ የሚያደርጉት 45ኛው ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝት እንደሆነ የቅድስት መንበር መግለጫ አስታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ነሐሴ 27/2016 ዓ. ም. ከሮም ተነስተው በቅድሚያ ወደ ኢንዶንሴዥያ መዲና ጃካርታ እንደሚደርሱና ከዚያም ጳጉሜ 1/2016 ዓ. ም. ወደ ፖርት ሞርስቢ በመጓዝ የፓሲፊክ ውቅያኖስ ደሴት በሆነች ፓፑዋ ኒው ጊኒ ውስጥ የሚገኙ ካቶሊካዊ ምዕመናንን እንደሚጎበኙ እና በዚያም እስከ ጳጉሜ 4/2016 ዓ. ም. ድረስ እንደሚቆዩ የጉብኝታቸው መርሃ ግብር አመልክቷል።

ቅዱስነታቸው ከዚያ ተነስተው የቲሞር ሌስቴ ዋና ከተማ ወደሆነች ዲሊ እንደሚጓዙ እና ከዲሊ በመነሳት ከመስከረም 1-3/2017 ዓ. ም. ድረስ ባሉት ቀናት የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው የመጨረሻ አገር ሲንጋፖርን ከጎበኟት በኋላ ወደ ሮም እንደሚመለሱ የጉብኝታቸው መርሃ ግብር አመልክቷል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሰኞ ነሐሴ 27/2016 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ ከሮም ፊውሚቺኖ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ ተነስተው ነሐሴ 28/2016 ዓ. ም. ጠዋት ወደ ኢንዶኔዥያ መዲና ጃካርታ ሶካርኖ-ሃታ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ይፋዊ አቀባበል እንደሚደረግላቸው ታውቋል።

ነሐሴ 29/2016 ዓ. ም. ጠዋት በመዲናዋ ጃካርታ በሚገኝ ፕሬዝደንታዊ ቤተ-መንግሥት ውስጥ ለርዕሠ ሊቃነ ፍራንችስኮስ አቀባበል ከተደረገላቸው በኋላ በኢስታና መርዴካ ፕሬዝዳንታዊ ቤተ መንግሥት ውስጥ ከአገሪቱ ፕሬዝዳንት ከክቡር አቶ ጆኮ ዊዶዶ ጋር እንደሚገናኙ ታውቋል።

ቅዱስነታቸው ቀጥለውም ረፋዱ ላይ በፕሬዝዳንታዊ ቤተ መንግሥት የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ተገኝተው ለባለ ሥልጣናት፣ ለሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮች እና ለልዩ ልዩ አገራት ዲፕሎማሲያዊ አካላት ንግግር እንደሚያደርጉላቸው ታውቋል። በአገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር ከረፋዱ አምስት ሰዓት ተኩል ላይ በመዲናይቱ በሚገኝ የቅድስት መንበር እንደራሴ ጽሕፈት ቤት ውስጥ ከኢየሱሳውያን ማኅበር አባላት ጋር የግል ስብሰባ እንደሚያደርጉ ታውቋል።

ከሰዓት በኋላ በስምንት ሰዓት ተኩል ላይ ከአገሪቱ ብጹዓን ጳጳሳት፣ ከካህናት፣ ከዲያቆናት፣ ከገዳማውያን እና ገዳማውያት፣ ከዘርዓ ክኅነት ተማሪዎች እና የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን ጋር በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ካቴድራል ውስጥ ተገናኝተው ንግግር ካደረጉ በኋላ በአሥራ አንድ ሰዓት ከሰላሳ አምስት ደቂቃ ላይ ጃካርታ ውስጥ በሚገኝ የወጣቶች ማዕከል ውስጥ “ኦከረንት” ትምህርት ቤት ውስጥ ከወጣቶች ጋር እንደሚገናኙ ታውቋል።

