ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ከ33 ዓመታት እስራት በኋላ የተፈታ እረኛን ማግኘታቸው ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የአቀባበል ሥነ-ሥርዓቱ ቫቲካን ውስጥ በሐዋርያዊ ቤተ መፃህፍት ውስጥ መካሄዱ ታውቋል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1991 ዓ. ም. በ26 ዓመቱ የታሰረው ቤኒያሚኖ ዙንቸዱ አሁን በ60ዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኝ ሲሆን፥ “ሦስት ሰዎችን ገድሏል” በማለት በሐሰት ለከሰሰው ግለሰብ ይቅርታ ማድረጉን ገልጾ፥ በኋላም ክሱ መሠረዙን ተናግሯል።
የጣሊያን የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ዙንቸዱን ከ33 ዓመታት እስራት በኋላ ማለትም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ያለፈው ጥር ወር 2024 ዓ. ም. ነፃ ማድረጉ ታውቋል።
ዙንቸዱ ከጠበቃው ጋር በመሆን፥ በጣሊያንኛ “ኢዮ ሶኖ ኢኖቸንተ” ሲረተጎም “እኔ ከወንጀሉ ንፁህ ነኝ” የተሰኘ መጽሐፍ ዓርብ ነሐሴ 17/2016 ዓ. ም. ጠዋት ከቅዱስነታቸው ጋር በተገናኘበት ወቅት በስጦታነት ማቅረቡ ታውቋል።
ዙንቸዱ ለረጅም ጊዜ እስር ቤት ውስጥ ያሳለፋቸውን አሳዛኝ ገጠመኞችን ሲያስታውስ፥ በሦስት የተለያዩ እስር ቤቶች መቆየቱን፣ አንዳንድ ጊዜም ከአሥራ አንድ ሰዎች ጋር በትንሽ ክፍል ውስጥ እንዲቆይ መደረጉን፣ የመታጠቢያ እና የመኝታ ቦታ ችግር ያጋጥመው እንደነበር በመጽሐፉ ውስጥ ጠቅሷል።
ድርጊቱ ኢ-ሰብዓዊ መሆኑን የጠቀሰው ዙንቸዱ፥ ከእርሱ የባሰ ችግር ውስጥ የሚገኙትን መርዳት መቻሉን ገልጾ፥ በእግዚአብሔር በመታመን እና ቤተሰቡን በማሰብ ጥንካሬን ሊያገኝ መቻሉን ተናግሮ፥ በመጽሐፉ ውስጥ “ነፍሰ ገዳይ ነው” ብሎት የከሰሰውን ሰው ይቅር ማለቱን እና በኋላም ክሱ መሰረዙን ዙንቸዱ ተናግሯል።