ር.ሊ.ጳ. በኢየሱስ የተገኘውን የሰማይ እንጀራ ስጦታ በደስታ ልንቀበል ይገባል ማለታቸው ተገለጸ!
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ- ቫቲካን
ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በእለቱ ያደረጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከታተሉን።
የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ! መልካም እለተ ሰንበት ይሁንላችሁ!
የዛሬ ቅዱስ ወንጌል ስለ ኢየሱስ ይነግረናል፣ እሱም በቀላሉ፡- “ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ” (ዮሐ. 6፡51) ይለናል። በሕዝቡ ፊት፣ የእግዚአብሔር ልጅ ራሱን በጣም በተለመደ እና በምናውቀው ምግብ- “እንጀራ እኔ ነኝ” በማለት ራሱን ገልጿል። እርሱን ከሚሰሙት መካከል፣ አንዳንዶች እርስ በርሳቸው መጨቃጨቅ ጀመሩ (ዮሐ. 6፡52)፡ ኢየሱስ እንዴት እንድንበላ የራሱን ሥጋ ሊሰጠን ይችላል? ዛሬም ቢሆን ይህን ጥያቄ ራሳችንን እንጠይቃለን፥ ግን ይህንን ጥያቄ የምንጠይቀው በአስደናቂ እና በአመስጋኝነት መንፈስ ነው። እዚህ ላይ በሁለት ነገሮች ላይ ማሰላሰል እንችላለን፣ ሁለት አመለካከቶች አሉ፡ ከቅዱስ ቁርባን ተአምር በፊት መደነቅ እና ምስጋና የሚሉትን ቃላት እናገኛለን።
በመጀመሪያ፡ መደነቅ የሚለውን የምናገኘ ሲሆን ይህም የኢየሱስ ቃል ያስገርመናል የሚለውን ትርጓሜ ይሰጠናል። ኢየሱስ ግን ሁሌም ያስገርመናል፣ ሁሌም! ዛሬም፣ በእያንዳንዳችን ሕይወት፣ ኢየሱስ እኛን እያስገረመን ነው። ከሰማይ የመጣው እንጀራ ከሚጠበቀው ሁሉ በላይ የሆነ ስጦታ ነው። የኢየሱስን መንገድ ያልተረዱት ተጠራጣሪ ሆነው ይቆያሉ፡ የሌላውን ሥጋ መብላት ኢሰብአዊ እና የማይቻል ይመስላል (ዮሐ. 6፡54)። ሥጋ እና ደም የአዳኙ ሰብዓዊነትን የሚገልጹ ናቸው፣ እርሱ ራሱ ሕይወቱን ለራሳችን መብል አድርጎ ያቀርባል።
ይህ ደግሞ ወደ ሁለተኛው አመለካከት ያመጣናል፣ ይህም ምስጋና የሚለው ነው። አንደኛው ማስገረም ወይም ማስደነቅ የሚለው ሲሆን አሁን ደግሞ ወደ ሁለተኛው ምስጋና ወደ ሚለው እንሸጋገራለን። ምስጋና፣ ኢየሱስ እራሱን ለእኛ እና ከእኛ ጋር ባቀረበበት ቦታ ስለምንገነዘበው ነው። ስለ እኛ ራሱን እንጀራ አደረጎ ሰጠን።“ሥጋዬን የሚበላ ሁሉ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለሁ” (ዮሐ. 6፡56)። እውነተኛው ሰው ክርስቶስ ሰው ለመኖር መብላት እንዳለበት ጠንቅቆ ያውቃል። ነገር ግን ይህ በቂ እንዳልሆነም ያውቃል። ምድራዊውን እንጀራ በተአምር ካባዛ በኋላ (ዮሐ. 6፡1-14)፣ ከዚህም የሚበልጥ ስጦታ ያዘጋጃል፡ እርሱ ራሱ እውነተኛ ምግብና እውነተኛ መጠጥ ይሆናል (ዮሐ. 6፡55)። አመሰግናለው ጌታ ኢየሱስ! በሙሉ ልባችን “አመሰግናለሁ፣ አመሰግናለሁ” እንበል።
ከአብ የሚመጣው ሰማያዊው ኅብስት ወልድ ራሱ ስለ እኛ ሥጋ አደረገ። ይህ ምግብ ሁላችንም በሆዳችን ሳይሆን በልባችን ውስጥ የሚሰማንን የተስፋ ረሃብን፣ የእውነትን እና የመዳንን ረሃብ ስለሚያረካ ከሚያስፈልገው በላይ ነው። እያንዳንዳችን ቅዱስ ቁርባን ያስፈልገናል!
ኢየሱስ ትልቁን ፍላጎታችንን ይንከባከባል፡ እርሱ ያድነናል፣ ህይወታችንን በራሱ ሥጋ ይመግባል፣ እናም ይህንን ለዘላለም ያደርጋል። ከእግዚአብሔር ጋር በኅብረት መኖር እንድንችል ለእርሱ ምስጋና ይግባውና ይፈልጋል። ህያው እና እውነተኛው እንጀራ አስማታዊ ነገር አይደለም፥ በፍጹም እንዲህ አይደለም። ለችግሮች ሁሉ ወዲያውኑ መፍትሄ የሚሰጥ ሳይሆን ለድሆች ተስፋ የሚሰጥ እና በድሆች ኪሳራ እብሪተኞች የሆኑ ሰዎችን የሚያሸንፈው የክርስቶስ አካል ነው።
ወንድሞቼ እና እህቶቼ እስቲ እራሳችንን እንጠይቅ፥ እኔ ለራሴ ብቻ ሳይሆን ለመላው ወንድሞቼና እህቶቼ መዳን እራብና እጠማለሁኝ ወይ? የምሕረት ተአምር የሆነውን ቅዱስ ቁርባንን ስቀበል፣ ስለ እኛ በሞተውና በተነሣው በጌታ ሥጋ ፊት በፍርሃት ቆሜያለሁን?
በዚህ የኅብስቱ ምልክት መንግሥተ ሰማይን እንድንቀበል ትረዳን ዘንድ ወደ ድንግል ማርያም አብረን እንጸልይ።