ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የጣሊያን የመብራት ኃይል ኩባንያ አባላትን በቫቲካን ተቀብለዋል ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የጣሊያን የመብራት ኃይል ኩባንያ አባላትን በቫቲካን ተቀብለዋል  (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የንጹሕ ኃይል አቅርቦት ታዳሽ ምንጮችን እና ኃላፊነት ያለበት ፍጆታን እንደሚጠይቅ ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጣሊያን የመብራት ኃይል ኩባንያ አባላትን በቫቲካን ተቀብለው አነጋግረዋል። ቅዱስነታቸው ለአባላቱ ባሰሙት ንግግር በንጹህ ኃይል አቅርቦት፣ በግልጽነት እና በሥነ-ምግባር ሃላፊነት ላይ ያላቸውን ቁርጠኝነት አወድሰው፥ ይህም ለጋራ ጥቅም እና ለአካባቢ ጥበቃ አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ቴርና” የተሰኘው የጣሊያ የመብራት ኃይል ኩባንያ በጣሊያን እና በአውሮፓ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ ትልቅ ሚና ከሚጫወቱት መካከል አንዱ እንደሆነ እና አባላቱ ለጋራ እና ለእያንዳንዱ ሰው ጥቅም የቆሙ መሆናቸውን ቅዳሜ ነሐሴ 25/2016 ዓ. ም. በቫቲካን ተቀብለው ባደረጉት ንግግር ገልጸዋል።

ቅዱስነታቸው በመቀጠልም የመብራት ኃይል አቅርቦት የብዙ ሰዎች ሥራ እና ጥረት መሆኑን ሳንገነዘብ እንደ ዋዛ እንደምንመለከተው ገልጸው፥ “በኢነርጂ መሠረተ ልማት ግንባት ላይ በሥራ ላይ እያሉ የወደቁትን መርሳት እንደማይገባ እና ተመሳሳይ አደጋ ከእንግዲህ ወዲህ እንደማይደርስ እናረጋግጥ!” በማለት ተናግረዋል።

ለተሻለ የወደፊት ሕይወት ቁርጠኛ መሆን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ቴርና” የተሰኘው የጣሊያ የመብራት ኃይል ኩባንያ በንፁህ ኃይል አቅርቦት ላይ ለመሥራት ያሳየውን ቁርጠኝነት በማጉላት፥ በብዙ ቅሪተ አካላት እና ታዳሽ ባልሆኑ ምንጮች ምክንያት በምድራችን ላይ ንጹሕ ያልሆነ የኃይል አቅርቦት መኖሩን ተናግረው፥ ነገር ግን ደግሞ በፍትህ እጦት፣ በጦርነቶች እና በስልጣን ጥመኝነት፣ ፍትሃዊ ባልሆነ የሠራተኛ ግንኙነት፣ ከፍተኛ ትርፍን በመሰብሰብ የንግድ ግንኙነቶችን እና ዘላቂ የሥራ ዕድልን በማጥፋት የሰዎችን ሕይወት የሚበክሉ የቆሸሹ እጆች መኖራቸውን አስረድተዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት የቴክኖሎጂ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፥ ምርት እና ፍጆታ ከጊዜ ወደ ጊዜ ፍትሃዊ እና ሁሉን አቀፍ መሆን እንዳለበትም አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የኢነርጂ አካታችነት እና የኢነርጂ ዴሞክራሲ ብዙ ገጽታዎች ያሉት ፈተና እንደሆነ አስረድተው፥ “አንድ ሰው የኃይል አቅርቦት ርዕሠ ጉዳይ ሆኖ ከቀጠለ ሉዓላዊ ዜጋ ሊሆን አይችልም” በማለት፥ “በዚህም ምክንያት የኃይል አቅራቢ ማኅበረሰቦች መስፋፋት ሊደገፍ እና ሊበረታታ የሚገባው ነው” ብለዋል።

በኢንዱስትሪው ሊኖር የሚገባ ግልጽነት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቫቲካን ለተቀበሏቸው የጣሊያን የመብራት ኃይል ኩባንያ የሥነ ምግባር ኮሚቴ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ግልጽነትን ዓላማቸው እንዲያደርጉት አደራ ብለው፥ እያንዳንዱ ትልቅ ኩባንያ መኖሩ ለአንድ አገር አስፈላጊ መሆኑን አበክረው ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመቀጠል “ኔትዎርክ” የሚለው ቃል በብዛት ጥቅም ላይ መዋሉን አስታውሰው፣ “ኔትወርክ” ለሰብዓዊ ትብብር እና ለመግባባት በከፊል ሆነ በጠቅላላ መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያሳድግ መልካም ዘይቤ ነው በማለት አስረድተዋል።

ሕይወትን መቀየር

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከጥቂት አሥርተ ዓመታት በፊት  የጣሊያ የመብራት ኃይል ኩባንያ “ቴርና” በድሆች ቤት ውስጥ ብርሃንን ለማምጣት ይሠራ እንደነበር አስታውሰዋል።

በጦርነት ወቅት፣ በከተሞች ውስጥ መጀመሪያ የሚወድመው መሠረተ ልማት የመብራት ኃይል መሆኑ በአጋጣሚ እንዳልሆነ፥ ምክንያቱም የዚህ መሠረተ ልማት ውድመት የቤተሰብን ሕይወት በቀጥታ የሚነካ እና የሕዝቡን ሞራል የሚቀንስ መሆኑን አስረድተዋል።

“ወዳጆቼ ሆይ! ሥራ ማኅበራዊ ፍቅር እና ወንድማማችነት ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “የኃይል አቅርቦትን በማመቻቸት እና በማሰራጨት የማሰብ ችሎታችሁን፣ ነፍሳችሁን፣ ልባችሁን እና ፍቅራችሁን ሥራ ውስጥ ታስገባላችሁ” ብለው፥ መል እክታቸውን ሲያጠቃልሉ “የሥራን ክቡርነት የበለጠ በማስታወስ የበለጠ ልታመሠግኑ ይገባል” ብለዋል።

 

31 August 2024, 16:03