መስከረም 30/2016 ዓ. ም. ጃካርታ ውስጥ በሚገኝ የኢስቲቂላል መስጊድ ውስጥ ከልዩ ልዩ የሃይማኖት ተቋማት ተወካዮች ጋር ከተገናኙ በኋላ በኢንዶኔዥያ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ውስጥ ከዕርዳታ ድርጅት ተወካዮች ጋር እንደሚገናኙ ታውቋል።

ቅዱስነታቸው መስከረም 30/2016 ዓ. ም. በኢንዶኔዥያ መዲና ጃካርታ በሚገኝ ስታዲየም ከአሥራ አንድ ሰዓት ጀምሮ የሚቀርብ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት እንደሚመሩ ታውቋል።

ቅዱስነታቸው በኢንዶኔዥያ መዲና ጃካርታ ውስጥ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ፈጽመው ዓርብ ጳጉሜ 1/2016 ዓ. ም. ጠዋት ወደ ፖርት ሞርስቢ ከመጓዛቸው በፊት በጃካርታ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ ሽኝት እንደሚደረግላቸው እና በተመሳሳይ ዕለት ማምሻውን ወደ ፖርት ሞርስቢ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ ስደርሱ አቀባበል እንደሚደረግላቸው ታውቋል።

ቅዱስነታቸው ቅዳሜ ጳጉሜ 2/2016 ዓ. ም. ጠዋት ከጠቅላይ ገዥው ጋር በቤተ መንግሥት ውስጥ ከተገናኙ በኋላ ከባለስልጣናት፣ ከሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮች እና ከዲፕሎማሲ አካላት ጋር ተገናኝተው ንግግር እንደሚያደርጉላቸው ታውቋል። ቀጥለውም በካሪታስ የዕርዳታ ድርጅት የሞያ ማሰልጠኛ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ውስጥ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ ከጎዳና ላይ የተሰበሰቡ ልጆችን ከጎበኟቸው በኋላ ከቀኑ አሥራ አንድ ሰዓት ላይ ከፓፑዋ ኒው ጊኒ እና ከሰሎሞን ደሴቶች ካቶሊክ ብጹዓን ከጳጳሳት፣ ካህናቶች፣ ዲያቆናት፣ ገዳማውያን እና ገዳማውያት፣ ከዘርዓ ክኅነት ተማሪዎች እና ከትምህርተ ክርስቶስ መምህራን ጋር በቅድስት ድንግል ማርያን የክርስቲያኖች ረድኤት ቤተ መቅደስ ውስጥ ተገናኝተው ንግግር እንደሚያደርጉላቸው ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ ጳጉሜ 3/2016 ዓ. ም. ጠዋት በፖርት ሞርስቢ ከአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር በሐዋርያዊ እንደራሴ ጽሕፈት ቤት ውስጥ ከተገናኙ በኋላ በጆን ጊዝ ስታዲየም ውስጥ የሚቀርበውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት እንደሚመሩ ታውቋል። ቅዱስነታቸው ቀጥለውም በአውሮፕላን ወደ ቫኒሞ በመጓዝ ከሰዓት በኋላ ከሀገረ ስብከቱ ካቶሊካዊ ምዕመናን ጋር በቅዱስ መስቀል ካቴድራል ውስጥ ተገናኝተው ንግግር እንደሚያደርጉላቸው ታውቋል። ቀጥለውም በቅዱስ ሥላሴ ትምህርት ቤት ውስጥ ከልዩ ልዩ ሚሲዮናውያን ጋር የግል ውይይት ካደረጉ በኋላ ወደ ፖርት ሞርስቢ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ እንደሚመለሱ ታውቋል።

