በቦስኒያ እና ሄርዞጎቪና ሜጁጎሪ ላይ ለሦስተኛ ጊዜ የተዘጋጀ የወጣቶች ፌስቲቫል በቦስኒያ እና ሄርዞጎቪና ሜጁጎሪ ላይ ለሦስተኛ ጊዜ የተዘጋጀ የወጣቶች ፌስቲቫል   (Radio Medjugorje Mir)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ወጣቶች እንደ ቅድስት ድንግል ማርያም እውነተኛ ደቀ መዝሙር እንዲሆኑ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሜጁጎሪ በተዘጋጀው ፌስቲቫል ላይ ለተገኙት ወጣቶች መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው ወጣቶች የእግዚአብሔርን ቃል በመቀበል እና ተልዕኳቸውን በታማኝነት በመወጣት ቅድስት ድንግል ማርያምን እንዲመስሉ አደራ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከሐምሌ 25-30 /2016 ዓ. ም. ድረስ በሚከበረው 35ኛ የሜጁጎሪ የወጣቶች ፌስቲቫል ተሳታፊዎች ዓርብ ሐምሌ 26/2016 ዓ. ም. መልዕክት ልከዋል። ቅዱስነታቸው “ማርያም የተሻለውን መርጣለች” በሚለው የፌስቲቫሉ መሪ ቃል ላይ በማስተንተን ለወጣቶች መልዕክት ማስተላለፍ በመቻላቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፥ በወጣቶች መንፈሳዊ ዕድገት፣ በቤተ ክርስቲያን እና በዓለም አቀፍ ቁርጠኝነት ላይ ያተኮሩ ምክሮችን ለግሰዋል።

እውነተኛ ደቀ መዛሙርት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “እውነተኛ ደቀ መዛሙርት” ባሉት መልዕክታቸው እንደገለጹት፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ለአልዓዛር እህት ማርታ እና ለማርያም በተናገረው መሠረት፥ የእውነተኛ ደቀ መዝሙር አቀራረብ የእግዚአብሔርን ቃል መስማት እንደሆነ አስታውሰው፥ ማርያምም ጌታ ወደ ቤቷ እንደ ገባ ስትገነዘብ ነገር ግን ወደ ልቧም እንዲገባ በመፈልግ እርሱን ለመስማት በእግሩ ሥር በመቀመጥ ምን ጊዜም የማይወሰድባት የተሻለ ሥፍራ መምረጧን አስረድተዋል።

እንደ ማርያም ለቃሉ ታማኝ መሆን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመቀጠል ሌላዋ እውነተኛ ደቀ መዝሙር የናዝሬቷ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንደሆነች በማስታወስ፥ እግዚአብሔር ወደ ቤቷ ገብቶ ባናገራት ጊዜ ቃሉን በልቧ ተቀብላ የእቅዱም ተካፋይ በመሆን ልጁን ሲልክ ፈቃደኛ መሆኗን ሙሉ በሙሉ ማሳየቷን አስረድተዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን በመስቀሉ ሲያድን ማርያም በሥፍራው እንደ ነበረች፣ በጴንጤቆስጤ ዕለት ቤተ ክርስቲያኑን ሲመሠርት ሐዋርያትን ስትከተል እንደ ነበረች፣ የእግዚአብሔርን ቃል በመቀበል ተልዕኮዋን በታማኝነት መፈጸሟን አስታውሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወጣቶችን “በተመሳሳይ መንገድ እውነተኛ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንድትሆኑ ተጠርታችኋላ” ብለዋል። በፌስቲቫሉ የተገኙት ወጣቶች በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት ቆመው በእግዚአብሔርን ቃል ላይ እንዲያሰላስሉ እና እርሱ ለእያንዳንዱ ወጣት ያወጣውን እቅድ አውቀው እንዲተባበሩ፣ አእምሮአቸውን እና ልባቸውን እንዲያበራላቸው በጸሎት ጠይቀው፥ በዚህም ምክንያት ከቅዱስ ወንጌል ጋር የጠበቀ ግንኙነትን እንዲመሠርቱ እና በልባቸው እንዲይዙት በማበረታታት የመንገዳቸው መሪ ሆኖ እንዲያገለግል አሳስበዋል።

በመንፈስ ጠንካራ እና ጥበበኛ መሆን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመቀጠልም እውነተኛ ደቀ መዝሙር ጥበበኛ እና በመንፈስ የበረታ እንደሆነ ገልጸው፥ “የእግዚአብሔርን መንግሥት ለሌሎች ማስተላለፍ እና ቃሉን መስበክ የካህናት፣ የገዳማውያት እና የገዳማውያን ግዴታ ብቻ ሳይሆን የወጣቶችም ግዴታ ነው” በማለት አስረድተዋል።

በፌስቲቫሉ ላይ የተገኙት ወጣቶች በቤተ ሰቦቻቸው፣ በትምህርት ቤቶች፣ በሥራ ቦታዎች እና በትርፍ ጊዜያት ሁሉ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ለመነጋገር ድፍረት እንዲኖራቸው አበረታትተው በተለይም በሕይወታቸው ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲገለጥ እና ዕለት በዕለትም ከወንጌል ጋር በሚስማማ መልኩ ውሳኔ እንዲያደርጉ መክረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጨረሻም፥ እያንዳንዱ ወጣት የቤተ ክርስቲያን እናት ለሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ራሱን እንዲያቀርብ፥ ከእግዚአብሔር ጋር ለመነጋገር እና ስለ እርሱ ለመመስከር ጥንካሬን እና ጥበብን እንድታማልድላቸው ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል በመማጸን መልዕክታቸውን ደምድመዋል።
 

03 August 2024, 17:14