ጳጉሜ 4/2016 ዓ. ም. በዲሊ ጆን ጊስ ስታዲየም ውስጥ ለውጣቶች መልዕክት ካስተላለፉ በኋላ ከፖርት ሞርስቢ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተነስተው ወደ ዲሊ ሲደርሱ ፕሬዝዳንት ኒኮላ ሎባቶ ይፋዊ አቀባበል እንደሚያደርጉላቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው ከፕሬዝዳንቱ ጋር በቤተ መንግሥት ውስጥ ከተገናኙ በኋላ በሥፍራው ለተገኙት ባለሥልጣናት፣ ለሲቪል ማኅበራት ተወካዮች እና ለዲፕሎማሲያዊ አካላት ንግግር እንደሚያደርጉላቸው ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ማክሰኞ ጳጉሜ 5/2016 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ ዲሊ ውስጥ በኢርማስ አልማ ትምህርት ቤት የሚገኙ አካል ጉዳተኛ ልጆችን ከጎበኟቸው በኋላ ከብጹዓን ጳጳሳት፣ ከካህናት፣ ከዲያቆናት፣ ከገዳማውያን እና ገዳማውያት፣ ከዘርዓ ክኅነት ተማሪዎች እና ከትምህርተ ክርስቶስ መምህራን ጋር በእመቤታችን ንጽሕት ድንግል ማርያም ካቴድራል ተገናኝተው ንግግር እንደሚያደርጉላቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው በመቀጠልም ከኢየሱሳውያን ማኅበር አባላት ጋር በሐዋርያዊ እንደራሴ ጽሕፈት ቤት ውስጥ የግል ስብሰባ ካደረጉ በኋላ ከቀኑ አሥር ሰዓት ተኩል ላይ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት እንደሚመሩ ታውቋል።

ቅዱስነታቸው ርቡዕ መስከረም 1/2017 ዓ. ም. ጠዋት ወደ ሲንጋፖር ከመጓዛቸው በፊት በዲሊ ዓለም አቀፍ አውሮፕላ ማረፊያ ፕሬዝደንት ኒኮላ ሎባቶ ሽኝት እንደሚደርጉላቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው በተመሳሳይ ዕለት ከሰዓት በኋላ ወደ ሲንጋፖር ቻንጊ ዓለም አቀፍ አውሮፕላ ማረፊያ ሲደርሱ ይፋዊ አቀባበል እንደሚደረግላቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው ቀጥለውም በቅዱስ ፍራንሲስ ዛቪዬር የሱባኤ ማዕከል ከኢየሱሳውያን ማኅበር አባላት ጋር እንደሚገናኙ ታውቋል።

ቅዱስነታቸው ሐሙስ መስከረም 2/2017 ዓ. ም. ረፋዱ ላይ በአገሪቱ ፓርላማ ውስጥ አቀባበል ከተደረገላቸው በኋላ ከአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ተገናኝተው በሲንጋፖር ብሔራዊ ዩኒቨርሲቲ የባህል ማዕከል ውስጥ ከባለ ሥልጣናት፣ ከሲቪል ማኅበራት ተወካዮች እና ከዲፕሎማሲያዊ አካላት ጋር ተገናኝተው ንግግር እንደሚያደርጉላቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው ከሰዓት በኋላ በአሥራ አንድ ከሩብ ላይ በሲንጋፖር ብሔራዊ ስታዲየም የተዘጋጀውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት እንደሚመሩ ታውቋል።

ቅዱስነታቸው ዓርብ መስከረም 3/2017 ዓ. ም. በቅድስት ቴሬዛ ማዕከል የሚገኙ አረጋውያንን እና ሕሙማንን ከጎበኟቸው በኋላ ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ በካቶሊካዊ መለስተኛ ኮሌጅ ውስጥ በተዘጋጀው የሃይማኖት ተቋማት ተወካዮች ስብሰባ ላይ ተገኝተው ለወጣቶች መልዕክት እንደሚያስተላልፉ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዓርብ መስከረም 3/2017 ዓ. ም. በአገሪቱ ሰዓት ከረፋዱ አምስት ሰዓት ከሃያ ላይ የስንብት ሥነ-ሥርዓት ከተደረገላቸው በኋላ በአምስት ሰዓት ከሃምሳ ላይ ከሲንጋፖር ቻንጊ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተነስተው ወደ ሮም-ፊዩሚቺኖ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በአሥራ ሁለት ሰዓት ከሃያ አምስት ደቂቃ ላይ እንደሚደርሱ የ45ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መርሃ ግብር አስታውቋል።

 

06 July 2024, 16:55